ከምሽቱ ፬ ሰዓት ከ ፶ ደቂቃ
ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ፭ተኛ ብርጌድ ፫ተኛ ሻለቃ ፪ተኛ ሻምበል መኝታ ክፍል
ስለ ብላቴ ምንነት: እንዴትነትና መልካምድር ወዘተ አሁን ለመተንተን አልፈልግም ግን በአጭሩ ቦታው ጫካ + ተራራ+ ወንዝ+ ድንጋይ+ ጭለማ+ ዝናብ+ ዓቡዋራ+ እሾህ+.......ነው:: ዛሬ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቁዋም ከደረስን ሳምንት ተጠግቷል::
በዚህ ቀን ሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ከአልጋችን ተነስተን ወደ ቁርስ እንድንሄድ በፊሽካ ስንታዘዝ ብንበሳጭም ወደሁዋላ ላይ የ ደቡብ ዝ ኦርኬስትራ በሙዚቃ "ሊያዝናንን"" መሆኑን ሰምተን ተረጋጋን:: በየሻምበላችን ተከፋፍለን ታዳሚ ወደሚቀመጥበት ኮረብታ እየዘፈንና እየሮጥን (ሞራል አውጥተን) እንድንሄድ ታዘዝን:: አብዛኛው ተማሪ እንደኔ በሰሞኑ የጠዋት ስፖርት የተነሳ ስትራፖ የያዘው: ባይዘውም እየዘፈነ ለመሮጥ ወኔ የሚያጥረው ስለነበር ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ የሄድነው በተልፈሰፈሰ ርምጃ ነበር::
እንደምንም ኮረብታዋ ጋር ደረስን:: ወደ ኮረብታዋ ቀድመው ከመጡና ሰማያዊ ቱታ ከለበሱ ሌሎች ሰልጣኝ ወንዶች ጋር ተቀላቀልን:: ከኛ በመቀጠል አሰልጣኞቻችን የሆኑት አየርወለዶች መጡ:: በመጨረሻ ሴት ሰልጣኞች መጡ:: በዚህ ግዜ ሰልጣኝ ወንዶች ያሰሙት ጩህት በክብር እንግድነት ተማሪው መሃከል የተቀመጡትን የማሰልጠኛው አዛዥ ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያምን ሳያስደነግጣቸው አልቀረም:: የጤና አልነበረም:: ለነገሩ አልገረመኝም:: ባለፉት አምስትና ስድስት ቀናት "በፍላጎታችን ነው የመጣነው" በሚል ሰበብ መረን የለቀቀና ከሥርዓት ውጭ የሆነ ባህሪ የሚያሳዩ ተማሪዎች ቁጥራቸው ጨምሯል:::
ኮረብታዋ ላይ አስር ሺህ የሚሆን ወታደራዊ ሰልጣኝ የኮሌጅ ተማሪ በሙሉ ግጥም ብሎ ከስር ከድንጋይ ና ከቀይ አሸዋ ክምር የተሰራ መድረክ ብጤ ጉብታ ላይ የሙዚቃ ባንዱ ይጫወታል: ይነፋል: ያቅጨልጭላል:: ዘፋኝ በየተራ ያቀነቅናል...እድሜ ላመንግስቱ ሃይለማርያም....
በመድረኩ ና በተቀመጥንበት ኮረብታ መሃል ለወትሮው የመኪና መንገድ የሆነ ክፍት ቦታ ላይ ተማሪ ግጥም ብሎ ይወራጫል:: መድረኩም ላይ በብዛት የሚታዩት ሰማያዊ ለባሽ ተማሪዎች ናቸው:: በዕለቱ የቀረበው ሙዚቃ ና ዘፈን ስሜት የሚነካ ቢሆንም ብዙ ደናሽ ነኝ ባይ ተማሪ የሚወራጨው በደመነፍስ መሆኑን ልገነዝብ ችያለሁ:: የሙዚቃው ሪትምና የነዚህ ተማሪዎች መወራጨት (ዳንስ) በጭራሽ አብሮ አይሄድም:: እኔም ከተራራው ለመውረድና ለመወራጨት ፈልጌ ነበር: ግን መሬቱ ሩቅ ከመሆኑም ባሻገር ትናንት የሰራሁት ስፖርት ጡንቻዬን ሽምቅቆት ነበር:: ስለዚህ ፍላጎቴን ገታሁት::
ሙዚቃው ከሰዓት አጋማሽ ላይ ተጀምሮ ወደ አመሻሹ የዘለቀ ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎች ከማሰልጠኛው አስር ና ሃያ ኪሎ ሜትር ድረስ ሄደው አረቄና ጠጅ ጠጥተው እንደመጡ የሆነ ሰው ሹክ ብሎኛል::
የመድረኩ ላይ ትርምስ ና ግርግር የትየለሌ ነበር:: ገና አቀንቃኙ ከጉሮሮው ድምፅ ሳይወጣ መድረኩ በአልባሌ ተወራጮች ይሞላል:: በተለይ የማልረሳው አቀንቃኝ አረጋሀኝ ወራሽ የሚዝፍንበትን የድምፅ ማጉያ ወደአፉ ማስጠጋት እስኪያቅተው ድረስ በተማሪዎች ሲዋጥ እንደነበር ነው :: አየርወለዶቹ በተማሪዎች ሁኔታ ብስጭት እንደገባቸው ግልፅ ነው:: ቢችሉ እያንዳንዱን በጫማ ጥፊ እያሉ ቢያስተኙት በወደዱ:: ዳሩ ምን ያደርጋል "በፍላጎታቸው ስለመጡ: እንዳትነኩዋቸው" ተብለው ታዘዋል አሉ::
No comments:
Post a Comment