ታህሳስ 28 1984 አ.ም. የገና
ዕለት (Long day in Jimma)
ለኔና ለነ መንጌ መታወስ ያለበት
ቀን ይህ ይመስለኛል:: የልጅነት ትዝታ.......
የገና ለት ጠዋት ስድስታችንም ማለትም
እኔ : መንጌ: አምሳሉ: ሚሊዮን: አብይና ማስረሻ በአሉን ምክንያት በማድረግ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በመሄድ ተሳልመን ወደ
ጤና ሳይንሱ ግቢ ተመለስን:: ከዚያም ከቁርስ በሁዋላ ጠዋቱን በጅጤሳ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በተማሪዎች ተዘጋጅቶ በነበረው የፀሎትና
መንፈሳዊ ትምህርት ፕሮግራም ላይ ተገኘን: ከአብይ በተቀር:: አዳራሹ በእጣንና ዑድ ጭስና መአዛ ታውዶ ነበር:: ረዣዥም ሳር ፈንጠር ፈንጠር ብሎ
በሰፊው አዳራሽ ውስጥ ተጎዝጉዙዋል:: በአዳራሹ አንድ ወገን እንደ መድረክ አይነት የተዘጋጀ ቦታ ይታያል:: መሃል ላይ የየሱስ
ክርስቶስ ስዕል የታያል በግራና በቅኝ የሚበሩ ሻማዎች የተሸከሙ ቀንዲሎች አሉ:: ከመድረኩ ፊትለፊት ጀምሮ እስከአዳራሹ መሃል ድረስ ያሉት መቀመጫ ወንበሮች በተማሪ ና በመምህራን ታዳሚዎች ሞልተዋል:: ነጠላ የለበሱ ተማሪዎች አንገታቸውን ደፍተውና ድምፃቸውን ዝቅ
አርገው ከወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ታዳሚውን ያስተናግዳሉ.......
ስድስታችን ከሰዓት በሁዋላ ተበታትነን
የዋልን ሲሆን እኔና አምሳሉ አንድ ላይ ነበርን:: ከተማ መሃል የምትኖር አንዲት የአምሳሉ ዘመድ የሆነች መምህርት ቤት ሂደን ጠላ
እየጠጣን ስንጫወት ቆየን::
ምሽቱን ሁላችንም ወደጤና ሳይንሱ
ግቢ ተመልሰን ተገናኘን:: ለቀናት ተቁዋርጦ የነበረው መብራት ስለተመለሰ ደስ ብሎን ነበር:: በዚህም የተነሳ ምሽቱን የዳንስ ምሽት
ለማድረግ በመስማማት አባይን ጨምረንና ሰባት ሆነን ፊልተር ለመጠጣት ዘውትር በንዲህ አይነት ወቅት ጎራ ወደምንልበት ግሪን ሆቴል
አመራን:: ሰዓቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ይል ነበር:: ግሪን ሆቴል ወለሉ በሳር ጉዝጉዋዝ ተሸፍኖ አመትባል መሆኖኑን ይናገራል::
ደስ የሚል መንፈስ ነበረው:: በግሪን ሆቴል ቆይታችን አምስት ጠርሙስ ፊልተር ለሰባት ጠጣን:: ይህ ክፍፍል አናሳ ቢሆንም ሁላችንም
ከሰአቱን በየፊናችን ጠጥተን ስለነበር እኔና መንጌ ይበቃል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ነበር:: ስለዚህም ሌሎቹም ላይ ተፅዕኖ በማድረግ
ከዚያ በላይ እንዳንጠጣ ከለከልን:: ነገር ግን ከአባይ በስተቀር ሌሎቹ በኔና በመንጌ ሃሳብ አልተስማሙም:: የሆነ ሆኖ ግሪን ሆቴል ፊልተር አለቀ ተባለ:: ስለዚህም
ሁላችንም ቤቱን ለቀን ወጣን:: እኔ መንጌና አባይ ወደ ጤና ሳይንሱ ለመመለስ ስንሻ እነ አብይና አምሳሉ ደሞ ለጉዳይ የሆነ ሰው
ጋ እንሄዳለን በሚል ሰበብ ተለዩን:: እኔ ሁላችንም ተመልሰን ዶርማችን ገብተን እንድንጨፍር በመፈለጌና ያም ስላልተሳካ ክፉኛ ተበሳጭቼ ሞቅታዬም በርዶ ወደ ጅጤሳሳ ተመለስኩ::
መንጌና አባይም አብረውኝ የተመለሱ
ሲሆን ዋይት ሃውስ ጋ ስንደርስ ተለያየን:: እኔ ወዲያውኑ ተስፋሁነኝ የተባለ ጉዋደኛየን አገኘሁትና ሻይ ለመጠጣት ተያይዘን ወደ
ውጭ ወጣን:: ከተስፋሁነኝ ጋ ብዙ ተጫወትን:: ብስጭቴም ለቀቀኝ:: ሻይ ጠጥተን ስንመለስ ሰዓቱ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ሆኖ ነበር::
ምሽቱ መቼም በጠፍ ጨረቃ የታጀበና የማይበርድ ብሎም የምይሞቅ ደረቅ የታህሳስ ምሽት ነበር:: በዚያ ሰዓት ከነአብይ ና መንጌ ጋ
መንገድ ላይ ተገናንኘን:: እነአብይን ሳያቸው ንዴቴ አገረሸ:: አይኔን አጉረጠረጥኩ:: እነሱ ደሞ ነገር ለማለዘብ እኔን ዋይት
ሀውስ ፈልገው አጥተውኝ ከመንጌ ጋ ሆነው እንደገና እየፈለጉኝ ነበር:: ስላጡኝ ይበልጥ ተበሳጭተውብኛል ለካ...የነሱ ንዴት ከኔ
እንደሚበልጥ ስለተገነዝብኩ ለዘብ አልኩና እንደውም ላግባባቸው ሞከርኩ:: ነገር ግን በዚያው ቅፅበት በተመሳሳይ አርዕስት አብይና
መንጌ ለብቻቸው ባደረጉት ክርክር ኃይለኛ አለመግባባት ውስጥ ገቡ:: አብይ ክፉኛ አኮረፈ:: ስለዚህ ሁለቱን ማግባባት ላይ ያተኮረ
እንቅስቃሴ አደረኩ:: የመንጌና የአብይን ጭቅጭቅ ቆሞ ሲከታተል የነበረው አምሳሉ በበኩሉ ሁኔታውን እንዳለ ጥሎ ለመሄድ ወሰነ::
ከብዙ ንግግሮችና የቃላት ምልልሶች በሁዋላ እንደገና እሱንም አግባብቼ ሁላችንም ወደ ዶርም 006 ተመለስን::
ሀሳባችን ቅድም ተነጋግረን የነበረውን
ዶርም ውስጥ የመጨፈር ፕላን ለማሳካት ነበር:: ዶርም እንደደረስን አብይ ትናንትና አምጥቶት የነበረውን ቴፕ ሪኮርደር ከራሱ ሎከር
ውስጥ ላወጣው ቁልፉን ከመንጌ ተረከብኩ:: ቴፕ ሪኮርደሩ ሌላ ዶርም ውስጥ ስለነበር አውጥቼው እስከምመለስ አብይና ማስረሻ ከዶርም
006 ተሰውረዋል:: አሁን ተስፋ በጣም ስለቆረጥኩ እዚያ የነበሩትን በሙሉ “በሉ ደህና እደሩ: ማንኛችን ጥፋተኛ እንደሆንን እግዜር
ይወቀው: ሁላችንም ግን በሆዳችን ክፉ እንዳናስብ” ብዬ ተሰናብቼ ወጣሁ:: ትንሽ እንደሄድኩ አምሳሉ ከሁዋላዬ እየተከተለኝ መጥቶ
“እባክህ ሳምሶን በቃ ተመለስና ወጥተን ሻይ እንጠጣ” አለኝ:: እኔም እሺ በማለት ከአምሳሉ: ከመንጌ ና ከሚልዮን ጋ ከዋይት ሃውስ
ወዲያ በሚወሰደው መንገድ አርገን ወደ ጤና ሳይንሱ መውጫ በር አቅጣጫ ሄድን:: በመንገዳችን ላይ የተማሪዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ ስንደርስ ከአዳራሹ
ውስጥ ከፍተኛ የሙዚቃ ድምፅ ይሰማ ነበር:: “አሀ እዚህ ፓርቲ አለ ማለት ነው?” ብለን ወደ አዳራሹ በር ስንጠጋ አብይና ማስረሻን
አገኘናቸው:: በወቅቱ የተዘጋውን ረዥም የአዳራሽ በር ለማስከፈት ከሚጥሩ ሌሎች ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው ነበር:: አብይና ማስረሻን
ይዘን ሻይ ለመጠጣት በሚል ጅጤሳን ለቀን ወጣን:: እዚህ ጋ ቁጥራችን ልክ እንደጠዋቱ ስድስት ሆነ ማለት ነው:: ሁላችንም ሞቅታችን
በርዶ ስለነበር ከሻይ ይልቅ ወንድማማቾች ቡና ቤት ሂደን መጠጥ ለመጠጣት ተስማማን:: እዚያም ለስለስ ያለ ጠጅ ጠጣን:: ጥቂት
ዘና አልን ሁላችንም:: እኔ በበኩሌ ለስለስ ያለ ሞቅታ ተሰማኝ:: ያቺ ለስላሳ ሞቅታ ሳታልቅ ወደ ዶርማችን ተመለስን: ዶርም
006:: እንደደረስን ያን መከረኛ ቴፕ ሪኮርደር ከተቀመጠበት አውጥተን ዘፈን ከፈትን: ድምፁንም እስከ መጨረሻው ለቀቅነው:: ሁላችንም
እጆቻችንንና እግሮቻችንን ማወራጨት ጀመርን: ዳንስ ማለት ነው:: አንዳድንድ የተኙ ተማሪዎች ወደውና በግዳቸው ተነሱ:: ቆጥ ላይ
የወጡትም ወረዱ:: ሙዚቃ የሸተታቸው ከሌላ ዶርም መጡና ተቀላቀሉን:: ኩርፊያ ተረሳ:: የሚችለውም የማይችለውም ባለ በሌለ ኃይሉ
ይድንስ ገባ:........................all night
long....all night.....all night ...
ቀደም ብሎ ለነበረው አለመግባባት
ሁላችንም እርስ በርስ ተወነጃጅለናል: ጥፋተኛንውን ግን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው:: አብይ ከማስረሻ በስተቀር ሁላችንንም ይወነጅላል:
በተለይም መንጌን:: መንጌ ደሞ በመጀመሪያ አብይን ቀጥሎም እኔንና ሌሎቹን ይከሳል:: እኔ ደግሞ አራቱን ማለትም አብይን: ማስረሻን:
ሚልዮንና: አምሳሉን ቁዋጥሬባቸው ነበር:: እነሱ ደሞ አራቱም በኔ ተበሳጭተዋል::