ጳጉሜ 6 ቀን 1987 ሰኞ
ዛሬ የ1987 አ.ም. የመጨረሻ ቀን ነው: ጳጉሜ 6:: የዶርሚቶሪ አልጋዬ አጠገብ ብቻዬን በትካዜ ተቀምጫለሁ:: በክፍሉ ዉስጥ ከኔ በስተቀር ማንም የለም::: በልቤ ውስጥ ያለን ነገር ለማውጣት እየታገልኩ ነው:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም የተለያዩ ሀሳቦች በእንግሊዝኛ አምሮዬ ውስጥ ይመላለሳሉ ግን በጽሁፍ አሳምሬ እንዳላስቀምጣቸው የቁዋንቁው ችሎታ ያጥረኛል:: በክፍሉ መስኮቶች አሻግሬ ስመለከት ዝናብ ሲዘንብ ይታየኛል ድምፁ ግን አይሰማኝም:: ቀፋፊ ቀን:: ምንም የምሰራው ነገር የለም:: የአዲስ አመት ዋዜማ በመሆኑ የትምህርተ-ሂወት እንቅስቃሴ ሁሉ ቀጥ ብሏል:: ከቤትና ቤተሰብ ርቄ ያለሁ በመሆኔ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዚህ ያመትባል ዋዜማም ጥልቅ ድብርት እየተሰማኝ ነው:: ላደለው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ ቀን ነው:: ጥፍጥናው ከዋናው አመትባል የሚልቅበት ግዜ ይበዛል…….
በተረፈ ነገ ሌላ ቀንና አመት ነው:: ይህን እመሰክራለሁ::
መስከረም 1 1988 እንቁ ለጣጣሽ!
“አበባዮሽ ቁሙ በተራ እንጨት ሰብሬ ቤት
እስክሰራ” የሚለውን የዚህን አመትባል የእንስቶች ተወዳጅ ዘፈን አስታወስኩ:: በተለይም ሁለተኛው ስንኝ ከኔና ከአብሮ ተማሪ ጉዋደኞቼ ፊት ለተደረደሩት የአምስተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት ወሳኝ ወራት ጥሩ መግለጫ ነው:: ሁላችንም ዘንድሮ እንጨት ሰብረን ቤት መስራት
ይጠበቅብናል……
እንቁጣጣሽ ለት አየሩ የሚደብር አልነበረም:: ጥሩ መልካምና ብራ ቀን ነበር:: ጠዋት እንደተለመደው ከጉዋደኞቼጋ ወይዘሮ አልማዝ ቤት ሂደን እንኩዋን አደረሳችሁ ካልን በሁዋላ የደንቡን ባህላዊ ዶሮ ወጥ ምግብ ተመገብን:: ከዚያም እየተጫወትን በዚያ ቆየን:: ከሰአት ምሳ ዘውድነህ ቤት ተጋብዤ ነበር:: ዛሬ መቸም የመብልና የመጠጥ ቀን ነው:: ዘውድነህ የተማሪዎች ዲን ቢሮ ሃላፊ ነው:: ዘውድነህን የተዋወኩት በተሰፋሁነኝ
በኩል ነው:: በዘውድነህ ቤት ዶክተር ተስፋም ነበር የዘውድነህ ባለቤትም እንዲሁ:: ቆንጆ ያመትባል ምግብ ተዘጋጅቶ ነበር:: ብዙ ጠላ በመጠጣቴ ደክሞኝ ስለነበር ከዚያ እንደተመለስኩ መኝታ ክፍሌ ገብቼ ተኛሁ::
መስከረም 2 1988 ሮብ
ሁሉም ነገር ወደነበረበት ተመለሰ:: አመቱ ብቻ ተለውጧል:: ስለዚህም ማጥናት ነበረብኝ:: ዛሬ Fluid and Electrolyte Management እንዲሁም Breast Diseases ለማንበብ ሞክሬ ሁለቱም ጭብጦቻቸው በቀላሉ አልፈታና አልገለፅ ብለውኝ ስለነበር ተበሳጭቼ ዋልኩ::
መስከረም 3 1988 ሃሙስ
ዛሬ ቀን እንዴት Femoral Hernia በቀዶ ጥገና እንደሚስተካከል እየረዳሁ አየሁ:: በምሽቱ በድንገተኛ ክፍል ተመድቤ ነበር:: ኢንተርንሺፕ ሃኪሞች ባጋጣሚ ባለመኖራቸው የነሱን ስራ ተክቼና ሙሉ በሙሉ ራሴን ችዬ የመስራት እድል አጋጥሞኝ ነበር:: በመሆኑም ለመጀመሪያ ግዜ በሽተኛን ወደ ህሙማን ክፍል ገብቶ እንዲታከም አዘዝኩ:: ረዥሙን ፊርማዬን ካርዱ ላይ በማኖር ህመምተኛን ኣድሚት (Admit) አደረኩ:: ለመጀመሪያ ግዜ የወሰንኩት Clinical
Decision…. ከባድ ውሳኔ ነው:: ግን ደስ አለኝ:: ወንዳታ አልኩት ራሴን:: ህመምተኛዋ የ 10 ወር ህጻን ስትሆን በሳምባ ምች (Brncopneumonia) ነው የመጣችው:: እብቅ እብቅ ትተነፍሳለች:: በትንፋሽ ማጠር ምክንያት የእናቷን ጡት መጥባት አልቻለችም::
የሳንባ ራጅ አዝዤ ተሰራላት:: ራጁ ተሰርቶ መጣ:: አየሁት:: ሳምባዎችዋ ሙሉ በሙሉ በደዌው ቆስለዋል:: “በደምስር የሚሰጥ ጸረ ተውሳክ (Antibiotic)ና ኦክሲጂን ባስችኩዋይ ያስፈልጋታል” አልኩዋቸው ለእናቷና እናቷን አጅበው ለመጡት ቤተዘመዶች :: ስለዚህ በህፃናት መኝታ ከፍል ቆይታ መታከም አለባት:: በኔ ውሳኔና ትዕዛዝ መሰረት ሚጢጢዋ ፍጥረት በእናቷ
እቅፍ ውስጥ ሆናና በቤተዘመድ ታጅባ ወደ ሕፃናት መኝታ ክፍል ስትወሰድ እያየሁ……”እውነት ነው?” አልኩ በውስጤ
No comments:
Post a Comment