Wednesday, October 29, 2014

አሁንም የቀጠለ

አሁንም የቀጠለ

ይህ እንግዲህ የህክምና ትምህርት ቤት ወግ ስለሆነ አንዳንድ አንባብያንን እንዳያሰለች ስጋት አለኝ:: ነገር ግን ምንም ማድረግ አልችልም::

ጥቅምት አስራ አንድ አስራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.
ባለፈው ተሳክቶልኝ ላይብረሪ ውስጥ ለሶስት ሰዓት ያለማቁዋረጥ ተቀመጥኩ:: እስከአሁን ድረስ እየገረመኝ ነው:: ለወትሮው *ጡ ላይ መርፌ እንደተሰካበት ሰው አሁን አሁን በእረፍት (break) ስም ስወጣና ሰገባ ነበር ሰዓቱ ያልቅ የነበረው:: ለሶስት ሰዓት ስቀመጥ ታዲያ ያነበብኩት ሳይኮሎጂ ነው:: ሳብጀክቱን አወደዋለሁ:: እሺ ብለው ከሚነበቡልኝ ትምህርቶች አንዱ ነው:: ሌላ እሺ ብሎ የሚነበብልኝ....ሌላ....ሌላ....የለም:: ሃይ ስኩል ከልቤ እመሰጥበት የነበረው ባዮሎጂ እንኩዋን እጅ እጅ ብሎኛል::በእርግጥ ሂሳብና ፊዚክስ ካልኩሌሽኖች መስራት አሁንም ድረስ አልሰለቸኝም:: ግን በቃ ገና ሚድ ሴሚስተር ፈተናችንን እንኩዋን ሳንወስድ ምነው ይህ አንደኛ ዓመት ወደዚያ አልቆ በተገላገልኩት እላለሁ.... ወደ እውነተኛው ሜዲስን ትምህርት እስከምንሸጋገር ቸኩያለሁ:: ከአንደኛው ሴሚስተር በሁዋላ ፍረሽማን እንጨት እንጨት ብሎኛል:: በነገራችን ላይ ሚድ ሴሚስተር ፈተና ልንወስድ የቀረን አንድ ሳምንት ቢሆን ነው::

ይልቅስ ዛሬ አንድ ደስ የሚል ደብዳቤ ከቤተሰብ ደረሰኝ:: ላኪው አባቴ ነው::ለ አንድ መቶ ስድስት ቀናት ታስሮ ከነበረበት ሆለታ ገነት የሚገኝ አስር ቤት መፈታቱን የሚገልፅ የብስራት ደብዳቤ ነው:: ቅኑና መምህሩ አባቴ ያለፈው መንግስት ባቋቋመው የሰራተኞች ፓርቲ ውስጥ ተሳትፎ ነበረህ በሚል በተመሳሳይና ተመሳሳይ ባልሆነ ምክንያት ከታሰሩ ከሌሎች እልፍ ጎልማሶች ጋ ያሳለፈውን የእስር ግዜ ጨረሰ:: በእውነቱ እኔ በጣም ደስ ያለኝ ከሁሉም በላይ ለእናቴ ነው:: ብቸኛ የገቢ ምንጭ የነበረ ባል በሌለበት በድንገት  የብዙ የቤተሰብ ኃላፊና አስተዳዳሪ መሆን ይከብዳል:: አባቴ ታስሮ ይህን ቀን ሳድግ አይስጠኝ የሚያስብሉ በርካታ በሀዘን የተሞሉ ረዥምና ደባሪ የችግር ቀናት ከእናቴ፣ ከወንሜና ከእህቶቼ ጋ አሳልፌ ነበር:: ክረምቱን ሙሉ ከቤት የተለየው አባቴ እስር ቤት እያለ ነው እኔ ወደዚህ የመጣሁት:: በአንድ በኩል በጮርቃው አስተሳሰቤ ወደዚህ መምጣቴን ወድጀዋለሁ። ይብላኝ ለወንድምና እህቶቼ እንጂ የቤቱን የለት ተለት ችግርና አበሳ ከመጋፈጥ ተገላግያለሁ:: ነገር ግን በየቀኑ በአይን የማይታይ አንዳች መግነጢሳዊ ገመድ ልቤን ወደቤቴ ክፉኛ ይስበው ነበር:: ይህ ቁልጭ ብሎ የታወቀኝ ዛሬ የአባቴን መፈታት ስሰማና ከላዬ ላይ አንዳች ነገር ዱብ ብሎ የወረደ ያህል የመንፈስ ቅለት ሲሰማኝ ነው.......እነሆ ለሌሎችም ሁሉ ቸር ያሰማልኝ

Thursday, October 23, 2014

ካለፈው የለጠቀ

ካለፈው የለጠቀ......


መምህራኖቻችንን እየጠላሁዋቸው በመሄድ ላይ እገኛለሁ:: ባለፈው የገለፅሁት አጠቃላይ የጤና ሳይንሱ ሁኔታ ያሳደረብኝ የተስፋ መገመስ: እሱንም ተከትሎ የመጣው ትምህርት መጥላቴ ሳያንስ የአስተማሪዎቻችን ለኛ ያለማሰብ በብርቱ እንድጠላቸው አደረገኝ:: ከልባቸው እኛን እውቀት ለመመገብ ሳይሆን የተሰጣቸውን ካሪኩለም በቀነ ገደቡ ለመጨረስ ይመስላል ከተወሰነው የሌክቸር ሰዓት በላይ ያለማቁዋረጥ ይናገራሉ:: በነገራችን ላይ ከደርግ መውደቅ ቀደም ብሎ በአንደኛው ሴሚስተር ሲያስተምሩን ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራውያን የነበሩ ሲሆን ግልፅ በሆነ ምክንያት ባሁኑ ግዜ የሉም:: እነሱ በልምድም ሆነ በእድሜ የጎለበቱ የነበሩ ሲሆን በዚህ ሴሚስተር የማያቸው ግን አንድ ፍሬ ና ልምድ የሌላቸው ናቸው:: አንዳንዶቹ በመሰረቱ ሌክቸር ሲሰጡ ድምፃቸው የማይወጣና የማይወርድ ምንም አይነት ዜማ ወይም ቅላፄ የሌለው ለዛ ቢስ ከመሆኑ የተነሳ ማሰልቸት ብቻ ሳይሆን እነሱን ተቀምጦ ማዳመጥ ያማል:: በዋናው ሰዓት ከተፈቀደው ገደብ አልፈው እያስተማሩ እንኩዋን ለማለት ያሰቡትን ብለው ስለማይጨርሱ ሜክ አፕ ክላስ ብለው ከሰዓት በሁዋላ እየጠሩ በንግግር ያጥለቀልቁናል:: በነሱ ቤት ማስተማራቸው ነው:: ድንቄም

ሌላው በጣም እየከነከነኝ ያለ ነገር ደግሞ ወደፊት ልንጀምረው ከስድስት ወር ያነሰ ግዜ ከቀረን የህክምና ሙያ ትምህርት ጋር ምንም አይነት ተዛማጅነት የሌላቸው ትምህርቶች እየተማርን መሆኑ ነው:: በተለይ አንድ ሶሺዮሎጂ የሚባል ትምህርት አለ:: ከትምህርቱ ማስጠላት የሚያስተምረን ብስል ቀይ ባለ ግዙፍ አፍንጫ ጮርቃ መምህር ሞዛዛነት! በቃ ጨጉዋራዬን ነው የሚልጠኝ:: ከብዙ ሌሎች ሰብአውያን ፊት ቁሞ ሌክቸር ለመናገር ይቅርና የግል ሃሳቡን ለሌላ ሰው ማካፈል መቻሉን እጠራጠራለሁ:: እንዴት ለመምህርነት ታጨ? ጥያቄው ለራሴ ና ለውስጤ ነው:: ባዮሎጂ መምህራችንም ቢሆን ከሶሺሎጂው ጥቂት ብቻ ነው የሚለየው:: ንግግሩ የማይጨበጥ ና በእንከን የተሞላ ነው:: እንግዲህ ከእንደዚህ አይነት አድካሚ ተናጋሪዎችና ንግግሮቻቸው በሁዋላ ወደ ቀዮ የሸክላ አዳራሽ ስሄድ ለሌላ አስከፊ ጅጤሳ ገፅታ እጋለጣለሁ..በዚህ ግዙፍ አዳራሽ ውስጥ ከአልጋዎችና ፊትለፊቶቻቸው እንደ ጅብራ ከተጋረጡት ቁም-ቁጭ ሳጥኖች በስተቀር ቁጭ ብሎ ለማንበበቢያ የሚሆን ወንበርና ጠረጴዛ የለም.....ላይብረሪ መሄድ ግድ ይላል....

Sunday, October 19, 2014

መስከረም ፪፪ ቀን ፩፱፰፬ አ.ም. ሐሙስ 

ዳግም ሲጀመር

እነሆ መስቀል አለፈ:: መቸም መስከረም ደስ የሚል ነገር አለው:: የአዲስ ዓመት መግቢያ: የአደይ አበባ ማበቢያ ና መፍኪያ ወር..... ለክርስትያኖች መስከረም አንድ ቀን በቅዱስ ዮሐንስ የተጀመረው ያመት በዓል ግርግር መስቀል ካለፈ በሁዋላ ጋብ ይላል:: ለብዙዎች መስከረም የተሃድሶና የተስፋ ወር ነው:: ለኛ ለ ጅጤሳ ተማሪዎች ግን የወደፊት ተስፋችንን ሰንቀን ትምህርታችንን በቅጡ እንዳንማር የሚያደርጉ ሁኔታዎችን በየጊዜው የምናይበት ሆነ የዘንድሮው መስከረም:: ባለፈው እንዳልኩት በጤና ሳይንሱ ውስጥ  ትምህርት ተብሎ አሁን እየተካሄደ ያለው ነገር የውሸት የውሸት መስሎ ነው የሚሰማኝ:: እንዲሁ ትምህርት እየተካሄደ እንዳለ ለማሳየት የሚደረግ ጥረት ይመስለኛል:: ለማን እንደሆን ማሳየት የተፈለገው አልገባኝም:: ለኛ ይሆን? በየቀኑ የማያቸውና የምሰማቸው ግዙፍ የሂደት ክፍተቶች አሉ:: በዚህ ሁኔታ ትምህርቴን መከታተልና ማጥናት አልቻልኩም:: ተስፋ ሊኖር ይገባል ለካ ለመንቀሳቀስ: ለመስራት: ለመቀጠል ወዘተ .......አንዳንዴ በአንክሮ አስብ: አስብና ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱ መማር ትርጉም አጥቶብኝ ተስፋ እቆርጣለሁ::

የጤና ሳይንሱ ዲፕሎማ ተማሪዎች በሙሉ አመፅ ላይ ናቸው:: ትምህርት በራሳቸው ጊዜ ካቆሙ ሰነበቱ:: በብላቴው ዘመቻ ምክንያት ትምህርት ለስድስት ወር ቢቁዋረጥም በስልጠናቸው ላይ ሌላ ስድስት ወር እንዲጨመር ሲል ጤና ሳይንሱ ያሳለፈውን ውሳኔ አልፈለጉትም:: እነሱ የሚፈልጉት በምንም ይሁን በምን የሚመረቁበት ጊዜ ከብላቴ ዘመቻ በፊት በታሰበው እንዲሆን ነው::

ባለፈው የህክምና ተማሪዎችን ያስተምሩ የነበሩ ኩባውያን በሙሉ የመንግስቱን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ከፍተኛ የሆነ የሁለተኛና የሶስተኛ ዓመት Basic Science መምህራን እጥረት አለ:: ከግብፅና ከህንድ መምህራን ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ እንዳለ ይሰማል: ግን ይህንን በቀላሉ ላምን አልቻልኩም: አዝናለሁ  ነባራዊ ሁኔታዎች ያስከተሉብኝ ተጠራጣሪነት ነው እንዲህ ያረገኝ:: የሁለተኛ ዓመት የህክምና ተማሪዎች ከነገ ጀምሮ ከፍል እንደማይገቡ ሰምቻለሁ:: ግቢው ውስጥ ያሉ አንዳንድ አበሻ ረዳት መምህራን እያስተማሩዋቸው ነበር:: ተማሪዎቹ ግን በዚያ መቀጠል አልፈለጉም:: 

ሌሎችም የተለያዩ ችግሮች አሉ.....እውን ጅጤሳ ከመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ ነው? የሚል ጥያቄ ባእምሮዬ ይመላለሳል:: አንዳንዴ በድንገት ጥቁር አንበሳ በሚማሩ የህክምና ተማሪዎች እቀናለሁ:: ደሞኮ እንደሰማሁት ከሆነ አዲስ አበባ ያሉ እንደነ ፕሮፌሰር አስራት ያሉ ሀኪሞች ጅጤሳን በእኩል ደረጃ አያዩትም:: መጀመሪያም ሲቁዋቁዋም ደስ አላላቸውም ነበር ይባላል:: ለኔ የሚሰማኝ ጅጤሳ በግድ ባንድ ሰው (በመንግስቱ) ፍላጎት የተመሰረተ የተማሪዎች ሞራል መግደያና ማሰቃያ ሆኖ ነው:: በዚያ ላይ ከተማው ዉሃ ያጥረዋል:: የሙቀቱስ ነገር!

ከስድስት ወራት በፊት ከዚህ ለተመረቁት ዶክተሮች ደስታ ሳይሆን ሃዘን ተሰማኝ በስቃይ ውስጥ እንዳለፉ በመገመት:: ለኔ ገና ለምጀምረው ደግሞ ፈራሁለት.....

Sunday, October 12, 2014

ዳግም ሲጀመር

ሰኞ መስከረም ፩፪ ቀን ፩፱፰፬ ..


ከደርግ ውድቀት በሁዋላ በተከተለው መስከረም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቁዋማት ሁሉ በራቸውን ለተማሪዎች ክፍት በማድረጋቸው ወደ ጅማ ጤና ሳይንስ አቀናሁ:: ትምህርትም ዛሬ ተጀመረ:: የሚሳዝነው ግን አሁንም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ መሆኔ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ባለፈው ዓመት ሪያዬ ከነበረው ቀይ የሸክላ አዳራሽ ውስጥ መገኘቴ ነው:: አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ነው:: ባለፉት ስድስት ወራት ዉስጥ የተከሰቱ የባህሪ ለውጦች ለውስጤ ይሰሙታል:: እንደበፊቱ ቀልድ የማላበዛ መስሎ ይሰማኛል:: ፊቴ ላይ እንደሚገለፅ እርግጠኛ ባልሆንም ውስጤ ግን ኮስታራነት ይሰማኛል:: ለሰላምታ ግድ የለሽ የሆንኩም ይመስለኛል:: በፊት ለመሰንዘር አመነታባቸው የነበሩ ቃላትን አሁን እንደዋዛ እናገራቸዋለሁ: ስለ ሌሎች ሰዎች ማሰብም ሆነ መጨነቅ አይዳዳኝም:: ከደብዳቤ አቅም እንኩዋን ጉዋደኞቼን ትቼ ለቤተሰቤ ብቻ ነው የፃፍኩት: ያውም በመከራ: አምና የነበረኝ የከረመ ፍቅርም እየወጣልኝ ነው መሰለኝ ልጅቱዋን አስቢያት አላውቅም: ቶሎ እበሳጭ የነበረውንም ትቻለሁ...ጉርምስናዬ ዘግይቶ መጥቶ ነው ማለት ነው??

ትምህርታችን ባለፈው ወደ ብላቴ የዘመትን ግዜ ካቆመበት እንደሚቀጥልና ወደሁዋላም ተሂዶ በሌክቸር የሚከለስ ነገር እንደሌለ ተነግሮናል:: ስለዚህ በንባብ ድጋፍ ተሃድሶ ማድረግ ይጠበቅብናል:: በመጪው ታህሳስ ወር የአንደኛ ዓመት ትምህርታችንን እናጠናቅቃለን ተብሎ ይጠበቃል:: 

ለምን እንደሆነ ባላውቅም ትምህርቱ ዳግም የሚቁዋረጥ መስሎ ይሰማዋል: ለውስጤ:: ያለፉት ስድስት ወራት ያሳዩኝ ከፍተኛና በቁጥር በርካታ የሆኑ የሀገር ውስጥ ለውጥ እንቅስቃሴዎች ያሳደሩብኝ ተፅዕኖ ይሆን? የቅርብ ጉዋደኞቼንም ሳያቸው ለትምህርቱ ግድ የለሽ የሆኑ ይመስላሉ:: በቃ በጤና ሳይንስ ግቢ ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴ የውሸት የውሸት ሆኖ ይሰማኛል….

ሐሙስ መስከረም ፩፭ ፩፱፰፫ ..
ከምሽቱ ፭ ሰዓት ከ ፪፭:: እንደሚመስለኝ አሁን ትምህርት የምር ተጀምሩዋል:: ብዙዎችን ከልባቸው ሲያነቡና መፅሐፍት ይዘው ሲንቀሳቅሱ ላይብረውንም ሲጠቀሙ  ማየት ጀመርኩ:: እንደአምናው ሌሎችን ሲያነቡ ሳይ መደናገጥ አሁን በጭራሽ አልዳሰሰኝም:: የማንበብ ፍላጎቴ እስከአሁን ብቅ አላለም:: ይገርማል:: ይበልጥ የገረመኝ ያሳሰበኝ ግን ይህ ሳይሆን ባለማንበቤ "ለምን አላነበብኩም?" ብዬ አለመጨነቄ ነው:: ቀለል አድርጌ ነው የያዝኩት:: በተለይ ላይብረሪ ውስጥ እስካሁን በተከታታይ ከአስራ አምስት ደቂቃ በላይ የቆየሁበት ጊዜ የለም:: በብዛት በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ እየተራመድኩ የተለያዩ ሃሳቦችን ባይምሮዬ ማሰላሰል ይቀናኛል እንዲሁም ይቀለኛል :: ሌክቸር ላይ ያለኝ የማዳመጥ ጉጉት ና አንክሮ ከቀድሞው በእጅጉ ቀንሱዋል:: ለዚህም ግድ የለኝም:: ክለሳን በሚመለከት ከስድስት ወራት በፊት በደብተሮቼ ላይ ያሰፈርኩዋቸውን የሌክቸር ማስታወሻዎች ስመለከት በተለይ ሂሳብና ኬሚስትሪ ከብደው የማይገፉ ሆነው የታዩኛል::

Wednesday, October 1, 2014

የብላቴ ማስታወሻ ማጠቃለያ

ዛሬ....
"የቤተሰብ ሃላፊነት ና የጎልማሳ ዳተኝነት ተባብረው ማስታወሻዬን እዚህ ብሎግ ላይ እንዳላሰፍር አርገውኝ ነው ሳልጽፍ የዘገየሁት!" በማለት የዛሬውን ጽሁፍ እጀምራለሁ።

ባለፈው የመስክ ላይ ፍንዳታ ና የአንድ አየር ወለድ ጉዳትን የሚያትት ጽሁፍ ካሰፈርኩ በኋላ በተከተሉት አራት የሚጠጉ ወራት ምንም አይነት ማስታወሻ አላሰፈርኩም። ለምን የሚለውን መመለስ አሁን ያዳግተኛል። በአራቱ ወራት ውስጥ በኔ የግል ሂወት ላይ እምብዛም የሆነ ለውጥ ባይከሰትም (ከጉርምስና መቀጠል በስተቀር) ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የለውጥ ኩነት ግን አብዛኛው የዚህ ጽሁፍ ታዳሚ ያስታውሰዋል የሚል ግምት አለኝ።

ግንቦት 1983 አ.ም. አጋማሽ ላይ ብላቴን ይጎበኛሉ እንዲሁም ስልጡን ተማሪዎችን ይመርቃሉ ተብለው የተጠበቁት ሊቀመንበር መንግስቱ ከኢትዮጵያ መኮብለላቸውን በሬዲዮ ሰማን። ያንን ሶስት ሰአት የፈጀ ንግግር ባደረጉ በወሩ እንደማለት ነው። የሳቸውን መኮብለል ተከትሎ ከጥቂት ቀናት በኋላ በተተረማመሰ ሁኔታ ና ከተወሰኑ በአውቶቡስና በአይሮፕላን ግቢውን ከለቀቁ ተማሪዎች በስተቀር ሌሎቻችን በእግር ብላቴን ለቀቅን። በግምት 60 ኪሎ ሜትር የሚሆን የገጠር ፒስታ መንገድ የምጻተ እስራኤል በሚምስል ረጅም ሰልፍ አቋርጠን ሞርቾ የምትባል ከተማ ብሎም ወደ ሰሜን 25 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው አዋሳ አመሻሽ ላይ ገባን። ለዚህ የፈጀብን 24 ሰአት ይሆናል- በእርግጥ ለሁለት ሰአት የሚሆን አንዲት ትንሽ ከተማ ላይ ተኝተናል። እኔና ጓደኞቼ አንድ ላይ ነበርን። መንጌ፣ ሚሊዮን፡ አባይ፡ አብይና ሚፍታህን አስታውሳለሁ።

ኢሃዲግ ግንቦት ሃያ አዲሳበባ ሲገባ እኛ አዋሳ ነበርን። አዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዶርሚቶሪዎቹን ከብላቴ ለሚመለሱ ተማሪዎች ክፍት አርጎ ነበር መሰለኝ.. እዚያ ነበር የምናድረው። በዚያን ግዜ አዋሳን ምናልባትም መላው ደቡብን ምንም የሚያስተዳር መንግስት አልነበረም። እስከማስታውሰው ድረስ ግን ከጥቃቅን የመንግስት ሱቅና መጋዘን ዘረፋ በስተቀር ብዙ ግርግር አዋሳ ውስጥ አልነበረም። እንደውም የተወሰኑ የአካባቢ ሽማግሎችና ፖሊሶች ተሰባስበው በመኪና እየዞሩ ህዝቡን ሲያረጋጉ ትዝ ይለኛል። እኛን ከብላቴ የመጣነውን ተማሪዎች በየቀበሌውው የሚገኙ፡ሴቶች በመተባበር ምግብ አዘጋጅተው እንደመገቡን አስታውሳለሁ። እግዚአብሄር ይስጣቸው። ከጓደኞቼ ጋ አንድ ሳምንት ገደማ አዋሳ ቆይተን በአንድ አውቶቡስ ተሳፍረን ወደ አዲስ አበባ ቼ አልን፡ ከሚልዮን በስተቀር። እርሱ ቀደም ብሎ አንድ ከአዋሳ ወደ ሞያሌ የሚንቀሳቀስ የጭነት መኪና ላይ ተንጠልጥሎ ሲሄድ ታይቷል። እኛ ወደ አዲስ አበባ ባቀናንበት እለት የወያኔ ወታደሮች በ ወታደራዊ የጭነት መኪኖች ታጭቀው ወደ አዋሳ አቅጣጫ ሲያመሩ ተመልክቻለሁ። እስከዚያ ቀን ድረስ አዋሳ አልነበሩም።

ሁላችንም በሰላም አዲስ አባባ ደርሰን ወደየቤታችን ገባን። በማግስቱ በቅሎ ቤት የሚገኘው መሳሪያ ግምጃ ቤት ፈነዳ። ከዚያም ብዙ ብዙ ሆነ..........

ምንም እንኳን እንዘምትበት ና እንወጋው ዘንድ ታስበን የነበረ መሆኑን ቢያውቅም ደጉ የኢሃዲግ መንግስት ብላቴ የዘመቱም ሆነ ያልዘመቱ ተማሪዎች ሁሉ ያቋረጡትን ትምህርት በመስከረም ወር 1984 አ.ም. እንደገና እንዲቀጥሉ በጎ ፈቃዱ መሆኑ ሳያንስ ከብላቴ ለተመለስነው በነፍስ ወከፍ 137 ብር እንደሰጠን አስታውሳለሁ...

በሚቀጥለው ማስታወሻዬ ጅማ ጤና ሳይንስ ተመልሰን ትምህርታችንን ከቀጠልንበት ከጸደዩ ከመስከረም ወር ጀምሮ የነበሩትን አንኳር አንኳር ክስተተቶች አሰፍራላሁ።፡ለዛሬው ደህና እንሰንብት.....