Wednesday, May 28, 2014

ብላቴ 4



መጋቢት ፪፱ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.
የብላቴ ፋሲካ ና የኔ መከፋት

*ስለዛሬው ቀን ከማወራ ይልቅ በትናንትናው እለት ከየኮሌጁ የመጡ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች አዘጋጅተውት ስለነበረው የትንሣዔ ዋዜማ ክብረ በዓል በጥልቀት ብተነትን ደስ ባለኝ:: ነገር ግን ዝግጅቱ በጣም የጎላ: የግድ ትዝታ የሚጥል  ና ባልፅፈውም እንኩዋን ልረሳው የማልችል መስሎ ስለተሰማኝ ያለብዙ ብእር በትንሹ ብቻ ነካ አድርጌ ላልፈው ወሰንኩኝ:: ከሁሉም ከሁሉም ክርስትያኞቹ የስቅለት ዝማሬና ወረብ በሚያከናውኑበት ጊዜ እንደከበሮ የተጠቀሙት እውነተኛ ከበሮ ሳይሆን ለውሃ ማስቀመጫ ተብለው ለየጉዋዱ የታደሉ ጀሪካኖችን መሆኑን ልብ በል/ይ:: ክብረ በዓሉ የተካሄደበት የመሰብሰቢያ ኬስፓን ለወትሮው ሙቀት ለመቀነስ በሚል ከውስጡ በጥጥ አንኩዋሮች የተለበጠ ቢሆንም ትናንትና ግን በአሉን ምክንያት በማድረግ ከጥግ እስከ ጥግ በተወጠሩ የሰልጣኝ ተማሪዎች አንሶላዎች ተሸፍኖ ነበር:: ጧፍ በብዛት ነበር: ከየት እንደመጣ ባላውቅም:: ማርያም ልጇን ክርስቶስ እየሱስን አቅፋ ያለችበት ትልቅ ስዕል ዳር ዳሩን ነጠላ ለብሶ መድረኩ ላይ ይታይ ነበር:: ስዕሉ ፊትለፊትና ዙሪያ ሻማዎች ና ጧፎች ይበሩ ነበር:: ሰልጣኝ ተማሪ ግጥም ብሎ ነበር:: አሁንም ከየት እንደመጣ የማላውቀው ቤተክርስትያን በሄድኩባቸው ጥቂት የቀድሞ ጊዜያት ሽታውን የማስታውሰው እጣን ና ነድ ክፍሉን አውዶት ነበር:: "አማን በአማን" የሚለው የትንሣዔ መዝሙር ሲዘመር ብዙ ተማሪዎች ጥልቅ ስሜት ውስጥ ገብተው እንደነበር አስተውያለሁ:: በዚያ የፍሎረሰንት ነጭ ብርሃን በሰፈነበት አዳራሽ ውስጥ ክብ ሰርተው በስሜት የሚዘምሩ ተማሪዎች ብዙዎቹ ላብ በላብ ሆነውና አይኖቻቸው ሰፍተው በአካል በዚያ ቦታ ላይ ይሁኑ እንጂ በመንፈስ መጥቀውና ና ተለይተው: በጋራ በሚሰማው ጉልህ ዝማሬ  ውስጥ የያንዳንዱ ጮህ ማለት የሚታወቀው አንገቶታቸው ላይ ባሉት የተወጠሩ ደም ስሮቻቸው አማካይነት ነበር.....በዕለቱ የጅማ ጤና ሳይንሶቹን ጨምሮ መንፈሳዊ ትምህርት የመስጠት ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ከየኮሌጁ የመጡ አውራ ኦርቶዶክስ አማኞች እንዲሁም አንኩዋር ዲያቆናት በብዛት ነበሩ:: አቤት የመዝሙር መዓት! እርግጠኛ ነኝ በብላቴ ታሪክ እንዲህ አይነት መንፈሳዊ ስብሰባ ተደርጎ አያውቅም.........ይህ ታዲያ ትናንት አለፈ

በአንፃሩ የዛሬው ቀን እጅግ የከፋ ነው:: በፋሲካ ቀን ከቤቴ ውጭ በጣም ርቄ የሰው ልጅ ብዙም የማይደርስበት ጫካ ውስጥ ነኝ:: ውስጥ ቢሆኑ ሙቀቱ አቅላጭ: ውጭ ቢወጡ እንዳውም ፀሀዩዋ ተጨምራ የምትቀውር: እሩቅ ልመለከት ቢባል አፈር የለበሰ ሜዳ ላይን እስኪታክት: በቆንጥር ተከትሎ ብሎም ተራራ....ፍፁም ደስ ያማይልና ተስፋ የሚሰርቅ ሁኔታ:: ሙት ሙት የሚል ቀን ነው የሆነብኝ:: የልቤ ምት እንዲሁም የህልውና መሻቴ ቁልቁል ወረደብኝ:: ደበረኝ:: ሕክምናም ሆነ አማካሪ የሌለው ነገር-በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ሌላም በርካታ እንደኔ የደበራቸው ተማሪዎች አሉ:: ነገ መጥቶ ያው የተለመደው ወታደራዊ ትምህርት እስከሚቀጥል ቸኮልኩ:: ይገርማል ወታደራዊ ትምህርት ከሌላ ነገር ተሽሎ ተገኘ......ያለፈውን ዓመት የቤታችንን ፋሲካ አስታወስኩ:: የማትሪክን ፈተና ወስጄ: ከደብተርና ከጥናት ነፃ ሆኘ የአዲስ አበባ በጋ ከመግባቱ ሁለት ወር ቀደም ብሎ ብዙም ባልሞቀ ና ብዙም ባልቀዘቀዘ ነፋሻ አየር በጣም በተረጋጋ ና ሂወት በተሞላ ሁኔታ ነበር ፋሲካን ያሳለፍኩት.....

አሁን ደግሞ ቆም አልኩና ብላቴ ከመጣሁ ጀምሮ ስለሚሰሙኝ አዳዲስ ስሜቶች አሰብኩ:: በራሴ ፍላጎት ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሆኑ የፀባይ ለውጦች እያሳየሁ ይመስለኛል:: ከተስፋ መቁረጥ የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ:: ለምሳሌ ቀልድ አስጠልቶኛል:: ከባድ ነው ቀልድ ፈርቶ ከሰው ጋ ተደባልቆ መኖር: አብረው የማይሄዱ ነገሮች:: ዝም ማለት እፈልጋለሁ:: ታየኝ እኮ እኔ ዝም ስል:: ለብቻዬ መሆንም አማረኝ:: ይሄም አጉል ይመሰለኛል:: መገረም ትቻለሁ:: ለራሴና ለጤናዬ የማደርገው ጥንቃቄ ቀንሷል....


*አንባቢ ሆይ ዛሬ ላይ ሆኘ ዘመን በፈጠረው ድረ ገፅ ከላይ ያለውን ፅሁፍ ከማስተወሻ ደብተሬ ላይ ስገለብጥ ና በምልሰት ግዜውን ስቃኝ በማስታወሻው የመጀመሪያ አንቀፅ ውስጥ የሰፈረው ሁነት የሆነበት ቀን ማህበረ ቅዱሳን የተባለው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ስብስብ የተመሰረተበት እለት እንደሆነ አስታወስኩ:: ይህ ትክክል ካልሆነ አርመኝ::

Tuesday, May 20, 2014

ብላቴ 3

መጋቢት ፪፯ ፩፱፰፫ አ.ም. 
አርብ ለት - ስቅለት

ዕለቱ ስቅለት ነው:: ይህን ግዙፍ የክርስትያን አመትባል ከቤቴ ውጭ ለመጀመርያ ግዜ ማሳለፌ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ዉስጥ መሆኔን ሳስበው ዘገነነኝ::የዛሬ ዓመት ትዝ አለኝ:: ቤታችን: ሰፈሩ: መንደሩ: ሽታው: ሳሩ: ቅጠሉ: በሬው: በጉ ና ዶሮው: ጭሱ ሁሉ ትዝ አለኝ...ወይኔ...

ዛሬ ታይገር የተባለው የአየር ወለድ ሙዚቃ ባንድ ነው ሰልጣኝ ተማሪዎችን እንዲያስደስትና እንዲያዝናና የታዘዘው:: ያለ አዲስ ክስተት ና ያለብዙ ተመልካች ሙዚቃው ተከናወነ:: 

ሰልጣኝ ተማሪው በአጭር ግዜ በብላቴ ውስጥ ኑሮ ተሰላችቷል:: ለአየር ወለዶቹ የተማሪ መታዘዝ ሕልም ከሆነ ሰንብቷል:: በሜንስ ቤት: በሰልፍ ቦታ ላይ: በኬላዎች ና በ ሴት ሰልጣኝ ተማሪዎች መኖሪያ አካባቢ ያሉ አየር ወለዶች በተደጋጋሚ ከወንድ ተማሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ:: ሆኖም ምንም አይነት እርምጃ በተማሪ ላይ አይውስዱም:: እንደውም አንድ ጉዋደኛዬ እንደነገረኝ ስድስተኛ ብርጌድ ውስጥ አንድ የ መቶ አለቃ አየር ወለድ አንድ ተማሪ ሰልጣኝን ሊመታው እጁን ሲሰነዝር ሌሎች ተማሪዎች አንድላይ በመሆን መቶ አለቃውን ሊደበድቡት ነበር:: አንዳንድ መኝታ ክፍሎች ውስጥ "እንደውም ቶሎ ወደየቤታችን ይመልሱን" የሚለው ቃል እየተሰማ ነው::የአምስተኛ ብርጌድ አዛዥ የሆነው የ ሻምበስ ኦልቀባ ንዴት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ማበድ የቀረው ይመስላል:: ዘወትር ሲናገር በብስጭት ና እምባ እስከሚወጣው ድረስ ነው:: በቀደም ለት ሰልፍ ላይ: "እኔ እናንተ ከመጣችሁ ከሰውነቴ ክብደት ላይ አምስት ኪሎ ቀንሻለሁ" ብሎ ተናገረ:: ተማሪዎች በሆዳቸው: አንዳንዶቹም ፊት ለፊት ሳቁ::

ከምግብ እና ከምግብ እቃዎች ፅዳት ጉድለት የተነሳ በማሰልጠኛ ውስጥ ከባድ የሆነ አጣዳፊ ተቅማጥ ና የሆድ በሽታ በመዛመት ላይ ነው:: እኔም ራሴ ሳይዘኝ አይቀርም: የምፀዳዳው ጥሩ አይነት አይደለም:: አንዳንድ ተማሪዎች በጣም ስለሚያጣድፋቸው አንሶላ እንደ ሽርጥ አገልድመው ጫካው ና ቆንጥሩ አጠገብ ይውላሉ: ዳማ ወይም ካርታ እየተጫወቱ:: በዚህ ላይ ደሞ ትናንትና ለወባ መከላከያ ተብሎ ለተማሪው ሁሉ የታደለውን አራት አራት ክኒን የዋጡ አንዳንዶች ትውከትና ፌንት መውጣት ድረስ ሁሉ አጋጥሙዋቸው ስለነበር የማሰልጠኛው ሆስፒታል ተጨናንቆ ነው የዋለው:: እንደውም ያ መከረኛው ስድስተኛ ብርጌድ አካባቢ የሞተ ተማሪ አለ እየተባለ ይወራል:: ይህን ስሰማ ፈራሁ-ብሞትስ? ብዬ:: አስቤው የማላውቅ ነገር ነው:: ደግነቱ የወባ መከላከያውን ክኒን አልዋጥኩትም::

ከሙዚቃው ዝግጅት በሁዋላ ስድስተኛ ብርጌድ ያለው ጉዋደኛዬ ከፈለኝ ጋ ሂጄ ነበር:: ከፈለኝ ከኔ በሁዋላ የመጣ ቢሆንም ከኔ የባሰ ደግሞ ነገር አለሙ ስልችት ብሎት ፊቱ ላይ የድካምና የቸልተኝነት እንዲሁም የመብሸቅ ሁኔታ ይነበብበታል:: ክፈለኝ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ተማሪ ተመሳስይ አይነት ስሜት  ውጥ ነው ያለው:: ቶሎ ወደየ ቤታችን ይመልሱን እያለ ያወራል..

ከከፈለኝ በሁዋላ ምሽቱ ላይ አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ተማሪዎች ተሰባስበው ስቅለትን ወድሚያከብሩበት የኬስፓን አዳራሽ ሄድኩ:: ፀሎትና ቅዳሴ በረዣዥሙ ነበር:: ዝግጅቱ ከምሽቱ ፯ ሰዓት ተጠናቀቀ.....

Wednesday, May 7, 2014

ብላቴ 2

መጋቢት ፪፫  ፩፱፰፫ አ.ም.
ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ - አሁንም አልጋዬ ላይ 


ትናንትና ከደቡብ እዝ ሙዚቃ ዝግጅት በሁዋላ ወደ ብላቴ አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ቁጥራቸው ወደ ስልሳ በሚጠጋ አውቶቡሶች ተጭነው ደረሱ:: የሐይ ስኩል ጉዋደኛዬ ከፈለኝ መምጣቱን ከሰው ሰማሁ:: ከፈለኝ በጣም የቅርብ ጉዋደኛዬ ነው:: ከ ማትሪክ በሁዋላ እኔ ወደ ጅማ ስሄድ እሱ ጎንደር ሄደ- ሁለታችንም ሕክምና ለማጥናት:: በእርግጥ የጎንደር የህክምና ተማሪዎች የመጀመሪያ ዓመት ኮርሶቻቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚወስዱ በመሆኑ ከፈለኝ የመጣው ካዲሳበባ ነው:: ገና አላገኘሁትም:: እስካየው ቸኩያለሁ..

ዛሬ በወታደራዊው ደንብ መሰረት ስራችንን የጀመርነው ከሌሊቱ ፩፩ ሰዓት ነው:: ጠዋት ጠዋት አየር ወለዶቹ ዱብ ዱብ ያስብሉናል:: ለሰውነት ጥንካሬና  ወባን ለመከላከል ጥሩ ነው ይላሉ:: ባለፉት ቀናት ይጫጫነኝ የነበረው የቀን እንቅልፍ እየተወኝ ነው ስለው እንደገና ጀመረኝ :: ማቅለሽለሽም ነበረኝ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ትቶኛል::

መጋቢት ፪፬ ፩፱፰፫ አ.ም.
......................ትናንት ከፈለኝን ያለበት አንደኛ ብርጌድ ድረስ ሂጄ አገኘሁት:: 
እውነተኛውን የውትድርና ትምህርት ዛሬ ጀመርን:: የብዙ ተማሪዎች ከወታደራዊ ስነስርዓት ውጭ መሆን (የአንዳንዱ እንደውም ከሲቪል ስነስርዓትም ጭምር ውጭ መሆን) አየር ወለድ አሰልጣኞቻችንን ተፈታተናቸው: አስቆጣቸው! ዛሬ በምሳ ሰዓት አንዳንድ ተማሪዎች የራሳቸውን ቅርጥፍ አድርገው ከበሉ በሁዋላ እዚያው በቆረጣ ሰልፍ ይዘው እንደገና ወደ ሜንስ ቤቱ በመግባት በፈፀሙት የድጋሚ መብላት ድርጊት  (አፈር ይብሉና) ሌሎች ክፍላቸው ሆነው በስነሥርዓት ተራ ይጠብቁ የነበሩ ተማሪዎችን ሳይበሉ ለመዋል ዳረጋቸው:: ይህን ተከትሎ ከሰዓት በሁዋላ የኛ ብርጌድ አዛዥ የሆነው ሻምበል ኦልቀባ ለታ እጅግ በጣም በመበሳጨቱ ፎሌን ቆጠራ ላይ አንዳንድ ጠንካራና የንዴት ቃላት ሁላችንም ላይ አወረደብን:: በሁዋላ እንደሰማሁት በየብርጌዱ በተመሳሳይ ሁኔታ አየር ወለዶች በብስጭት ተማሪውን ሲናገሩ ና ሲጮሁበት ነበር አሉ:: ባለፈው እንዳልኩት በጫማ ጥፊና በርግጫ ቢሉን ደስ ባላቸው ግን ""ጫፋችንን እንዳይነኩ" ታዘዋል:: 

ንዴትና ብስጭት ሰፍኖበት የነበረው ከሰዓት ተጠናቆ ደንገዝገዝ ሲል እራት ደሞ በላን:: አሁን በሥርዓት ነበር የተበላው:: ግን እንጀራዋ አነሰች::

ጊዜያዊ መፀዳጃ ና ገላ መታጠቢያ ቤቶች ከእንጨት ባፋጣኝ እየተሰሩ ነው:: ይህም ለብላቴ አዲስ ነው:: ከዚህ በፊት ሰልጥነው የወጡት ወታደሮች በሙሉ የሚፀዳዱት ዙሪያቸውን ካለው ቆንጥርና ጫካ ውስጥ ሲሆን የሚታጠቡትም ወንዝ ውስጥ ነበር መሰለኝ:: የ ኮሌጅ ተማሪ ወታደር ግን "ሞልቃቃ" ነው:: 

በነገራችን ላይ ዛሬ ማታ ከራት በሁዋላ ወታደራዊ ትምህርት ነበረን:: አርእስቱ በጭለማ ስለማጥቃትና ስለመከላከል ሲሆን በገለፃ የታገዘ ነበር:: ገለፃ ስል ግን የውሸት አይደለም ሁሉም ነገር እውነተኛ ነበር:: ላውንቸር ሲተኮስ በቅርብ አየሁ:: በርካታ አብሪ ጥይቶች ተተኮሱ:: ፈንጂዎችም ፈነዱ:: ከየክፍላችን ተነስተን ወደገለፃው ስፍራ ስንሄድ የነበረው ጨለማ እጅግ በጣም ድቅድቅ ስለነበር እጅ ለጅ ተያይዘን ነበር የምንራመደው....