Wednesday, April 30, 2014

ብላቴ 1

መጋቢት ፪፪  ፩፱፰፫ አ.ም.
ከምሽቱ ፬ ሰዓት ከ ፶ ደቂቃ
ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ፭ተኛ ብርጌድ ፫ተኛ ሻለቃ ፪ተኛ ሻምበል መኝታ ክፍል

 ስለ ብላቴ ምንነት: እንዴትነትና መልካምድር ወዘተ አሁን ለመተንተን አልፈልግም ግን በአጭሩ ቦታው ጫካ + ተራራ+ ወንዝ+ ድንጋይ+ ጭለማ+ ዝናብ+ ዓቡዋራ+ እሾህ+.......ነው:: ዛሬ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቁዋም ከደረስን ሳምንት ተጠግቷል::

በዚህ ቀን ሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ከአልጋችን ተነስተን ወደ ቁርስ እንድንሄድ በፊሽካ ስንታዘዝ ብንበሳጭም ወደሁዋላ ላይ የ ደቡብ ዝ ኦርኬስትራ በሙዚቃ "ሊያዝናንን"" መሆኑን ሰምተን ተረጋጋን:: በየሻምበላችን ተከፋፍለን ታዳሚ ወደሚቀመጥበት ኮረብታ እየዘፈንና እየሮጥን (ሞራል አውጥተን) እንድንሄድ ታዘዝን:: አብዛኛው ተማሪ እንደኔ በሰሞኑ የጠዋት ስፖርት የተነሳ ስትራፖ የያዘው: ባይዘውም እየዘፈነ ለመሮጥ ወኔ የሚያጥረው ስለነበር ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ የሄድነው በተልፈሰፈሰ ርምጃ ነበር::

እንደምንም ኮረብታዋ ጋር ደረስን:: ወደ ኮረብታዋ ቀድመው ከመጡና ሰማያዊ ቱታ ከለበሱ ሌሎች ሰልጣኝ ወንዶች ጋር ተቀላቀልን:: ከኛ በመቀጠል አሰልጣኞቻችን የሆኑት አየርወለዶች መጡ:: በመጨረሻ ሴት ሰልጣኞች መጡ:: በዚህ ግዜ ሰልጣኝ ወንዶች ያሰሙት ጩህት በክብር እንግድነት ተማሪው መሃከል የተቀመጡትን የማሰልጠኛው አዛዥ ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያምን ሳያስደነግጣቸው አልቀረም:: የጤና አልነበረም:: ለነገሩ አልገረመኝም:: ባለፉት አምስትና ስድስት ቀናት "በፍላጎታችን ነው የመጣነው" በሚል ሰበብ መረን የለቀቀና ከሥርዓት ውጭ የሆነ ባህሪ የሚያሳዩ ተማሪዎች ቁጥራቸው ጨምሯል:::

ኮረብታዋ ላይ አስር ሺህ የሚሆን ወታደራዊ ሰልጣኝ የኮሌጅ ተማሪ በሙሉ ግጥም ብሎ ከስር ከድንጋይ ና ከቀይ አሸዋ ክምር የተሰራ መድረክ ብጤ ጉብታ ላይ የሙዚቃ ባንዱ ይጫወታል: ይነፋል: ያቅጨልጭላል:: ዘፋኝ በየተራ ያቀነቅናል...እድሜ ላመንግስቱ ሃይለማርያም....

በመድረኩ ና በተቀመጥንበት ኮረብታ መሃል ለወትሮው የመኪና መንገድ የሆነ ክፍት ቦታ ላይ ተማሪ ግጥም ብሎ ይወራጫል:: መድረኩም ላይ በብዛት የሚታዩት ሰማያዊ ለባሽ ተማሪዎች ናቸው:: በዕለቱ የቀረበው ሙዚቃ ና ዘፈን ስሜት የሚነካ ቢሆንም ብዙ ደናሽ ነኝ ባይ ተማሪ የሚወራጨው በደመነፍስ መሆኑን ልገነዝብ ችያለሁ:: የሙዚቃው ሪትምና የነዚህ ተማሪዎች መወራጨት (ዳንስ) በጭራሽ አብሮ አይሄድም:: እኔም ከተራራው ለመውረድና ለመወራጨት ፈልጌ ነበር: ግን መሬቱ ሩቅ ከመሆኑም ባሻገር ትናንት የሰራሁት ስፖርት ጡንቻዬን ሽምቅቆት ነበር:: ስለዚህ ፍላጎቴን ገታሁት:: 

ሙዚቃው ከሰዓት አጋማሽ ላይ ተጀምሮ ወደ አመሻሹ የዘለቀ ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎች ከማሰልጠኛው አስር ና ሃያ ኪሎ ሜትር ድረስ ሄደው አረቄና ጠጅ ጠጥተው እንደመጡ የሆነ ሰው ሹክ ብሎኛል::

የመድረኩ ላይ ትርምስ ና ግርግር የትየለሌ ነበር:: ገና አቀንቃኙ ከጉሮሮው ድምፅ ሳይወጣ መድረኩ በአልባሌ ተወራጮች ይሞላል:: በተለይ የማልረሳው አቀንቃኝ አረጋሀኝ ወራሽ የሚዝፍንበትን የድምፅ ማጉያ ወደአፉ ማስጠጋት እስኪያቅተው ድረስ በተማሪዎች ሲዋጥ እንደነበር ነው :: አየርወለዶቹ በተማሪዎች ሁኔታ ብስጭት እንደገባቸው ግልፅ ነው:: ቢችሉ እያንዳንዱን በጫማ ጥፊ እያሉ ቢያስተኙት በወደዱ:: ዳሩ ምን ያደርጋል "በፍላጎታቸው ስለመጡ: እንዳትነኩዋቸው" ተብለው ታዘዋል አሉ::

Wednesday, April 23, 2014


ሠላም

አውቃችሁም ሆነ በስህተት የምጭረውን ስትከታተሉ የነበራችሁ ሁሉ: መጫሬን እንደምቀጥል ልንግራችሁ ፈልጌ ነው:: 

በቅርብ ግዜ ብላቴ የሚባለው የወታደሮች ማሰልጠኛ ከደረስን በሁዋላ አለፍ አለፍ ብዬ ካሰፈርኩዋቸው ማስታወሻዎች ላይ እየቆነጠርኩ ጀባ እላችሁዋለሁ:: እባካችሁ ታገሱኝ::

መልካም

Tuesday, April 1, 2014

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፭

መጋቢት ፩፮/፩፯ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.

ወደ ብላቴ ስንሄድ ከፍል ፭


የ ወሊሶ ትዝታ
በተማሪዎች የተሞሉት አውቶቡሶች እየተጉዋዙና ደግሞም እያረፉ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ ወሊሶ ከተማ ደረሱ:: ማን እንዳዘዘው ባላውቅም ወሊሶ ዉስጥ ለምሳችን ተብሎ የተዘጋጀ ምግብ ነበር:: ለእራት ሆነ:: ከተማዋ በድቅድቅ ጨለማና በፀጥታ ተውጣለች:: አልፎ አልፎ የኤሌትሪክ ግንዶች ላይ ካሉ አምፑሎች የሚወጣ የደበዘዘ ብርሃን ይታያል:: የአውቶቡሶቹ መብራትና ጉልህ ድምፅ ትንሿን ከተማ ሳያውካት አልቀረም:: እኔና ጉዋደኞቼ ከነበርንበት አውቶቡስ ጋር  ከጅማ እስከ ወሊሶ ያለውን ወጣ ገባ መንገድ ከመጉዋዛችን በስተቀር የቀመስነው እህል ስላልነበር በጣም ርቦን ነበር:: ማንነታቸውን ባላውቅም የሆኑ ሰዎች እየመሩ ምግብ ወደተዘጋጀበት ቦታ ሲወስዱን በወቅቱ የነበረው ብርድ ያዘለ ነፋስ እየተንሿሿ ይገርፈን ነበር:: ከአውቶቡሱ ከወረድን በሁዋላ በአንድ መስመር ሰልፍ ይዘንና መንገዱን ተሻግረን ቀጥ ብለን ከወረድን በሁዋላ ታጥፈን ወደ አንድ የአምፑል ብርሃን ወዳለበት ቤት አመራን:: ምግብ የተዘጋጀበት ቤት ነው:: አምስት አምስት እየሆንን ያገኘነው ቦታ ላይ በመቀመጥ በትሪ ተደርጎ የቀረበልንን እንጀራ በወጥ እየተሻማን በላን::

ከምግቡ በሁዋላ ሁሉም ቀድሞ ያላሰበበት የመኝታ ጉዳይ ነበር:: ብዙም ሳይቆይ አጅበውን ከሚሄዱት ወታደሮች መረጃ መጣ:: አውቶቡሶቹ ውስጥ ቁጭ ብለን ነው ቀሪውን ሌሊት የምናሳልፈው!!! ወይኔ ጉዴ! በበኩሌ እንዴት ሆነን እንድምናድር ግራ ገባኝ:: ቁጭ ብዬ አድሬ አላውቅም:: ደነገጥኩ:: ለእንቅልፍ እንዲሆነኝ የሚያሰክር መጠጥ መጠጣት አማረኝ: ግን በዚያ ሰዓት ግሮሰሪዎችና ቡና ቤቶች በሙሉ ዝግ እንደሚሆኑ ግልፅ ነበር:: ለነገሩ አሰብኩት እንጂ ከ ስድስት ብር በስተቀር ኪሴ ውስጥ ዱዲ አልነበረም:: በእርግጥ ስድስት ብር አደንዝዞ የሚያስተኛ ያበሻ አረቄ ሊገዛ ይችላል:: (ስድስት ብሩ በቀደም ብላቴ ትሄዳላችሁ ሲባል ሁለት ሱሪዎቼንና አንድ ጫማ ሸጬ ካገኘሁት ገንዘብ ላይ የተረፈ መሆኑን ልብ በል/በይ:): 

ወደ አውቶቡሱ ተመለስኩ:: መቀመጫዎች በሙሉ ተይዘው ነበር:: ቀን ስንጉዋዝ የነበርንበት አደራደር አሁን አይሰራም:: እንቅልፍ የጣላቸው ተማሪዎች የተወሰኑትን መቀመጫዎች በሞኖፖል ተጋድመውባቸዋል:: ብዙ ተማሪዎች ግን አልተኙም:: ተቀምጠው እርስ በርሳቸው ያወራሉ:: እነ ጌታቸው ና ኃይሉ አሁንም ሹፌሩ አካባቢ ተቀምጠው ሞቅ ያለ ወሬ ይዘዋል:: የነ መንግስቱን: አምሳሉንና ሚሊዮንን ድምፅ ከወደሁላ አካባቢ እሰማለሁ:: አስግድና አስፋውም እንደዚሁ መሃል አካባቢ ይሰሙኛል:: እኔ እንደቆምኩ ቀረሁ:: ምንም የምቀመጥበት ቦታ ባለመኖሩ በውስጤ ቱግ ብያለሁ:: መራመድ ራሱ አይቻልም:: የተኙ ተማሪዎች እግሮች የመረማመጃውን ቀጭን ኮሪዶር አጥረው ዘግተውታል:: የአውቶቡሱ ውስጥ የጨለመ ሲሆን ከፊል ብርሃን  ደጅ ካሉት የአሌትሪክ ግንድ አምፑሎች ባውቶቡሱ መስኮቶች አልፎ ይገባል:: ከመበሳጨቴ የተነሳ ተናገር ተናገር አለኝ:: ግን የሚሰማ ሲኖር ነው እሱም:: ይህን ስረዳ ለራሴው በከባዱ እህህህህ...ብዬ ተነፈስኩ:: ራሴን አሞኝ ነበር:: የሚስማማኝ መቀመጫ ላገኝ ስላልቻልኩ እንደቆምኩ ቀረሁ:: ለነገሩ እኔም አጠፋሁ :: የተገኘው ላይ መቀመጥ ሲገባኝ የሚስማማኝ መቀመጫ መሻቴ:: የተቀመጡት ወሬያቸውን ቀጥለዋል :: አረ ተረት ተረትም የሚያወራ አለ! "ተረት ተረት" ይላል የፕሪሜዱ አስፋው " አንዳንድ አጠገቡ የነበሩ ተማሪዎች የድካም ሳቅ ይስቃሉ "ኢሂ..ኢሂ.........ኢሂ...........ሂ":: በርትቶ የላምበረት የሚል አልሰማሁም:: ራቅ ብዬ ስለነበር ተረቱ ስለምን እንደሆነ ልሰማ አልቻልኩም::

ቀስ በቀስ እንደቆምኩ ሰዓቱ ሄደ:: ወሬዎቹ አልቀነሱም::  እንዳውም ጨመሩ:: የተቀመጡ ተማሪዎች የተኙትን መቀስቀስ ጀመሩ በተራቸው ለመተኛት:: "አንተ ተነስ እንጂ አሁን ደግሞ የኔ ተራ ነው" የሚሉ ድምፆች ሰማሁ:: "ምምም......ንንንን.." ይላል የተኛ ሰው ድምፅ በእንቅልፍ ልብ አይነት:: ሰዓቱን በትክክል ባላስታውስም የሌሊቱ አጋማሽ ላይ አስፋውና ሚሊዮን በሆነ ነገር ተጣሉ:: ከተረቱ ጋ የተገናኘ ሊሆን ይችላል:: ድንገት ግርግር ሆነ:: ሊደባደቡም ተነሱ:: አስፋው እጅግ በጣም እንደተናደደ ፊቱ ላይ ያስታውቅ ነበር:: በከፊል ብርሃንም ቢሆን ፊቱ መቅላቱን አስተውያለሁ:: ከገላጋዮች ተቀላቀልኩ:: ልናገላግል በመሃል የገባነውን ሁሉ አስፋው "ዋ! ተጠንቀቁ" አለን:: እንደውም አብይንም ሊጣላው ፈለገ:: ማስረሻንም እንዲሁ:: እኔ እንደዚያ በራሴ ብስጭት ውስጥ ሆኘ የአስፋው ንግግሮች ፈገግ አስኙኝ:: የሰከረ ወይም የቀወሰ ነው የመሰለኝ:: "ዋ ይሄን ልጅ እረፍ በሉት:: እኔ ሰው እጄ ላይ አልበረክት ብሎኛል" ይልና ትንሽ ቆይቶ ደግሞ "ዋ ይሄ ልጅ በጄ ሰበብ እንዳይሆን" እያለ ይጮሃል:: እዚያ ያለነው አብዛኞችችን ቀጫጭን የነበርን ቢሆንም አስፋው ደሞ ከኛም ይቀጥን ነበር......

ግርግሩ እንደምንም በረደና ከለሊቱ አስር ሰዓት ላይ አንድ ይመቸኛል ብዬ ያሰብኩት መቀመጫ ላይ ቁጭ እንዳልኩ አሸለበኝ:: በዚያውም እንቅልፍ ወሰደኝ:: የነቃሁትም ከጠዋቱ ፩፪ ሰዓት ላይ አውቶቡሶቹ ሞተሮቻቸውን ማሞቅ ሲጀምሩ ነው:: ወሊሶ ከተማ ላይ ጎህ ቀዶ ነበር:: መጋቢት ፩፯ ቀን ከጠዋቱ ፩፪ ተኩል ሲሆን ወሊሶን ለቀቅን......