የመጀመሪያ ግንዛቤ
ዛሬ አመሻሹ ላይ ከተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ (ጃምቦ ምግብ ቤት) ራት ተመግቤ ስወጣ አንድ የ ነርሲንግ ተማሪ የሆነ ወጣት ከአዲስ አበባ የተላኩ አምስት ደብዳቤዎችን ሰጠኝ:: እርሱ በግል ችግር ዘግይቶ ገና መምጣቱ ነው:: ሶስቱ ደብዳቤዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ዓመት ከገቡ የ ሃይ ስኩል ጉዋደኞቼ የተላኩ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከሰፈር አብሮ አደጎቼ ነበሩ:: ብዙም ግዜ ሳላጠፋ ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ በመሄድ አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ ደብዳቤውቹን አንድ ባንድ አነበብኩዋቸው:: የሁሉም ደብዳቤዎች አጠቃላይ መንፈስ ሰላምታ ነው:: እየረሳሁት የነበረውን የሰፈርና የቤተስብ ናፍቆት በትዝታ ትጎትቼ እንደገና ተጋተርኩት:: ወደ ትምህርቱ ትኩረት በማድረግ በኩል ደህና ተሽሎኝ ነበር:: እንደመጀመሪያው ብዙ ሃሳቦች በአንድ ግዜ የሚመጡብኝ አባዜ ትቶኝ ነበር:: ከሩቅ ትዝታ ለመውጣት ስል ስለ ጅጤሳ ማሰብ ጀመርኩ ለምሳሌ የ ትናንትና ውሎዬን.....
የትናንትናውን ከሰዓት የህክምና ተማሪዎች በሙሉ ያሳለፍነው ባዮሎጂ ላቦራቶሪ ውስጥ ነበር:: ትምህርት ከጀመርን የመጀመሪያው ላቦራቶሪ ክፍለ ግዜ መሆኑ ነው:: የ ክፍለ ግዜው ዋና መንፈስ በማይክሮስኮፕ መመልከት ነበር:: ለመጀመሪያ ግዜ ከማይክሮስኮፕ አጉሊ መነፅር በታች ቅንጣት ፀጉር አኑሬ ተመለከትኩ: እንደሌሎቹ ተማሪዎች:: ማይክሮስኮፑ አንድ ለአንድ ስለማይበቃ ፀጉሩን ያየነው በቡድን ሆኖ በየተራ ነው:: እኔ ባጋጣሚ ከሴቶቹ አንዱዋ ጋ ስለነበርኩ የፀጉር ቅንጣት ለማግኘት አልተቸገርኩም:: ሌክቸር ላይ የሚፈጥነውና ሲናገር የትግርኛ ለዛ ያለው የባዮሎጂ ኢንስትራክተር ፀጉሩን በማይክሮስኮፕ ካየን በሁዋላ ሀተታ (Report) እንድንፅፍ ባዘዘን መሰረት እኔም ፃፍኩ:: ግን ዛሬ ሳስበው አንድ የከነከነኝ ነገር አለ:: በሀተታው መጨረሻ ላይ ግንዛቤ (Conclusion) ብዬ ያስቀመጥኩት እንዲህ ይነበባል በእንግሊዝኛ... "Black hair appears brown under microscope":: ለራሴ አሳቀኝ:: የሳኩበት አንዱ ምክንያት ዘሬ የፀጉሩ ቅንጣት ባለቤት የሆንችውን ልጅ በቅርብ ርቀት ና በትኩረት የማየት ዕድል ስለገጠመኝ ነው: ቅድም አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቅምጠን ነበር ምሳ የበላነው:: የልጅቱዋ ፀጉር ጠቆር ይላል እንጂ ለካ ቡና አይነት ነው!
ናፍቆት ውስጥ ላለመግባት መታገሌን ቀጥያለሁ.....በነገራችን ላይ ትናንትና ማታ ለሁለተኛ ግዜ የመብራት አገልግሎት ተቁዋርጦ ነበር:: ደግነቱ መፅሐፍት ቤት ውስጥ አልነበርኩም:: አንድ ጅማ ውስጥ የማውቃቸው ቤተሰብ ቤት ውስጥ ነበርኩ:: እኔ የነበርኩበት ሰፈር መብራት ስለነበረ ወደ ጅጤሳ ስመለስ ነው ኤሌክትሪክ መቁዋረጡን ያወቅሁት:: ቀስ በቀስ የተገነዘብኩት ነገር መብራት ብቻ ሳይሆን ዉሃም በተደጋጋሚ ይቁዋረጣል:: ዛሬ ቀን እንኩዋ የተማሪዎች ምግብ ቤት ዉስጥ የእጅ መታጥቢያም ሆነ ጉርሻን ከጉሮሮ ማውረጃ የሚሆን የመጠጥ ዉሃ አልነበረም:: ምሳ በደረቁ ተበላ:: እኔም ፀጉር በላሁ.....ባይኔ
የጤና ሳይንሱ ግቢ መቸም ሰፊ ነው:: እኛ ወንዶቹ ከምናድርበት ቀይ የሸክላ አዳራሽ አንስቶ ሴቶች ና ከፍረሽ ማን ባሻገር ያሉ ተማሪዎች የሚኖሩበት ዋይት ሃውስ የሚሰኝ ህንፃ ለመድረስ አንድ አስር ደቂቃ ይፈጃል መሰል:: በመጀመሪያ ከኛ ማደሪያ ወጥቼ በ ዛፎች መሃልና በመፀዳጃ ቤቶቹ ጎን: ብዙ ቀደምት የእግር ጉዞዎች በሰሩት ቀጭን የእግር መንገድ ላይ እራመዳለሁ:ከዚያም በመፅሕፍት ቤቱ ጎን አድርጌ በቀኝ የተማሪዎች ሻይ ቤት በግራ የጤና ሳይንሱን ዋና መግቢያ በር በርቀት እያየሁ አልፍና ወደ ነርሲንግ ደፓርትመንት ህንፃ የሚወስድ የእግር መንገድ ላይ እወጣለሁ: እዚህ መንገድ ላይ ዳር ዳሩን የተከረከመ ፅድ ያለ ሲሆን በቀኝ የ ምርቃት ስታዲዮም እየተገነባ ያለበትበት የጎደጎደ ቦታ በግራ ደግሞ መሃሉ ላይ የባንዲራ ምሶሶ የቆመበት አነስተኛ ሜዳማ ስፍራን አልፎ ስንጀምር የተመዘገብንበት የ ሸክላ ህንፃ ይታየኛል:: በዚህ የሽክላ ህንፃ ውስጥ የተማሪዎች ጉዳይ ቢሮ ና ክሊኒክም ይገኛል::በነርሲንግ ህንፃ ስር ባለ ሰፊ መተላለፊያ ኮሪዶር አልፌ በመቀጠል በቀኝ የኛን ሌክቸር ሆል በግራ ደግሞ ባዮሎጂ ላቦራቶሪን አልፋለሁ: ሁለቱም ከብሎኬት የተሰሩ ናቸው:: ከዚያም አቅጣጫዬን ወደ ቀኝ በማድረግ ወደ ዋይት ሃውስ አቀናለሁ:: ረጅም የእግር መንገድ ነው ይሄ:: ጎዳና ብለው ይሻላል:: በሁለቱም ጎኑ በሳር የተሸፈነ ወጣ ገብ መሬት ሲኖር በቀኝ አልፎ አልፎ ዛፎች አሉ:: የዓመቱ መግቢያ በመሆኑ ነው መሰል ሳሩ ርዝመቱ የዋዛ አይደለም:: በቅርቡ ይታጨዳል የሚል ግምት አለኝ....
መልካም.....ቸር ይግጠመን
መልካም.....ቸር ይግጠመን
No comments:
Post a Comment