ሰኔ 2 ቀን 1987 አ.ም.
ዛሬ ለምን እንደሆነ ባላውቅም
ፅሁፌን በዚህ እጅግ መንፈሳዊ ሐረግ እጀምር ዘንድ ውስጤ አለኝ: በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
በዚህች ቅፅበት የምገኘው አዲስ
አበባ ቀራንዮ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታችን ሳሎን ውስጥ ካለችው አነስተኛ ታጣፊ አልጋ ላይ ተቀምጬ ነው::
አራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርቴን አጠናቅቄና ወደአምስተኛ ዓመት መሸጋገሬን አውቄ ከሚያዚያ 28 ጀምሮ በእረፍት ላይ
እገኛለሁ:: እስከ ሰኔ 28 ቆይቼ ወደ ጅጤሳ እመለሳለሁ::
ይህን የማስታወሻ አጀንዳ አንድ
ጉዋደኛዬ በራሱ አነሳሽነት ሰጠኝ:: እሱ ይሕን ባያደርግ ኖሮ ማስታወሻ ሁለተኛ ላለመፃፍ ወስኘ ነበር:: አሁን ግን ሃሳቤን
ቀየርኩ:: ከጊዜ ወደ ጊዜ ማስታወሻ መፃፍ እየታከተኝና አስጠሊታ
እየሆነብኝ ቢመጣም ምናልባት አምስተኛ ዓመት ከኢንተርንሺፕ በፊት የመጨረሻው የህክምና ትምህርት ዓመት ስለሆነ የብዕር ሚዛን
የሚደፋ አጋጣሚ አይጠፋው ይሆናል በሚል ለመፃፍ አሰብኩ::
የዘንድሮ እረፍት ባጠቃላይ ሲታይ
ምንም አይልም:: ደህና ነው:: አንዳንድ ግዜ ብቻ ቀኑ አልሄድ ይላል:: የሚገርመው ነገር ያሳለፍኩት ግንቦት ወር ባልተለመደ
ሁኔታ ብርዳም ነበር:: ከዚህ ብርድ ይሁን ከሌላ ምክንያት ጤንነቴ የጠራ አልነበረም:: ሰውነቴን ለምን በጣም እንደማዳምጥ
አይገባኝም:: በየቀኑ ቁርጥማት ይሰማኛል:: በተደጋጋሚ ይደክመኛል:: ራሴን ቅልል ቅልል ይለኛል:: ሆዴን ያመኛል:: እንቅልፍ
በደንብ አልተኛም:: መተኛት ራሱ ያደክመኛል:: ሽንቴ ከቀድሞ ይልቅ አሁን ቶሎ ቶሎ ይመጣል:: ሌሊት ቢያንስ ሁለት ግዜ
ለመሸናት ከአልጋዬ እነሳለሁ:: ውሃም ቶሎ ቶሎ ይጠማኛል:: ቆዳዬ ያለወትሮው እንደ መድረቅ ብሏል:: እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ይሰውረኝ::
ሐምሌ 3 ቀን 1987 አ.ም.
ዛሬ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ
የአምስተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት ሀ ተብሎ ተጀመረ:: ዶክተር ዳመና የሚባል ያንገት በላይ ቀዳጅ ሀኪም የጉሮሮ: የጆሮና
የአፍንጫ ሕክምና ለሁለት ሳምንት ሊያስተምረን ዛሬ ጀመረ:: ይህ እንግዲህ አናሳ (Minor) ኮርሶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ
መሆኑ ነው:: በበኩሌ በአናሳ ኮርስ አመቱን መጀመራችን ደስ ነው ያለኝ:: ለደምበኞቹ ኮርሶች ገና አልተዘጋጀሁም::
ዘንድሮ በአንድ ዶርም ውስጥ 12
ሆነን እንድኖር ስለተደረገ ካምናው ይልቅ በዶርሙ ውስጥ ከፍ ያለ ግርግር አለ:: ጥበትና ትርምስ ይንፀባረቃል:: ማታ-ማታ
በጣም በምፈልገው ፀጥታ ፋንታ ጫጫታ ይነግሳል:: ለማንበብ ቀርቶ በእርጋታ ለማረፍ እንኩዋን አይመችም:: 12 ሆነን በአንድ
ዶርም እንድንኖር የተደረገው ጅጤሳ አዲስ የዲግሪ መረሃ ግብሮችን በመዘርጋት ተጨማሪ ነርሶችን: ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖችንና ሳኒተርያኖችን
ለማስገባት በማቀዱ ይመስለኛል:: ዋይት ሃውስ ህንፃ በመሰከረም ወር በጣም እንደሚጣበብ እገምታለሁ::