ሚያዚያ 10 ቀን 1984 አ.ም.
ጅማ
PC-1 እየተባለ የሚጠራውን የሁለተኛ ዓመት
ሕክምና ትምህርቴን ለመከታተል ጅጤሳ ከተመለስኩ ሁለት ሳምንት ሆነኝ:: የቅርቤ ከሆኑት ጉዋደኞቼ ጋር በዋይትሃውስ ዶርም ቁጥር
207 ውስጥ ከትሜያለሁ:: በርካታ የባቼ ልጆች ከእረፍት መልስ የወፈሩና ያማረባቸው ሲሆን እኔና ጥቂት ሌሎች ልጆች አላማረብንም
ባይባልም የሰውነታችን ሁኔታ ለውጥ ሳያሳይ ነው የተመለስነው::
የፒሲዋን ትምህርቶች ለህክምና መሰረታዊ
የሆኑትን ሳይንሶች Anatomy: Physiology: Biochemistry: Histology ና Embryology ያካተቱ ናቸው::
የአጠቃላይ ዲፓርትመንቱ ኃላፊነት የተሰጠው ሰው አቶ ኢሳያስ ይባላል:: አቶ ኢሳያስ ከቢሮ ኃላፊነቱ በተጨማሪ የBiochemistry
እውቀት የታጠቀ እንደሆነና እንደሚያስተምረን በመጀመሪያው ቀን orientation ስብሰባችን ላይ ነግሮናል:: የፒሲዋን ትምህርቶችን
መጪውን ዓመት ሙሉ ተቀምጠን የምናዳምጥበትና የምንቀስምበት ክፍል ውስጥ ወስዶ በመንፅሩ የበታች ዳርቻ አሻግሮ እየተመለከተን ረዥም
ዲስኩር አደረገ:: ወፈር ያለ ሰውነቱና ጠቆር ያለ ገፅታው በመጀመሪያ ሳየው የሌላ አፍሪካ አገር ዜጋ እንዲመሰለኝ አርድርጎኝ
ነበር::
አቶ ኢሳያስ በኦርየንቴሽኑ ወቅት ከተናገራቸው
በርካታ ማስፈራሪያ መሰል አረፍተ ነገሮች መካከል አንድ በጣም የወደድኩለት አባባል አለ:: “በምንም ተአምር ከምሽቱ ስድስት በሁዋላ እንዳታነቡ:
ዋጋ የለውም!” እኔ ታዲያ በሆዴ አርጎት ነው!? አልኩ ይህን ስሰማ:: ሌላው ደስ ያለኝ ነገር የፒሲዋን ትምህርቶችን
የሚያስተምሩን እንደፊቱ ኩባውያን ሳይሆኑ ግብፃውያን እንደሚሆኑ መስማቴ ነው:: ከኛ የቀደሙት በኩባውያን የተስተማሩ ባቾች እንደነገሩን
ከሆነ ከኩባውያን እንግሊዝኛ አለመቻል ጋ የተያያዘ ብዙ የመማር ማስተማር ሂደት ችግር ነበር:: ስለዚህም ተማሪዎቹ ለእውቀታቸው
መዳበር ላይብረሪ ሂዶ መፅሐፍ ማንበብን እንደዋነኛ ምንጭ አድርገው መትጋትና መፍጋት ነበረባቸው:: እኔ ታዲያ በከዚህ በፊት ታሪኬ
እንደገለፅኩት ቤተ መፅሐፍት ተቀምጦ ማንበብ ላይ ያለኝ ስር የሰደደ አሉታዊ አመለካከት በኩባውያን መምህራን ስር ብሆን ችግር መፍጠር
ብቻ ሳይሆን ስጋት ውስጥ ይጥለኝ እንደነበር ግልፅ ነው:: ስለዚህም ግብፆቹ በእንግሊዝኛ ቁዋንቁዋ እንደሚያስተምሩን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ
ባልሆንም የኩባዎቹ ካካባቢው መጥፋት ግን የአእምሮ ረፍት ሰጥቶኛል:: መቼም ግብፃውያኑ በአረብኛ እናስተምራችሁ እንደማይሉ
ተስፋ አደርጋለሁ::