Unknown B
እኔና እኔን መሰል የህክምና ተማሪዎች ጠዋትና ከቀትር በሁዋላ ለትምህርት: ማታ ማታ ደግሞ ለጥናት በምናውለው ሰዓት ምክንያት እረፍት አጥተን ግዜ እያጠረን: የ ቀኑን መሮጥ ሳናውቀው: በእለት ተለት ክስተቶች ታጅቦ ግዜ ወደፊት ሲነጉድ የግዜን ተቃራኒ አቅጣጫ ይዞ ደሞ የ ግማሽ ሰሚስተር ፈተና ከች አለ!
ከፊዚክስ በስተቀር በሁሉም የትምህርት አይነቶች ፈተና ለመውሰድ የቀረን አንድ ሳምንት ብቻ ነው:: ፊዚክስ ፈተና ነገ እንወስዳለን! ወይኔ! አሁን ይሄን በምፅፍበት ሰዓት ብዙዎቹ እኔን መሰሎች በየሌክቸር ሆሉ: በየ ዶርሙ: በላይብረሪው ጥጋጥጎች እንዲሁም ውጭ ሳይቀር ባገኙት አመቺ ቦታ ሁሉ ተቀምጠው ረዛዥም በሆኑ የፊዚክስ ቀመሮች ራሳቸውን ያለማምዳሉ:: ነገ በ ፍሬሽማን ሌክቸር ሆል ውስጥ መንኮራኩር ይመጥቃል! የብርሃን ጉዞ: የኮስሞስ ና የ አስተሮይድ ርቀት ይለካል...
ይህችን አጭር የሆነች ማስታወሻ ከመዝጋቴ በፊት አንድ ነገር ልበል:: አሁንም በባዮሎጂ ላቦራቶሪ ውስጥ የሚፈጠሩ አጋጣሚዎቼ እንደቀጠሉ ናቸው:: ከትናንት ወዲያ ከሰዓት የምግብ አይነቶችን መለየት በሚል ርዕስ በላቦራቶሪ ውስጥ የሚገኙ Pipettes (ፓይፔትስ) በመጠቀም የተለያዩ ኬሚካሎችን ካንዱ ብርጭቆ ወደ አንዱ የማገለባበጥ ሥራ ላይ ነበርን:: በመጀመሪያ ምን እንደነካኝ አላውቅም አንድ ቴስት ቱብ ሰበርኩ:: የሱ ሳያንስ ትንሽ ቆይቼ አንድ "Unknown B" የሚል ፅሁፍ የሰፈረበት ቴስት ቱብ ውስጥ ያለን ኬሚካል ወደ Pipette ውስጥ ለመሳብ ዘወትር እንደሚደረገው በመጠኑ በፓይፔቱ በላይ በኩል በአፌ ሳብ አደርጋለሁ ስል ኬሚካሉ እየተምዘገዘገ ወጥቶ አፌ ውስጥ ተዘራ:: በ reflex action ጠጣሁት:: ምንም ምንም አይልም ለነገሩ:
ምንነቱ ያልታወቀ ነገር በመጠጣቴ ደነገጥኩ: ግን ጠጥቼ ቀና ስል ማንም መጠጣቴን እንዳላስተዋለ ተገነዘብኩ:: ጎሽ! ሁሉም በየራሱ ጠረቤዛ ላይ በተመሳሳይ ሥራ ተጠምዱዋል: ግማሹ እንደኔ ፓይፔት ይዞ መጠጣ ያካሂዳል:: ሌላ የጠጣ ቢኖርስ? አልኩ በሆዴ:: ማን መጠጣቱን ማን ያውቃል?
Unknown B ከጠጣሁ ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ምንም የተከሰተብኝ ነገር ባለመኖሩ ፍርሃቴ ለቀቀኝ........
No comments:
Post a Comment