ጥር 23 ቀን 1984
አ.ም
አዲስ አበባ ቀራንዮ
የጥምቀት በዓል ባለፈው ሰሞን ተከበረ:: ይህ በዓል ሲከበር እዚህ ያደኩበት ሰፈር በመሆኔ በእውነት ደስ ብሎኛል:: የጥምቀት በዓል ልጅነቴን ጉልህ
አድርገው ከሚያስታውሱኝ ትዝታዎች አንዱ
ነው:: በልጅነቴ በየዓመቱ ጥምቀት ሲመጣ ጥምቀተ ባህር እየተባለ ወደሚጠራ ስፍራ ከሰፈር ጉዋደኞቼ ጋ እንሄዳለን:: እዚያም ከዋዜማው
እለት ጀምሮ ስንሮጥ: ስንላፋ እንዲሁም ለጥምቀት ብለን ባጠራቀምነው ሳንቲም ብርቱካን: በረዶ: ሸኮራ አገዳ: ብስኩት ወዘተ...እየገዛን ስንበላ ውለን እናመሻለን:: ጧፍ እናበራለን:: እንደሌላው ጊዜ ሳይሆን ለጥምቀት እለት እስከ እኩለሌሊት እንድናመሽ በወላጆቻችን ይፈቀድልናል::
መቼም የልጅነት ጉልበት ያማይልቅበት ነውና ጥምቀተ ባህር ውስጥ በአዋቂዎች እግር ስር ስንሹሎኮሎክና ካንዱ ጫፍ ወደ አንዱ ጫፍ ስንሮጥ አይደክመንም ነበር:: አንዳንድ ጉዋደኞቼ በእርግጥ የሚሮጡት ከሌላ ደከም ካለ/ች ልጅ ላይ ብርቱካን ወይም ማስቲካ ወይም
ሌላ የሚበላ ነገር መንትፈው ነበር::የቀራንዮ መድኃኔዓለም ታቦት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ለጥምቀት
ዋዜማ ለት ሲገባና በማግስቱም ከጥምቀተ ባህሩ ወደ ቤተክርስትያኑ ሲመለስ በሚጉዋዝበት ባቡር መንገድ ላይ የነበረው ትእይንት ፈፅሞ
አይረሳኝም:: ባንድ ወገን የቤተክርስትያን ዘማሪዎች በቀለማት የደመቀ አንድ አይነት ልብስ ለብሰው እስከቻሉት ድረስ በመጮህ ና ከበሮ በመደለቅ ሲዘምሩ ና አንዳንዶቹም ሲዘሉ: እልፍ ብሎ ደግሞ የብሄረሰብ ባህላዊ ጭፈራዎች የሚታዩበት ስብስብ (በተለይ ዶርዜኛ ና ኦሮምኛ): ከዚያ ደግሞ ዘመናዊ ሙዚቃ በ ሃርሞኒካ የሚዘፈንበትና ወጣቶች የጊዜውን ዳንስ የሚደንሱበት ግሩፕ የሚፈጥሩት የመንገድ ላይ ግርግር እስከዛሬ ባይነ ህሊናዬ አለ:: ዘንድሮ ይሄው አድጌ በወጣት የኮሌጅ ተማሪ ደንብ ደርበብ ብዬ ጥምቀትን ከዳር ቆሜ እንደ ትርኢት አየሁት:: የሀይ ስኩል ጉዋደኛዬና ጎንደር
ሕክምና ትምህርት ቤት የተመደበው ከፈለኝ አብሮኝ ነበረ:: ያኔ እኔ ራሴ ተዋናይ የነበርኩበትን የጥምቀት በዓል ተውኔት እንደ ታዳሚ
ተመለከትኩት:: የጥምቀት በዓል ደስ ይላል....
ወደዛሬ ልመለስ:: ዕረፍቴ ረዥም ስለሆነ አንዳንዴ መታከት ብቻ ሳይሆን የምሰራው ግራ ግብት ይለኛል:: ልቦለዶች በተከታታይ እያነበብኩ ነው:: አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የትርጉም መፅሀፍት በብዛት እየተፃፉ ነው:: ልክ አሁን “Madam
X” ወይም “ስም የለሽ” የተሰኘ ትርጉም ልቦለድ አንብቤ ጨረስኩ::
ትናንትና አርብ ለት ፒያሳ ከሚገኘው British Council ቤተ መፅሃፍት ሂጄ ነበር:: እንደ ጊዜ ማሳለፌያ ነበር የሄድኩት:: አሀ! አዎ ስለ Bronchitis
ለማንበብም ፈልጌ ነበር:: አንዲት በቅርብ የማውቃት የናቴ ጉዋደኛ የሆነች ሴት በቅርቡ ሀኪም ቤት ሄዳ ሀኪም “Bronchitis”
አለብሽ አላት:: በጣም ያስላታል:: አክታም በብዛት ትተፋለች:: ከዚህ በመነሳት ለምን ስለዚህች ሴት በሽታ አላነብም የሚል ሃሳብ መጣልኝ:: ስለዚህም British
Council ተገኘሁ::
ቤተ መፅሃፍቱ ውስጥ Medicine የሚል ሼልፍ አለ:: እዚያ ሄድኩና የተደረደሩትን መፅሃፍት ሁሉ ቃኘሁዋቸው::
“Pharmacology: Pediatrics: Surgery: Nursing ወዘተ... ለተወሰኑ ደቂቃዎች ካማተርኩ በሁዋላ “Disorders
of the Chest” የሚል መፅሐፍ አይቼ አነሳሁት:: አነበብኩ ስለ “Acute
Bronchitis” ና “Chronic Bronchitis” .... “disease
of the alveoli” ይላል::በተወሰነ መልኩ ማንበቤ ደስ ቢለኝም አሁን ይሕን ማንበቤ ምንም ትርጉም እንደሌለው ሆኖ ተሰማኝ:: ገና ፍሬሽ ማን መጨረሴ ነው:: እንደዚህ አይነቶቹም መፅሃፍት አንብቦ ና ተረድቶ ለመጠቀም ቢያንስ አራተኛ ዓመት ተማሪ መሆን ያለብኝ ይመስለኛል:: አራተኛ ዓመት ከመደረሱ በፊት ደግሞ ከፊቴ የተደቀኑ ሁለት እንደተራራ የገዘፉ አመቶች አሉ:: በጅጤሳ Preclinical Years ይባላሉ:: የነዚያ ሰው ይበልኝ.....
No comments:
Post a Comment