ታህሳስ 22 1988 አ.ም. (ጃኑዋሪ 1፣ 1996 እ.ኤ.አ.)
ሀበሻ ላልሆኑ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ስዎች ዛሬ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ነው:: 1995ን ጨርሰው ወደ 1996 ገቡ:: መልካም አዲስ ዓመት ብያለሁ:: እኔ ግን ይህን ቀን የማስታውሰው የአእምሮ ሕክምና (psychiatry ) ትምህርት የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን በመሆኑ ብቻ ነው:: ያ የለፈው የታህሳስ መጀመሪያ የፈተና ሰሞን አለፈ:: እኔም ፈተናዬን ተፈተንኩ:: ነገር ግን ለትውስታ የሚሆን አንድም ነጥብ ሳላሰፍር እንደተፈተንኩ ላጭር ረፍት ወደ አዲስ አበባ ሂጄ ነበር:: ባለፈው ሰኞ ወደ ጅማ ተመለስኩ:: የአእምሮ ሕክምና ትምህርትም በበነጋው ተጀመረ:: በቅጡ ማንበብ ባልጀምርም ትምህርቱን ወድጀዋለሁ:: ከሕክምና ትምህርቶች ሁሉ አንደኛ የምወደው እሱ ነው ብዬ ደፍሬ መናገር ባልችልም በትምህርቱ ክፍለግዜ ስለሰዎች ባህሪ ፣ አንዲሁም ስለ psychoanalysis የምናደጋቸውን ውይይቶች በጣም ተመስጬባቸዋለሁ:: ምናልባት ቤተሰብ ጋ እረፍት አድርጌ ገና መምጣቴ ስለሆነና ያዕምሮዬም ጤና ጥሩ ስለሆነ ጥሩ ተሰምቶኝ ይሆናል እንዲህ ያልኩት::
የካቲት 17 1988 አ.ም. እሁድ
የአራተኛ አመት የህክምና ተማሪ የሆነው ክንፈ ዛሬ ሞተ:: ራሱን በስቅላት አጠፋ:: በማደሪያ ክፍሉ ባለ ሎከር ውስጥ በኤሌትሪክ ገመድ ተሰቅሎ ተገኘ:: ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም:: እጅግ ጥልቅ የሆነ ሃዘን እየተሰማኝ ነው:: የመሞቱን ወሬ ከሰማሁ በሁዋላ ጉዋደኞቼን አግኝቼ አስከማረጋግጥ አላመንኩም ነበር:: እንደኔና እንደአብዛኞቹ ተማሪዎች ከድሀ ቤተሰብ የተወለደና የወደፊት ሂወቱን ብሩህ ለማድረግ የሚፍጨረጨር ምስኪን ዜጋ ነበር:: ራሱን አጠፋ? ለምን? ኦ አንተ አግዚአብሔር ወጀቡን አረጋጋው: ቀሪዎቻችንን እንዲህ አናደርግ ዘንድ ጠብቀን! አሜን!
የለም! ገና አልጨረስኩም:: በዚህ ጉዳይ የምለው ተጨማሪ ነገር አለ:: ስለክንፈ ሳይሆን ስለራሴ:: እንዲዚህ አይነትና መሰል ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ሲከሰቱ ስለክስተቱ ብቻ ሳይሆን ስለራሴም በጥልቅ አስባለሁ:: አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው:: እኔም ሆንኩ የክንፈን ሞት የሰሙ የጤና ሳይንሱ ተማሪዎች በሙሉ ያልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ነን:: አንዳንዶቹ የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ
ተኝተዋል:: እንደክንፈ አይነት አሟሟት እንደማልሞት አርግጠኛ መሆን አሰኘኝ :: ሁልግዜ ችግር እንዳለብኝ እያሰብኩ በኑሮም እነጫነጫለሁ:: አሁን ግን ሳስበው ያ ሁሉ እውነት አይደለም:: ሌሎች መፍትሄ የሌለው ከባድ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው::
ዛሬ እጀግ ብራ የሆነና ነፋሻ ያማረ መልካም እሁድ ቀን ሆኖ ነው የዋለው:: ክንፈም በመፅሃፍት ቤቱ ውስጥ በትጋት ሲያጠና ነበር- እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ:: ከዚያ ቀጥሎ ወደ ማደሪያ ክፍሉ በመሄድ ራሱን አጠፋ! ብዙ ግዜ ለብቻው የሚራመድ : ብዙ የማይናገርና ብዙም ለትምህርቱ ደንታ የሌለው የሚመስል ልጅ ነበር:: ተማሪ ራሱን ሲያጠፋ በ ጤና ሳይንሱ ታሪክ ክንፈ የመጀመ ሪያው ነው::
ፍርሃት ፍርሃት አለኝ:: ምንን እንደምፈራ ግን አላውቅም:: መንግስቱ ክንፈን ይቀርበው ነበር:: አሁን መንግስቱ የት ነው ያለው? ሬሳውን አጅቦ ወደ ክንፈ አገር እንድብር ሄዷል መሰለኝ::
እዚግህ ላይ ይብቃኝ መሰለኝ መፃፉ:: 10 ሚሊግራም ዲያዜፓም ያስፈልገኛል:: አለዚያ እንቅልፍ ላይወስደኝ ይችላል:: ወይስ አልውሰድ? ትንሽ ልጠብቅ እስቲ ........
ማስታወሻ: በዚህ ቀን ፅሁፌን ከጨረስኩ በሁዋላ በድንገት ሳላውቀው እንቅልፍ ወሰደኝ:: ያዘጋጀሁትን ዲያዜፓም ታብሌት አልወሰድኩትም