Friday, December 26, 2014

ታህሳስ 28 1984 አ.ም. የገና ዕለት (Long day in Jimma)

ለኔና ለነ መንጌ መታወስ ያለበት ቀን ይህ ይመስለኛል:: የልጅነት ትዝታ.......

የገና ለት ጠዋት ስድስታችንም ማለትም እኔ : መንጌ: አምሳሉ: ሚሊዮን: አብይና ማስረሻ በአሉን ምክንያት በማድረግ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በመሄድ ተሳልመን ወደ ጤና ሳይንሱ ግቢ ተመለስን:: ከዚያም ከቁርስ በሁዋላ ጠዋቱን በጅጤሳ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በተማሪዎች ተዘጋጅቶ በነበረው የፀሎትና መንፈሳዊ ትምህርት ፕሮግራም ላይ ተገኘን: ከአብይ በተቀር:: አዳራሹ  በእጣንና ዑድ ጭስና መአዛ ታውዶ ነበር:: ረዣዥም ሳር ፈንጠር ፈንጠር ብሎ በሰፊው አዳራሽ ውስጥ ተጎዝጉዙዋል:: በአዳራሹ አንድ ወገን እንደ መድረክ አይነት የተዘጋጀ ቦታ ይታያል:: መሃል ላይ የየሱስ ክርስቶስ ስዕል የታያል በግራና በቅኝ የሚበሩ ሻማዎች የተሸከሙ ቀንዲሎች አሉ:: ከመድረኩ ፊትለፊት ጀምሮ እስከአዳራሹ መሃል ድረስ ያሉት መቀመጫ ወንበሮች በተማሪ ና በመምህራን ታዳሚዎች ሞልተዋል:: ነጠላ የለበሱ ተማሪዎች አንገታቸውን ደፍተውና ድምፃቸውን ዝቅ አርገው ከወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ታዳሚውን ያስተናግዳሉ.......

ስድስታችን ከሰዓት በሁዋላ ተበታትነን የዋልን ሲሆን እኔና አምሳሉ አንድ ላይ ነበርን:: ከተማ መሃል የምትኖር አንዲት የአምሳሉ ዘመድ የሆነች መምህርት ቤት ሂደን ጠላ እየጠጣን ስንጫወት ቆየን::

ምሽቱን ሁላችንም ወደጤና ሳይንሱ ግቢ ተመልሰን ተገናኘን:: ለቀናት ተቁዋርጦ የነበረው መብራት ስለተመለሰ ደስ ብሎን ነበር:: በዚህም የተነሳ ምሽቱን የዳንስ ምሽት ለማድረግ በመስማማት አባይን ጨምረንና ሰባት ሆነን ፊልተር ለመጠጣት ዘውትር በንዲህ አይነት ወቅት ጎራ ወደምንልበት ግሪን ሆቴል አመራን:: ሰዓቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ይል ነበር:: ግሪን ሆቴል ወለሉ በሳር ጉዝጉዋዝ ተሸፍኖ አመትባል መሆኖኑን ይናገራል:: ደስ የሚል መንፈስ ነበረው:: በግሪን ሆቴል ቆይታችን አምስት ጠርሙስ ፊልተር ለሰባት ጠጣን:: ይህ ክፍፍል አናሳ ቢሆንም ሁላችንም ከሰአቱን በየፊናችን ጠጥተን ስለነበር እኔና መንጌ ይበቃል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ነበር:: ስለዚህም ሌሎቹም ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ከዚያ በላይ እንዳንጠጣ ከለከልን:: ነገር ግን ከአባይ በስተቀር ሌሎቹ በኔና በመንጌ  ሃሳብ አልተስማሙም:: የሆነ ሆኖ ግሪን ሆቴል ፊልተር አለቀ ተባለ:: ስለዚህም ሁላችንም ቤቱን ለቀን ወጣን:: እኔ መንጌና አባይ ወደ ጤና ሳይንሱ ለመመለስ ስንሻ እነ አብይና አምሳሉ ደሞ ለጉዳይ የሆነ ሰው ጋ እንሄዳለን በሚል ሰበብ ተለዩን:: እኔ ሁላችንም ተመልሰን ዶርማችን ገብተን እንድንጨፍር በመፈለጌና ያም ስላልተሳካ ክፉኛ ተበሳጭቼ  ሞቅታዬም በርዶ ወደ ጅጤሳሳ ተመለስኩ::

መንጌና አባይም አብረውኝ የተመለሱ ሲሆን ዋይት ሃውስ ጋ ስንደርስ ተለያየን:: እኔ ወዲያውኑ ተስፋሁነኝ የተባለ ጉዋደኛየን አገኘሁትና ሻይ ለመጠጣት ተያይዘን ወደ ውጭ ወጣን:: ከተስፋሁነኝ ጋ ብዙ ተጫወትን:: ብስጭቴም ለቀቀኝ:: ሻይ ጠጥተን ስንመለስ ሰዓቱ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ሆኖ ነበር:: ምሽቱ መቼም በጠፍ ጨረቃ የታጀበና የማይበርድ ብሎም የምይሞቅ ደረቅ የታህሳስ ምሽት ነበር:: በዚያ ሰዓት ከነአብይ ና መንጌ ጋ መንገድ ላይ ተገናንኘን:: እነአብይን ሳያቸው ንዴቴ አገረሸ:: አይኔን አጉረጠረጥኩ:: እነሱ ደሞ ነገር ለማለዘብ እኔን ዋይት ሀውስ ፈልገው አጥተውኝ ከመንጌ ጋ ሆነው እንደገና እየፈለጉኝ ነበር:: ስላጡኝ ይበልጥ ተበሳጭተውብኛል ለካ...የነሱ ንዴት ከኔ እንደሚበልጥ ስለተገነዝብኩ ለዘብ አልኩና እንደውም ላግባባቸው ሞከርኩ:: ነገር ግን በዚያው ቅፅበት በተመሳሳይ አርዕስት አብይና መንጌ ለብቻቸው ባደረጉት ክርክር ኃይለኛ አለመግባባት ውስጥ ገቡ:: አብይ ክፉኛ አኮረፈ:: ስለዚህ ሁለቱን ማግባባት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ አደረኩ:: የመንጌና የአብይን ጭቅጭቅ ቆሞ ሲከታተል የነበረው አምሳሉ በበኩሉ ሁኔታውን እንዳለ ጥሎ ለመሄድ ወሰነ:: ከብዙ ንግግሮችና የቃላት ምልልሶች በሁዋላ እንደገና እሱንም አግባብቼ ሁላችንም ወደ ዶርም 006 ተመለስን::

ሀሳባችን ቅድም ተነጋግረን የነበረውን ዶርም ውስጥ የመጨፈር ፕላን ለማሳካት ነበር:: ዶርም እንደደረስን አብይ ትናንትና አምጥቶት የነበረውን ቴፕ ሪኮርደር ከራሱ ሎከር ውስጥ ላወጣው ቁልፉን ከመንጌ ተረከብኩ:: ቴፕ ሪኮርደሩ ሌላ ዶርም ውስጥ ስለነበር አውጥቼው እስከምመለስ አብይና ማስረሻ ከዶርም 006 ተሰውረዋል:: አሁን ተስፋ በጣም ስለቆረጥኩ እዚያ የነበሩትን በሙሉ “በሉ ደህና እደሩ: ማንኛችን ጥፋተኛ እንደሆንን እግዜር ይወቀው: ሁላችንም ግን በሆዳችን ክፉ እንዳናስብ” ብዬ ተሰናብቼ ወጣሁ:: ትንሽ እንደሄድኩ አምሳሉ ከሁዋላዬ እየተከተለኝ መጥቶ “እባክህ ሳምሶን በቃ ተመለስና ወጥተን ሻይ እንጠጣ” አለኝ:: እኔም እሺ በማለት ከአምሳሉ: ከመንጌ ና ከሚልዮን ጋ ከዋይት ሃውስ ወዲያ በሚወሰደው መንገድ አርገን ወደ ጤና ሳይንሱ መውጫ በር አቅጣጫ ሄድን:: በመንገዳችን ላይ የተማሪዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ ስንደርስ ከአዳራሹ ውስጥ ከፍተኛ የሙዚቃ ድምፅ ይሰማ ነበር:: “አሀ እዚህ ፓርቲ አለ ማለት ነው?” ብለን ወደ አዳራሹ በር ስንጠጋ አብይና ማስረሻን አገኘናቸው:: በወቅቱ የተዘጋውን ረዥም የአዳራሽ በር ለማስከፈት ከሚጥሩ ሌሎች ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው ነበር:: አብይና ማስረሻን ይዘን ሻይ ለመጠጣት በሚል ጅጤሳን ለቀን ወጣን:: እዚህ ጋ ቁጥራችን ልክ እንደጠዋቱ ስድስት ሆነ ማለት ነው:: ሁላችንም ሞቅታችን በርዶ ስለነበር ከሻይ ይልቅ ወንድማማቾች ቡና ቤት ሂደን መጠጥ ለመጠጣት ተስማማን:: እዚያም ለስለስ ያለ ጠጅ ጠጣን:: ጥቂት ዘና አልን ሁላችንም:: እኔ በበኩሌ ለስለስ ያለ ሞቅታ ተሰማኝ:: ያቺ ለስላሳ ሞቅታ ሳታልቅ ወደ ዶርማችን ተመለስን: ዶርም 006:: እንደደረስን ያን መከረኛ ቴፕ ሪኮርደር ከተቀመጠበት አውጥተን ዘፈን ከፈትን: ድምፁንም እስከ መጨረሻው ለቀቅነው:: ሁላችንም እጆቻችንንና እግሮቻችንን ማወራጨት ጀመርን: ዳንስ ማለት ነው:: አንዳድንድ የተኙ ተማሪዎች ወደውና በግዳቸው ተነሱ:: ቆጥ ላይ የወጡትም ወረዱ:: ሙዚቃ የሸተታቸው ከሌላ ዶርም መጡና ተቀላቀሉን:: ኩርፊያ ተረሳ:: የሚችለውም የማይችለውም ባለ በሌለ ኃይሉ ይድንስ ገባ:........................all night long....all night.....all night ...


ቀደም ብሎ ለነበረው አለመግባባት ሁላችንም እርስ በርስ ተወነጃጅለናል: ጥፋተኛንውን ግን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው:: አብይ ከማስረሻ በስተቀር ሁላችንንም ይወነጅላል: በተለይም መንጌን:: መንጌ ደሞ በመጀመሪያ አብይን ቀጥሎም እኔንና ሌሎቹን ይከሳል:: እኔ ደግሞ አራቱን ማለትም አብይን: ማስረሻን: ሚልዮንና: አምሳሉን ቁዋጥሬባቸው ነበር:: እነሱ ደሞ አራቱም በኔ ተበሳጭተዋል:: 

Wednesday, December 17, 2014

ታህሳስ ሃያዎች-አስራዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.
የፍረሽማን ማጠቃለያ ፈተና ሰሞን

ለፈተናችን ሶስት ቀን ሲቀረው አራት ትምህርቶች እንደኮሶ አስጠሉኝ: ፊዚክስ: ሶሺዮሎጂ: ፈርስት ኤይድ ኮሙኒቲ  ሄልዝ:: ለትምህርትና ለንባብ የነበረኝን እጅግም ያልጋለ ፍላጎት ይበልጥ በረዶ እንዲሆን ያደረጉት እንዚህ ትምህርቶችና መምህራኖቻቸው ይመስሉኛል: አቤት ስጠላቸው! እርግጠኛ ነኝ ትምህርቶቹን ልጠላ የቻልኩት በመምህራኑ አስጠሊታ አታካች እንዲሁም የተዝረከረከ የማስተማር ዘዴ የተነሳ ነው:: በተለይ ፊዚክስ መምህር.....

የተዋበ መስሎ በሞራል የተጀመረው የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርት በመሃል በዘመቻ ምክንያት ተቁዋርጦ: በመጨረሻው ላይ የሄው እንጨት እንጨት ብሎ ሊጠናቀቅ ነው:: የአንደኛ ሴሚስተር ውጤቴ መልካም የነበረ ቢሆንም ለዚህኛው ፈተና ዳግም ብቻ ሳይሆን የበለጠም ፈራሁ: እወድቅ ይሆን ብዬ...የተማሪ ነገር 

ፈተናው በእንግሊዝኛና በካልኩለስ ተጀመረ:: አቤት ካልኩለስ መቼም ከባድ ነበር:: ሁሉም ተማሪ አማረረ:: እኔ በበኩሌ ከፈተናው ስወጣ ናላዬ ዞሮ ስለነበር በማግስቱ ጠዋት ለሚጠብቀኝ organic chemistry ፈተና ምንም አይነት የመጨረሻ ዝግጅት እንደማላደርግ እርግጠኛ ነበርኩ:: ሆኖም ግን organic chemistry ፈተና ያን ያህል አልከበደኝም ነበር:: organic chemistry በተፈተንበት ቀን ከሰዓት የወሰድናቸው first aid  community health ፈተኖችም ደህና ነበሩ::

በእውነቱ እዚህ ወቅት ላይ ቆም ብዬ በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው ወደ ሁለተኛ ዓመት እንደማልፍ ነው:: በዚህ ምንም ስጋት የለኝም:: ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቴ በአንደኛ ሴሚስተር ከነበረው በጣም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል:: ለነገሩ ምን አገባኝ ካለፍኩ...

organic chemistry ፈተና በወሰድንበት ቀን ማግስት biology ፈተና ይጠብቀኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ምሽቱን ያሳለፍኩት በቴሌቪዥን መመልከቻው አዳራሽ ውስጥ ነበር: relax እያደረኩ::

በተከታዮቹ ቀናት የቀሩትን ትምህርት አይነቶች በሙሉ ተፈተንናቸው:: 

የገና  ዋዜማ ፩፱፰፬ ..

የአንደኛ ዓመት ማጠቃለያ ፈተናችንን ተከትሎ የገና በዓል ታህሳስ ሃያ ስምንት ቀን ተከበረ:: ለወትሮው ሃያዘጠኝ የሚከበር ቢሆንም የዘንድሮው ሃያዘጠኝ ረቡዕ ማለትም የፆም ቀን ላይ ስለዋለ ነው መሰለኝ ከፊቱ ባለው የፍስክ ቀን እንዲከበር ሆነ:: የሆነ ሆኖ በዛሬው በዓል የሚደሰቱ ከሆን ደስ ሊላቸው የሚችሉት ለሃይማኖታቸው ያደሩ ጴንጤ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ይመስሉኛል:: ምክንያቱም ካለፈው አርብ ጀምሮ ዛሬ አምስተኛ ቀን መሆኑ ነው: በጅማ ከተማ የኤሌትሪክ ኃይል ተቁዋርጡዋል:: መብራት የለም:: በዚህም ምክንያት ለማክሰኞ ዋዜማ ሰኞ ምሽት ሊደረጉ ታስበው የነበሩ የመዝናኝና የሙዚቃ ምሽቶች ሳይካሄዱ ቀሩ:: እኔና ጉዋደኞቼም አብይ ተውሶ ባመጣው ቴፕ ረኮርደር ዶርማችን ውስጥ ሙዚቃ እየሰማን ለመጨፈር አቅደን ነበር:: ምን ዋጋ አለው...አልሆነም:: ለነገሩ እነ መንጌ: አብይ: አምሳሉ: ማስረሻ ሚሊዮን ወደ ግሪን ሆቴል ሄደው ጠጣ ጠጣ አድርገው ተመለሱ:: እኔ ያልጠጣሁ ቢሆንም የዋዜማውን ምሽት አብሬያቸው ዋይት ሃውስ በሚገኘው ዶርም 006 ስጫወትና ስዘፍን አመሸሁ:: ዶርሜ ባይሆም እዚያው አደርኩ:: የዶርሙን ጨለማ በገፈፈች አንዲት ሸንቃጣ ሻማ ታግዘን የእንግሊዝኛና የአማርኛ ዘፈኖች እራሳችን እየዘፈንን ዶርሙንም ሆነ አጎራባች ዶርሞችን በጠበጥናቸው:: በተለይ መንጌ አይረሳኝም: ከዚያ ቀን በፊት አሳይቶት በማይውቅ ሁኔታ ይደንስና ይጫወት ነበር……ትዝታ

Thursday, December 11, 2014

ህዳር መጨረሻ ገደማ አስራ ዘጠኝመቶ ሰማንያ አራት ..
ካባለፈው የአውቶቡስ ተራ አጋጣሚ በሁዋላ በተሰማኝ ድንጋጤ ስርዓት ይዤ ትምህርቴን የምቀጥል መስሎኝ የነበረ ቢሆንም ፈፅሞ በጥናት ልተጋ አልቻልኩም:: ከፍተኛ የሆነና ስር የሰደደ የጥናት ፍላጎት ማጣት ውስጥ ገባሁ:: መማር ራሱ አዙሪት ነገር ሆነብኝ:: አለርጂክ! ይህን ከመረዳት የመነጨ ጭንቀት በአምሮዬ በየቀኑ ይመላለስ ገባ:: ቤተ ክርስትያን መሄድ: መፅሐፍ ቅዱስ ማንበብ እንዲሁም ማስታወሻ መፃፍ ጭንቀቴን የሚያቃልል አልሆነም:: የሚገርመው ግን ቀስ በቀስ ጭንቀቱን ለመድኩት:: ከዚያማ የሚያስጨንቀው አለመጨነቅ ሆነ…….ይገርማል

ወደቤት መመለሻዬ ተቃርቡዋል:: የሁለተኛ ሴሚስተር ፈተና ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ ተፈትነን አመቱን እናጠናቅቃለን:: የቤተሰቤን ሁኔታ ለጊዜው አላውቅም:: መልክትም ሆነ የኪስ ገንዘብ ከተላከልኝ ሰነበተ:: ነገር ግን እግዜር ይመስገን: ቢያንስ አባቴ ከእስር ቤት ተፈትቱዋል::

ከምሽቱ አራት ሰዓት በሁዋላ ለጥናት መቆየት ስላቃተኝ ሌሊት ሌሊት አስር ሰዓት ላይ እየተነሳሁ ማንበብ ጀምሪያለሁ:: እየሰራ ያለ ፕላን ይመስላል:: ይህ የጠዋት ሰዓት አእምሮዬ የመጨረሻ ብሩህ ደረጃ ላይ የሚሆንበት ሰዓት መሆኑን ከተገነዘብኩ ውዬ አድሬያለሁ:: እናም ሰሞኑን በዚህ ሰዓት የማነበው ከባዱና ዘግኛኙን Organic Chemistry ነው:: Sociology የሚባለውን ትምህርት አለማንበብ ብቻ ሳይሆን ክፍል ገብቼ የሚሰጠውን ሌክቸር እንኩዋን መከታተል ትቻለሁ:: 



ታህሳስ ስድስት አስራ ዘጠኝመቶ ሰማንያ አራት ..

መልካም ዜና:: አባቴ የማስተማሩን ሥራ እንደገና መጀመሩን በቅርቡ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ሂዶ የተመለሰው የሰፍሬ ልጅ ታጠቅ ነገረኝ:: እህቶቼና ወንድሜም ትምህርታቸውን በሰላም እየተከታተሉ መሆኑን ተረዳሁ:: ታጠቅ እረፍት ላይ ሳለ ወደኔ ቤተሰቦች ቤት ብቅ ብሎ ነበር:: ወደ እረፍቱ ሲሄድ እኔ የፃፍኩትን ደብዳቤ አድርሶ ከነሱ ደግሞ ደብዳቤ: ጥቂት ገንዘብ: ዳቦ ቆሎና ሳሙና ይዞ ተመለሰ:: የቤተሰቡ አባላት: የመጨረሻዋ እህቴን ጨምሮ ደብዳቤ ፅፈው ልከዋል::ቤተሰቤ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በማወቄ በእውነት በጣም ደስ አለኝ:: ቀለለኝም:: በዚህ ቀን ለሁለተኛው ሴሚስተር ማጠቃለያ ፈተናችን የቀረው ሁለት ሳምንት ብቻ ነው:: ጥናት ተጧጧፏል:: ከባዮሎጂ Genetics: Plant Physiology: ከሂሳብ The Theories of Calculus: ከፊዚክስ Thermodynamics: Relativity ፈተና ውስጥ በዋነኝነት እንደሚካተቱ ተነግሮናል:: ብዙ ተማሪዎች ሳይተኙ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት እንደሚቆዩ ለማየት ባልታደልም ሰምቻለሁ:: እኔ ይህችን አጭር ማስታወሻ ፅፌ ለመትኛት ስዘጋጅ ሰዓቱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ ይላል…..