ጥቅምት 19 1988 አ.ም.
የውስጥ ደዌ ሕክምና (Internal
Medicine) በእውነትም ሰፊ እጅግ በጣም ሰፊ ነው:: በዚህም የተነሳ አሁን ያለሁበት የተግባር ልምምድ ፈታኝ ነው:: ብዙ
ብዙ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ማንበብ ይጠይቃል:: ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ መጠየቅን ይጠይቃል::ለ እያንዳንዱ በሽታ ለምን አንደመጣ ከየት እንደመጣ እንዴት
እንደመጣ መቸ እንደሚያበቃ በምን እንደሚያበቃ ምን እንደሚያስከትል እና ሌሎችም እልፍ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው :: እንደ የውስጥ ደዌ ሕክምና
ተማሪነቴ እንዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በሰኮንድ በሚቆጠር ቅፅበት በአእምሮዬ ውስጥ ፈጥሬ መልሱንም መመለስ ይጠበቅብኛል:: ይህ ግን በተግባር ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ነው:: የቻልኩትን ያህል እሞክራለሁ:: የቻሉትን መሞከር ጥሩ ተግባር ቢሆንም ዶክተር ጴጥሮስ በሚጠይቅ ግዜ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ አውቆ አለመገኘት ተስፋ
አስቆራጭ ነው:: ለአሸማቃቂ ትግሳፅ ይዳርጋል::
እያንዳንዱን በሽታ ከስሩ ጀምሮ ለማንበብና ለማስታወስ ከሚገመተው በላይ ግዜ ስለሚወስድ ብዙ ግዜ መሸምደድ
ያስፈልጋል:: ሽምደዳ አጭሩ መንገድ (Shortcut) የሆነበት ፊልድ ሕክምና ብቻ ይመስለኛል::
የህክምና እውቀታችን ከሚገመግምባቸው የዘወትር መድረኮች
አንዱ ያልጋ ዙሪያ ውይይት (Bed Side) ነው:: በዚህ በበሽተኛው
ዙሪያ ቆመን በምናደርገው ውይይት ከመካከላችን አንድ የህክምና ተማሪ ከተመደቡለት ህሙማን ሰለ አንዱ ዝርዝር ሁኔታ ለአስተማሪው
ዶክተርና ለቡድኑ አባላት ያቀርባል:: አስተማሪው በርካታ ጥያቄዎች
ይጠይቃል:: አብላጫው ጥያቄ ላቅራቢው ቢሆንም ሁሉም የቡድኑ
አባል ቢያንስ አንድ ጥያቄ ይደርሰዋል:: ሁሉም ያቅራቢውን ሐተታ ከሰማ በሁዋላ በፍጥነት በማሰብ ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀት አለበት::
አላውቀውም ማለት ቢቻልም ደጋግሞ ግን አላውቀውም ማለት ከላይ እንዳልኩት ለአሸማቃቂ ታግሳፅ የሚዳርግ ነው::
ለምሳሌ ዛሬ ጠዋት አንድ AGN (Acute Glomerulonephritis)
ኬዝ ላይ Bed Side ነበረን: ከዶክተር ጴጥሮስ ጋር:: ባጠቃላይ
ጥሩ አልነበረም:: ( ማለትም ዶክተር ጴጥሮስ ሁላችንንም ገስፆናል) ማለት ነው:: ከሰዓት ደሞ Management Session ነበረን:: ይህ እንደ Bed Side አይነት ቢሆንም በሽተኛው በሌለበት ክላስ ሩም ውስጥ የሚካሄድ ጠለቅ ያለ ትምህርት ነው:: ኬዙ Diabetic Ketoacidosis, Hypoglycemia ና Hyperosmolar coma ነበር:: እጅግ የሚያደክም
ከሰዓት ነበር:: በዚህ የተነሳ ምሽቱን ከማንበብ ቦዘንኩ:: ለነገ መነበብ የነበረባቸውን Anemia ና Bone
& joint tuberculosis ሳላነብ አሸለብኩ::
No comments:
Post a Comment