Wednesday, June 18, 2014

ዛሬ ማስታወሻ አላዘጋጀሁም:: ይቅርታ:: እንደሚቀጥል ግን ቃል እየገባሁ የሚቀጥሉትን ሁለት ግጥሞች እጋብዛለሁ::

ይህ የሌላ ሰው ግጥም ነው አርስቱ የሃሳብ መርከብ ነው (የገጣሚውን ስም ረስቼዋለሁ የተፃፈው ግን በ ፩፱፰፪ አ.ም. ነው )

መቁዋጫ የሌለው 
የሂወት ፈተና 
ሕላዌው የማያልቅ 
ገቢረ ህሊና
ይጉዋዛል በፍጥነት 
ሞገዱን ቀጣጥሎ
ይህ የሃሳብ መርከብ 
መልህቁን መች ጥሎ

ይህ ደግሞ የኔ ግጥም ነው (2013)
ሮሮ ለ ምናብ
ዓለም ዓለም ዓለም  አንቺ የኔ ዓለም
የህሊናዬ ግብር
አንች ወሰነ ሰፊ ጥግ አልባ ጠፊ ጉም
ትየለሌ ባህር
ከጥዋት አንስቶ ውድቅት እስከሚሆን
ደግሞ እስከሚነጋ
በውስጥሽ ጎዳኖች ስጉዋዝ ስብከነከን
ለህወቴ ክፍተት
 ወጌሻ ፍለጋ
ማለቂያ በሌለው ድርስ ምልስ ጉዞ
አእምሮዬ ዛለ
ስጋው ሰውቴም ወደቀ ደንዝዞ
መቆም ስላልቻለ
በውነተኛው  ዓለም ባራዊው  ሂወት
የምሄድበትን
የኑሮ ሰንክሳር አቀበት ቁልቁለት
የአድሜ  ጅረቴን
ልይዘው ቸገረኝ ውሉ ተዘነጋኝ
ቀልቤ ተወናብዶ
አንቺ ውስጥ ቀረሁ ግና ምን ሊጠቅመኝ

አቅሌለ ተሰዶ 

Wednesday, June 4, 2014

ብላቴ 5

ለብላቴ ሰማይ የስራውን ይስጠው 

ሚያዚያ ፩ ፩፱፰፫ አ.ም.

ምናልባት የምተርፍና የማልሞት ከሆነ የዛሬዋን ቀን መቼም አልረሳትም:: የጠዋቱን ትምህርትና የሰልፍ ስነስርዓት በደንቡ መስረት ስናካሂድ ከሰዓት በሁዋላ ምን እንደሚፈጠር የጠረጠረ በጭራሽ አልነበረም:: ልክ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ለፎሌን በፊሽካ ስንጠራ በደከመና በዛለ ሰውነት ብዙም ደስ ባላለው መንፈስ ከየኬስፓናችን ወጣን:: የዛሬው ከሰዓት ትምህርት አይነት የኢላማ ተኩስ ልምምድ ነበር:: ስለዚህም አየርወለዶቹ ከዚህ በፊት ሂደን ወደማናውቅበት ልቅ ና ሜዳማ የሆነ ስፍራ ወሰዱን:: በዙሪያውም ሆነ በሜዳው ላይ ከአንዲት የዘበኛ ማደሪያ ከምትመስል ማማ በስትቀር ምንም አይነት ነገር የለም:: ለጥ ያለ ሜዳ......... ስንደርስ እኔና ጉዋደኞቼ ተልፈስፍሰን ነበር:: ፀሀዩዋ በጣም ከመፋጀቱዋ የተነሳ እዚህ አካባቢ ወደ ታች ወረድ ብላ የምትኖር ነው የሚመስለው::  

የሚገርመው ነገር ይህ ሁኔታ አፍታም ሳይቆይ ልክ የመጀመሪያዎቹ ኢላማ ተለማማጆች ስፍራቸውን እንደያዙ ከሁዋላችን በርቀት ከሚገኙት ተራሮች ላይ የተነሳ ኃይለኛ ንፋስ ሜዳው ላይ የነበረውን ዓቡዋራ እያነሳ ሁላችንንም አለበሰን:: ከዚህ በፊት ህወቴን ሙሉ እንዲህ አይነት ጠንካራ ነፋስ አጋጥሞኝ አያውቅም:: ንፋሱ ብዙም ሳይቆይ ቀጥ-ፀጥ አለ:: 

በዚያው ቅፅበት ተራሮቹ እጅግ በጣም በጠቆረ ዳመና ከዳር እስከ ዳር ተሸፈኑ:: ያልተጠበቀ ዝናም በፍጥነትና በብዛት ይወርድ ጀመር:: ከማደሪያችን አንድ ወይም ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከመሆናችንም ባሻገር ሜዳው ላይም ሆነ በሜዳውና በ ማደሪያችን መካከል ከዝናብ ለመጠለል የሚሆን ምንም አይነት ነገር አልነበረም:: ዝናቡ ደግሞ ብዙ ብቻ ሳይሆን በጣም ቀዝቃዛ ነው:: ዉሽንፍር ና ነፋስ የቀላቀለም ነው:: በስላች የሚወርደው ይህ ዝናብ እያንዳንዱ ጠብታ ትልልቅ ከመሆኑ የተነሳ ፌቴን ሲገርፈኝ እንደ ብዙ ጥፊዎች ነበር የሚሰማኝ::  

ተማሪዎች መሮጥና መራወጥ ጀመሩ:: እኔም እንደዛው ለመሮጥ ሞከርኩ የዝናቡና የንፋሱ ከብደት ይበልጥ የተሰማኝ አሁን ነው:: መሮጥ አልቻልኩም:: ብቻ በርምጃና በሩጫ መሃል ያለ እንቅስቃሴ ማድረጌን ቀጠልኩ .......ማዝገም የሚባለው ይሄ ሳይሆን አይቀርም:: የለበስኩት ቱታ ሰውነቴ ላይ ተጣበቀ:: እያዘገምኩ እያለ ከዝናቡ በሁዋላ እታመም ይሆን ብዬ አሰብኩ:::: ነገ በቃ የሆነ በሽታ ይይዘኛል:: ምንም ጥርጥር የለውም:: በጣም ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ካዘገምኩ በሁዋላ ዞር ብዬ ሳይ ከሜዳው መቶ ሜትር የሚሆን ብቻ ነው የራኩት:: እዛው ነኝ ብል ይሻላል:: በዚያ ላይ ደከመኝ ::በሚገርም ሁኔታ አንዲት ሁለት የሚሆኑ ቅርንጫፍ ያላት አጭር ዛፍ አየሁ ና እሱዋው ስር ሂጄ ተጠልልኩ:: አንድ ሌላ ተማሪም አብሮኝ ተጠለለ:: አላውቀውም....

ዋጋ የለውም ራቁቷን የሆነች ዛፍ ስር እጠለላለሁ ብዬ በማሰብ እንደውም ለዝናቡ ቆምኩለት:: ምኑ ሞኝ ነኝ:: ደግነቱ ሌላም ሞኝ አጠገቤ አለ:: ብቻዬን አይደለም የተሞኘሁት:: ከዝናቡ ተጨማሪ ከሁለቱ ቅርንጫፎች እየወረደ የሚመታኝ ወደል ጠብታ ከዝናብ ባሰ:: እንደገና ማዝገሜን ቀጠልኩ:: የሚገርመው ነገር በዚያ በዶፍ መሃል ውሃ ጠማኝ:: አይደረስ የለም ብዬ ብዬ ማደሪያ ኬስፓኔ ደረስኩ:: ምንም ሌላ ያደረኩት ነገር የለም:: አካሌ ላይ የተጣበቀውን ቱታ እንደምንም አወላልቄ ና ጥዬ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ ተከናንብኩ:: ከሞትኩም በዚያው ልሙት...እራቴንም አልበላም.....