Sunday, April 3, 2016

መስከረም 2 ቀን 1986 አ.ም.

የልደታ ትዝታ

ትናንት እንቁጣጣሽ ዋለ:: አዲስ ዓመት ገባ:: በዚሁ ቀን ምሽት ላይ ከአብሮአደግ ወዳጆቼ ሳሚ: ዳዊትና ተሾመ ጋ ልደታና አካባቢዋ በመዘዋወር ከቡና ቤት ቡናቤት እየለዋወጥን በመጠጥና በዳንኪራ ራሳችንን ስናዝናና አመሸን:: ይገርማል እንደቀልድ ቡና ቤት ገብቶ መጠጥ መጠጣት ጀመርኩ:: እድሜዬ አሁን 21 ዓመት ነው:: ጅማ በተደጋጋሚ ያደረግሁት ቢሆንም አዲስአበባ ግን የመጀመሪያዬ መሆኑ ነው:: በጣም ደስ ና ደስ ብሎኝ ነው ያመሸሁት:: ከነሳሚ ጋር በገባንባቸው ቡና ቤቶች ሁሉ የሚያጋጥሙን አዲሳቤ ጠጪዎች ወጣትም ይሁን ሽማግሌ: ሴትም ሆነች ወንድ: ሁሉም እንደኛው በሞቅታ ንፍቀ ክበብ ውስጥ የነበሩና ቡናቤቶቹ ማዕዘኞች ላይ ከተሰቀሉት ድምፅ አጉሊ ስፒከሮች ከሚሰሙት ማናቸውም አይነት ዘፈኖች ጋር የሚወራጩ ነበሩ:: አሁን ሳስበው እኔ ራሴ ሞቅ ብሎኝ ስለነበር ነው እንጂ እየተወራጩ ሳይሆን እየደነሱ ነበር:: ቡናቤቶቹ በሰው ከመሞላታቸው የተነሳ ለመደነስ የሚሆን ቦታ ባለመኖሩ ሁሉም ሰው እዛው በቆመበት ነው ይወራጭ  የነበረው:: ወደየትኛውም አቅጣጫ መንቀሳቀስ የሰው እቅፍ ውስጥ ከመዳረግ ባሻገር ያልተጠበቀ ሰላምታና መጠጥ ባሰረው ምላስ "እንኩ..ዋ..ዋ....ን አ...ደደ...ረ..ሰህ/ሽ" መባባልን ያስከትል ነበር:: ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲሆን ሁላችንም ወደነ ሳሚ ቤት በመሄድ አንድ ለሁለት ሰው እንደምንም የምትበቃ አልጋ ላይ ተጣበን አደርን::  እኔ በጣም በጠዋት በመነሳትና ወደ ቤቴ በመሄድ ራሴ አልጋ ላይ መተኛቴን ቀጥዬ የነበረብኝን የወገብ ህምም አስታግሼ ና አረፋፍጄ ተነሳሁ:: አሁን ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ተኩል ገደማ ይሆናል.....የልደታ ትዝታ..

ጥቅምት 27 ቀን 1986 አ.ም.

ወሳኝ ወቅት

ከአዲሳበባ እረፍት ከተመለስኩ በሁዋላ አንኩዋር የሆነ አጋጣሚ ባይገጥመኝም: የሶስተኛ አመት የምህርት ሂደትና የኔ ሁኔታ በየቀኑ ባይምሮዬ ይመላለስ ነበር:: ሶስተኛ ዓመት ከገባሁ በሁዋላ በራሴ ላይ ያየሁት ተጨባጭ ነገር ለትምህርት ያለኝ ፍላጎት ክፉኛ ማነሱና ይህም በአንዳንድ የፈተና ውጤቶቼ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው:: ከዚህ በፊት በትምህርት ሂወቴ አይቻቸው የማላውቅ የፈተና ውጤቶች ማግኘት ጀመርኩ:: ይህ ሁኔታ አስደንግጦኝ በርትቶ ለማጥናት በመነሳሳት ፈንታ እኔ ግን የበለጠ የትምህርት ፍላጎቴ ቀነሰ:: ያለፉት ቀናት ጅማ ከገባሁ በሁዋላ ለመጀመርያ ጊዜ በገዘፈ ሃሳብ አእሞሮዬ የተፈተነባቸው  ቀናት ነበሩ:: ምክንያቱም ትምህርቴን አቁዋርጬ ረዘም ያለ እረፍት ለማድረግ ጊዜያዊ መልቀቂያ (ዊዝድሮዋል) ለመጠየቅ አስቤ ነበር:: ነገር ግን ይህ በቀላሉ ይሁን ብዬ የማደርገው ነገር አልነበረም:: አእምሮዬ ጉዳዩን ለመፈፀም ቢገፋፋኝም ከፊቴ የተጋረጡ በቂ መልስ የሚሹ ሞራላዊ የህሊና ጥያቄዎች ነበሩ:: ብዙ ነገሮችና ትዝታዎች ወደአእምሮዬ ተመላልሰው ነበር: ባለፉት ቀናት:: ገና የጅጤሳን ግቢ የረገጥኩ ሰሞን በአውቶቡስ ታጭቀው ወደ ጦር ካምፕ ለስልጠና የሄዱት ጮርቃ ነፍሶች ታውሱኝ:: ከዚያም በድንገት እረፍት ለማድረግ በማሰብ ወደ ጅማ አውቶቡስ ተራ የሄድኩ ጊዜ የተመለከትኩት ትዕይንት ታወሰኝ:: ሌሎች ብዙ ሰዎችና ሁኔታዎች ታወሱኝ......እኔ ከነዚህ ሁሉ እሻላለሁ....አልኩ:: ዞሮ ዞሮ ግን ጭንቅላቴ በሀሳብ ውዝግብ ከሚፈነዳ በሚል ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን ዊዝድሮዋል ለማውጣት ማስረጃ ፍለጋ ከዚህ በፊት ሌሎች ተማሪዎች እንዳደረጉት ዶክተር ይልማ ጋ ሄድኩ:: ይህ ሰው ሳይካትሪስት ወይም የስነ አእምሮ ዶክተር  ነው::  ዊዝድሮዋል ለመጠይቅ የተገደድኩበትን ምክንያት ከላይ እንዳስቀመጥኩት ስነግረው ፈፅሞ ሊዋጥለት አልቻለም::  እኔን በማዳመጥ ብዙ ግዜም መውሰድ አልፈለገም:: በቀጥታ መድረኩን እሱ ተቆጣጥሮት የተለያዩ ምክሮች ከመከረኝ በሁዋላ ትምህርቴን እንድቀጥል በጥብቅ አስጠንቅቆ ሸኘኝ::  የምክሩ ጭብጥ እንደሚከተለው ነበር

" ሰው ሁልግዜ እንደነበረ አይሆንም:: የሂወትን እውነታዎች መቀበል አለብን:: በአንድ ወቅት ከብር የነበራቸው: ሁኔታዎች ሁሉ ተስተካክለውላቸው ይኖሩ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች በሌላ ግዜ ክብራቸው ተገፎ: ሁኔታዎች አልሳካ ብለዋቸው የሚወድቁበት ግዜ አለ:: አንድ ሰው ውድቀቱንም በፀጋ መቀበል አለበት:: ውድቀት የማይከሰት ነገር አድርጎ መቁጠር የለበትም:: መጥፎ ግዜ በመጣ ቁጥር ከችግር ለመሸሽ የማይሆን ነገር መስራት የለበትም:: ችግርን መጋፈጥ አለበት......"



ምክሩ እውነት ሆነም አልሆነም በዚህ አይነት ትምህርቴ ቀጠለ ማለት ነው.........

No comments:

Post a Comment