Sunday, July 10, 2016

ሰኔ 2 ቀን 1987 አ.ም.

ዛሬ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ፅሁፌን በዚህ እጅግ መንፈሳዊ ሐረግ እጀምር ዘንድ ውስጤ አለኝ: በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

በዚህች ቅፅበት የምገኘው አዲስ አበባ ቀራንዮ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታችን ሳሎን ውስጥ ካለችው አነስተኛ ታጣፊ አልጋ ላይ ተቀምጬ ነው:: አራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርቴን አጠናቅቄና ወደአምስተኛ ዓመት መሸጋገሬን አውቄ ከሚያዚያ 28 ጀምሮ በእረፍት ላይ እገኛለሁ:: እስከ ሰኔ 28 ቆይቼ ወደ ጅጤሳ እመለሳለሁ::

ይህን የማስታወሻ አጀንዳ አንድ ጉዋደኛዬ በራሱ አነሳሽነት ሰጠኝ:: እሱ ይሕን ባያደርግ ኖሮ ማስታወሻ ሁለተኛ ላለመፃፍ ወስኘ ነበር:: አሁን ግን ሃሳቤን ቀየርኩ::  ከጊዜ ወደ ጊዜ ማስታወሻ መፃፍ እየታከተኝና አስጠሊታ እየሆነብኝ ቢመጣም ምናልባት አምስተኛ ዓመት ከኢንተርንሺፕ በፊት የመጨረሻው የህክምና ትምህርት ዓመት ስለሆነ የብዕር ሚዛን የሚደፋ አጋጣሚ አይጠፋው ይሆናል በሚል ለመፃፍ አሰብኩ::

የዘንድሮ እረፍት ባጠቃላይ ሲታይ ምንም አይልም:: ደህና ነው:: አንዳንድ ግዜ ብቻ ቀኑ አልሄድ ይላል:: የሚገርመው ነገር ያሳለፍኩት ግንቦት ወር ባልተለመደ ሁኔታ ብርዳም ነበር:: ከዚህ ብርድ ይሁን ከሌላ ምክንያት ጤንነቴ የጠራ አልነበረም:: ሰውነቴን ለምን በጣም እንደማዳምጥ አይገባኝም:: በየቀኑ ቁርጥማት ይሰማኛል:: በተደጋጋሚ ይደክመኛል:: ራሴን ቅልል ቅልል ይለኛል:: ሆዴን ያመኛል:: እንቅልፍ በደንብ አልተኛም:: መተኛት ራሱ ያደክመኛል:: ሽንቴ ከቀድሞ ይልቅ አሁን ቶሎ ቶሎ ይመጣል:: ሌሊት ቢያንስ ሁለት ግዜ ለመሸናት ከአልጋዬ እነሳለሁ:: ውሃም ቶሎ ቶሎ ይጠማኛል:: ቆዳዬ ያለወትሮው እንደ መድረቅ ብሏል::  እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ይሰውረኝ::

ሐምሌ 3 ቀን 1987 አ.ም.

ዛሬ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ የአምስተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት ሀ ተብሎ ተጀመረ:: ዶክተር ዳመና የሚባል ያንገት በላይ ቀዳጅ ሀኪም የጉሮሮ: የጆሮና የአፍንጫ ሕክምና ለሁለት ሳምንት ሊያስተምረን ዛሬ ጀመረ:: ይህ እንግዲህ አናሳ (Minor) ኮርሶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ መሆኑ ነው:: በበኩሌ በአናሳ ኮርስ አመቱን መጀመራችን ደስ ነው ያለኝ:: ለደምበኞቹ ኮርሶች ገና አልተዘጋጀሁም::


ዘንድሮ በአንድ ዶርም ውስጥ 12 ሆነን እንድኖር ስለተደረገ ካምናው ይልቅ በዶርሙ ውስጥ ከፍ ያለ ግርግር አለ:: ጥበትና ትርምስ ይንፀባረቃል:: ማታ-ማታ በጣም በምፈልገው ፀጥታ ፋንታ ጫጫታ ይነግሳል:: ለማንበብ ቀርቶ በእርጋታ ለማረፍ እንኩዋን አይመችም:: 12 ሆነን በአንድ ዶርም እንድንኖር የተደረገው ጅጤሳ አዲስ የዲግሪ መረሃ ግብሮችን በመዘርጋት ተጨማሪ ነርሶችን: ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖችንና ሳኒተርያኖችን ለማስገባት በማቀዱ ይመስለኛል:: ዋይት ሃውስ ህንፃ በመሰከረም ወር በጣም እንደሚጣበብ እገምታለሁ:: 

No comments:

Post a Comment