መስከረም 2 ቀን 1986 አ.ም.
የልደታ ትዝታ
ትናንት እንቁጣጣሽ ዋለ:: አዲስ ዓመት ገባ:: በዚሁ ቀን ምሽት ላይ
ከአብሮአደግ ወዳጆቼ ሳሚ: ዳዊትና ተሾመ ጋ ልደታና አካባቢዋ በመዘዋወር ከቡና ቤት ቡናቤት እየለዋወጥን በመጠጥና በዳንኪራ
ራሳችንን ስናዝናና አመሸን:: ይገርማል እንደቀልድ ቡና ቤት ገብቶ መጠጥ መጠጣት ጀመርኩ:: እድሜዬ አሁን 21 ዓመት ነው:: ጅማ
በተደጋጋሚ ያደረግሁት ቢሆንም አዲስአበባ ግን የመጀመሪያዬ መሆኑ ነው:: በጣም ደስ ና ደስ ብሎኝ ነው ያመሸሁት:: ከነሳሚ
ጋር በገባንባቸው ቡና ቤቶች ሁሉ የሚያጋጥሙን አዲሳቤ ጠጪዎች ወጣትም ይሁን ሽማግሌ: ሴትም ሆነች ወንድ: ሁሉም እንደኛው
በሞቅታ ንፍቀ ክበብ ውስጥ የነበሩና ቡናቤቶቹ ማዕዘኞች ላይ ከተሰቀሉት ድምፅ አጉሊ ስፒከሮች ከሚሰሙት ማናቸውም አይነት
ዘፈኖች ጋር የሚወራጩ ነበሩ:: አሁን ሳስበው እኔ ራሴ ሞቅ ብሎኝ ስለነበር ነው እንጂ እየተወራጩ ሳይሆን እየደነሱ ነበር::
ቡናቤቶቹ በሰው ከመሞላታቸው የተነሳ ለመደነስ የሚሆን ቦታ ባለመኖሩ ሁሉም ሰው እዛው በቆመበት ነው ይወራጭ የነበረው:: ወደየትኛውም አቅጣጫ መንቀሳቀስ የሰው እቅፍ ውስጥ ከመዳረግ
ባሻገር ያልተጠበቀ ሰላምታና መጠጥ ባሰረው ምላስ "እንኩ..ዋ..ዋ....ን አ...ደደ...ረ..ሰህ/ሽ" መባባልን ያስከትል ነበር:: ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲሆን
ሁላችንም ወደነ ሳሚ ቤት በመሄድ አንድ ለሁለት ሰው እንደምንም የምትበቃ አልጋ ላይ ተጣበን አደርን::
እኔ በጣም በጠዋት በመነሳትና ወደ ቤቴ በመሄድ ራሴ አልጋ ላይ መተኛቴን ቀጥዬ የነበረብኝን የወገብ ህምም አስታግሼ ና አረፋፍጄ ተነሳሁ:: አሁን ከጠዋቱ
አምስት ሰዓት ተኩል ገደማ ይሆናል.....የልደታ ትዝታ..
ጥቅምት 27 ቀን 1986 አ.ም.
ወሳኝ ወቅት
ከአዲሳበባ እረፍት ከተመለስኩ በሁዋላ አንኩዋር የሆነ አጋጣሚ ባይገጥመኝም: የሶስተኛ
አመት የምህርት ሂደትና የኔ ሁኔታ በየቀኑ ባይምሮዬ ይመላለስ ነበር:: ሶስተኛ ዓመት ከገባሁ በሁዋላ በራሴ ላይ ያየሁት
ተጨባጭ ነገር ለትምህርት ያለኝ ፍላጎት ክፉኛ ማነሱና ይህም በአንዳንድ የፈተና ውጤቶቼ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው:: ከዚህ
በፊት በትምህርት ሂወቴ አይቻቸው የማላውቅ የፈተና ውጤቶች ማግኘት ጀመርኩ:: ይህ ሁኔታ አስደንግጦኝ በርትቶ ለማጥናት በመነሳሳት
ፈንታ እኔ ግን የበለጠ የትምህርት ፍላጎቴ ቀነሰ:: ያለፉት ቀናት ጅማ ከገባሁ በሁዋላ ለመጀመርያ ጊዜ በገዘፈ ሃሳብ አእሞሮዬ
የተፈተነባቸው ቀናት ነበሩ:: ምክንያቱም ትምህርቴን አቁዋርጬ ረዘም
ያለ እረፍት ለማድረግ ጊዜያዊ መልቀቂያ (ዊዝድሮዋል) ለመጠየቅ አስቤ ነበር:: ነገር ግን ይህ በቀላሉ ይሁን ብዬ የማደርገው
ነገር አልነበረም:: አእምሮዬ ጉዳዩን ለመፈፀም ቢገፋፋኝም ከፊቴ የተጋረጡ በቂ መልስ የሚሹ ሞራላዊ የህሊና ጥያቄዎች ነበሩ::
ብዙ ነገሮችና ትዝታዎች ወደአእምሮዬ ተመላልሰው ነበር: ባለፉት ቀናት:: ገና የጅጤሳን ግቢ የረገጥኩ ሰሞን በአውቶቡስ ታጭቀው
ወደ ጦር ካምፕ ለስልጠና የሄዱት ጮርቃ ነፍሶች ታውሱኝ:: ከዚያም በድንገት እረፍት ለማድረግ በማሰብ ወደ ጅማ አውቶቡስ
ተራ የሄድኩ ጊዜ የተመለከትኩት ትዕይንት ታወሰኝ:: ሌሎች ብዙ ሰዎችና ሁኔታዎች ታወሱኝ......እኔ ከነዚህ ሁሉ
እሻላለሁ....አልኩ:: ዞሮ ዞሮ ግን ጭንቅላቴ በሀሳብ ውዝግብ ከሚፈነዳ በሚል ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን ዊዝድሮዋል
ለማውጣት ማስረጃ ፍለጋ ከዚህ በፊት ሌሎች ተማሪዎች እንዳደረጉት ዶክተር ይልማ ጋ ሄድኩ:: ይህ ሰው ሳይካትሪስት ወይም የስነ
አእምሮ ዶክተር ነው:: ዊዝድሮዋል ለመጠይቅ የተገደድኩበትን ምክንያት ከላይ እንዳስቀመጥኩት
ስነግረው ፈፅሞ ሊዋጥለት አልቻለም:: እኔን በማዳመጥ ብዙ ግዜም
መውሰድ አልፈለገም:: በቀጥታ መድረኩን እሱ ተቆጣጥሮት የተለያዩ ምክሮች ከመከረኝ በሁዋላ ትምህርቴን እንድቀጥል በጥብቅ
አስጠንቅቆ ሸኘኝ:: የምክሩ ጭብጥ እንደሚከተለው ነበር
" ሰው ሁልግዜ እንደነበረ አይሆንም:: የሂወትን እውነታዎች መቀበል
አለብን:: በአንድ ወቅት ከብር የነበራቸው: ሁኔታዎች ሁሉ ተስተካክለውላቸው ይኖሩ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች በሌላ ግዜ ክብራቸው
ተገፎ: ሁኔታዎች አልሳካ ብለዋቸው የሚወድቁበት ግዜ አለ:: አንድ ሰው ውድቀቱንም በፀጋ መቀበል አለበት:: ውድቀት የማይከሰት
ነገር አድርጎ መቁጠር የለበትም:: መጥፎ ግዜ በመጣ ቁጥር ከችግር ለመሸሽ የማይሆን ነገር መስራት የለበትም:: ችግርን መጋፈጥ
አለበት......"
ምክሩ እውነት ሆነም አልሆነም በዚህ አይነት ትምህርቴ ቀጠለ ማለት
ነው.........