ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 1984 አ.ም. ከሰአት 11 ሰኣት ከ 52 ደቂቃ
የእፅዋትን ልምላሜ: የጨረቃን ድምቀትና የጸሃይን ጥልቀት አንጸባራቂ ብርሃን በሂወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ማድነቅ የቻልኩት ጅማ ከመጣሁ ወዲህ ነው:: ጅማ ከአመት አስከ አመት ኣረንጓዴ ነው.....ትናንትና ሰኔ ግም አለ! ሰማዩም ላይ ጥቁር ደመናዎች ይታዩ ጀመር:: በጅማ ይህም ያምራል...... ብቻ በክረምቱ መግባት የሚያስፈሩኝ ሁለት ነገሮች አሉ:: ጭቃና የመብራት መቋረጥ::በዛሬአው ቀን አናቶሚ የጽሁፍ ሀተታ ፈተና ወሰድን:: ስለፈተናው ከባድ ይሁን ቀላል ለመናገር ይከብደኛል:: ውጤቱ ሲመጣ ማየት ይሻለኛል....
ሰኔ ዘጠኝ ቀን 1984 አ.ም.
ባለፈው ከባድ የዝርፊያ አደጋ ተፈጸመብኝ:: አጥቤ ያሰጣሁት ሁለት ሱሪ ፥ ሁለት ሹራብ፥ አንድ ጃኬት፥ ሶስት ካኒቴራ፥ አንድ ቲሸርት፥ አንድ ፎጣና ሁለት የትራስ ልብስ ተሰረቀብኝ:: ደርቋል ብዬ ልሰበስብ ስሄድ ደርቄ ቀረሁ:: የልብስ መስቀያው ገመድ ባዶውን በንፋስ ይወዛወዛል:: ይህን አደጋ ተከትሎ በርካታ የማጽናኛ ቃላት ከጓደኞቼና መኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ የጎረፉ ሲሆን ወዲያውኑም የልብስ ልገሳና ውሰት ሀሳቦች ቀርበውልኛል:: ከሁሉም ደስ የሚለው ነገር ግን የተሰረቀው ልብስ ብዙ ስለነበር ለማዘን አለመመቸቱ ነው:: በዚያ ፈንታ ወዲያው ረሳሁት:: ለነገሩ የፒሲዋን ትምህርትም ለሃዘን ጊዜ የሚሰጥ አይደለምና ኑሮዬን አንደቀድሞው ቀጠልኩ......
ስኔ 11 ቀን 1984 አ.ም. ከምሽቱ ስድስት ሰአት- ስለ ማሂ
ዛሬ ቀን በፊዚዮሎጂ ከፍለጊዜ Cardiovascular System ተጀመረ::ፕሮፌሰር ማሂ አየፈጠነ በመናገሩ በቅጡ የገባኝ ነገር አልነበረም:: ይህን መምህር በዚህ በመፍጠኑ የተነሳ አየጠላሁት ነው:: ለነገሩ ሲያስረዳ ከመፍጠኑም ባሻገር ለኛ ለኢትዮጵያውያን ንቀት ያለው መስሎ ስለሚሰማኝ ቀልቤ አይወደውም:: በእውቀቱ እጅግ ይመካል:: አንዳንዴ ያለምንም ምክንያት የሚሰጠንን ሌክቸር ምስቅልቅሉን ያወጣውና ግራ ያጋባናል:: ያደናብረናል:: እንደሌሎቹ ግብፃውያን መምህራን የተወሰነ ሪፈረንስ መጽሃፍ አይከተልም:: ከትምህርት ውጭ በሆነ ነገር እንኩዋን ከተናደደ ቁጭቱን ሌክቸሩን በማበላሸትና አኛን ግራ በማጋባት ይወጣል:: ብዙ ጊዜ ትልልቅ አንቱ የተሰኙ መፅሀፎችን በስም እየጠራ ይተቻል፥፥ ያንቋሽሻል፥፤ በጣም ሲበዛ ጉረኛ ነው....ማሂ
No comments:
Post a Comment