አርብ ለት - ስቅለት
ዕለቱ ስቅለት ነው:: ይህን ግዙፍ የክርስትያን አመትባል ከቤቴ ውጭ ለመጀመርያ ግዜ ማሳለፌ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ዉስጥ መሆኔን ሳስበው ዘገነነኝ::የዛሬ ዓመት ትዝ አለኝ:: ቤታችን: ሰፈሩ: መንደሩ: ሽታው: ሳሩ: ቅጠሉ: በሬው: በጉ ና ዶሮው: ጭሱ ሁሉ ትዝ አለኝ...ወይኔ...
ዛሬ ታይገር የተባለው የአየር ወለድ ሙዚቃ ባንድ ነው ሰልጣኝ ተማሪዎችን እንዲያስደስትና እንዲያዝናና የታዘዘው:: ያለ አዲስ ክስተት ና ያለብዙ ተመልካች ሙዚቃው ተከናወነ::
ሰልጣኝ ተማሪው በአጭር ግዜ በብላቴ ውስጥ ኑሮ ተሰላችቷል:: ለአየር ወለዶቹ የተማሪ መታዘዝ ሕልም ከሆነ ሰንብቷል:: በሜንስ ቤት: በሰልፍ ቦታ ላይ: በኬላዎች ና በ ሴት ሰልጣኝ ተማሪዎች መኖሪያ አካባቢ ያሉ አየር ወለዶች በተደጋጋሚ ከወንድ ተማሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ:: ሆኖም ምንም አይነት እርምጃ በተማሪ ላይ አይውስዱም:: እንደውም አንድ ጉዋደኛዬ እንደነገረኝ ስድስተኛ ብርጌድ ውስጥ አንድ የ መቶ አለቃ አየር ወለድ አንድ ተማሪ ሰልጣኝን ሊመታው እጁን ሲሰነዝር ሌሎች ተማሪዎች አንድላይ በመሆን መቶ አለቃውን ሊደበድቡት ነበር:: አንዳንድ መኝታ ክፍሎች ውስጥ "እንደውም ቶሎ ወደየቤታችን ይመልሱን" የሚለው ቃል እየተሰማ ነው::የአምስተኛ ብርጌድ አዛዥ የሆነው የ ሻምበስ ኦልቀባ ንዴት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ማበድ የቀረው ይመስላል:: ዘወትር ሲናገር በብስጭት ና እምባ እስከሚወጣው ድረስ ነው:: በቀደም ለት ሰልፍ ላይ: "እኔ እናንተ ከመጣችሁ ከሰውነቴ ክብደት ላይ አምስት ኪሎ ቀንሻለሁ" ብሎ ተናገረ:: ተማሪዎች በሆዳቸው: አንዳንዶቹም ፊት ለፊት ሳቁ::
ከምግብ እና ከምግብ እቃዎች ፅዳት ጉድለት የተነሳ በማሰልጠኛ ውስጥ ከባድ የሆነ አጣዳፊ ተቅማጥ ና የሆድ በሽታ በመዛመት ላይ ነው:: እኔም ራሴ ሳይዘኝ አይቀርም: የምፀዳዳው ጥሩ አይነት አይደለም:: አንዳንድ ተማሪዎች በጣም ስለሚያጣድፋቸው አንሶላ እንደ ሽርጥ አገልድመው ጫካው ና ቆንጥሩ አጠገብ ይውላሉ: ዳማ ወይም ካርታ እየተጫወቱ:: በዚህ ላይ ደሞ ትናንትና ለወባ መከላከያ ተብሎ ለተማሪው ሁሉ የታደለውን አራት አራት ክኒን የዋጡ አንዳንዶች ትውከትና ፌንት መውጣት ድረስ ሁሉ አጋጥሙዋቸው ስለነበር የማሰልጠኛው ሆስፒታል ተጨናንቆ ነው የዋለው:: እንደውም ያ መከረኛው ስድስተኛ ብርጌድ አካባቢ የሞተ ተማሪ አለ እየተባለ ይወራል:: ይህን ስሰማ ፈራሁ-ብሞትስ? ብዬ:: አስቤው የማላውቅ ነገር ነው:: ደግነቱ የወባ መከላከያውን ክኒን አልዋጥኩትም::
ከሙዚቃው ዝግጅት በሁዋላ ስድስተኛ ብርጌድ ያለው ጉዋደኛዬ ከፈለኝ ጋ ሂጄ ነበር:: ከፈለኝ ከኔ በሁዋላ የመጣ ቢሆንም ከኔ የባሰ ደግሞ ነገር አለሙ ስልችት ብሎት ፊቱ ላይ የድካምና የቸልተኝነት እንዲሁም የመብሸቅ ሁኔታ ይነበብበታል:: ክፈለኝ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ተማሪ ተመሳስይ አይነት ስሜት ውጥ ነው ያለው:: ቶሎ ወደየ ቤታችን ይመልሱን እያለ ያወራል..
ከከፈለኝ በሁዋላ ምሽቱ ላይ አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ተማሪዎች ተሰባስበው ስቅለትን ወድሚያከብሩበት የኬስፓን አዳራሽ ሄድኩ:: ፀሎትና ቅዳሴ በረዣዥሙ ነበር:: ዝግጅቱ ከምሽቱ ፯ ሰዓት ተጠናቀቀ.....
No comments:
Post a Comment