Saturday, November 22, 2014

ሁለተኛ ግንዛቤ

ህዳር ቀን ፩፱፰፬ ..

ሁለተኛ ግንዛቤ

ባለፉት ቀናት የሚድ ሴሚስተር ፈተና ውጤቶቻችንን አወቅን:: በኔ በኩል ከሂሳብ በስተቀር ውጤቶቼ በሙሉ ደካማ ነበሩ:: የጠበኩት ቢሆንም እውነት ሆኖ ሳየው ደነገጥኩ:: ብዙ ሌሎች ተማሪዎች በልጠውኛል:: ከሐይ ስኩል; በሁዋላ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥመኝ የመጀመሪያው ነበር: ማለቴ በትምህርት በሌሎች ብዙ ተማሪዎች መበለጥ::መንፈሴ ሲጎዳ ተሰማኝ:: ሂሳብ ሃምሳ ጥያቄ አርባ ስድስቱን በትክክል በመመለስ የኔ ውጤት ከፍተኛው ሳይሆን አይቀርም::  ሂሳብ መምህራችን ተስፋ ልደት ቢሮው አስጠርቶ “አንቺ ኮ አንበሳ ነሽ” ሲለኝ ማመን አልቻልኩም:: ምን ዋጋ አለው በሌሎቹ ውጤቶች የተጎዳውን ስሜቴን ሊጠግነው አልቻለም:: የጠቅላላ ፈተና ዉጤቴን ካወኩ በሁዋላ ድብርት በተከተሉት ቀናት እየተጫጫነኝ መጣ:: ለማንበብም ሆነ ለመፃፍ ያለኝ ሞራል ከበፊቱ የበለጠ ዝቅ አለ:: አንዳንዶቹን መምህራን ማየት ሁሉ አስጠላኝ:: ትንሽም ቢሆን ላቦራቶሪ ስንሄድ ይሻለኛል:: ምናልባት ላቦራቶሪ ውስጥ ከንባብ ከማዳመጥ ይልቅ ድርጊት ስለሚበዛ ይሆናል:: ሆኖም የያዘኝ ድብርት እየጠነከረ መጥቶ ለምንም ነገር ዝግጁ አለመሆን ደረጃ ላይ ደረስኩ::

ዛሬ አንድ ሃሳብ መጣልኝ:: ቤተሰብ ጋር ለጥቂት ቀናት ቆይቼ ለመመለስ አሰብኩ:: በእውነቱ የቤተሰብ ናፍቆት የለብኝብም ግን ከዚህ አካባቢ ለሁለት ለሶስት ቀንም ቢሆን መራቅ ድብርቴን ያሽለው ይሆናል ብዬ አሰብኩ::ይህን እፁብ ድንቅ የሆነ ሃሳብ ለማመንጨት በመቻሌ ራሴን ከፍ ከፍ አደረኩት:: ስር ከሰደደ ችግር የተወለደ ሃሳብ:: ችግሩ ግን ሃባ ሳንቲም በኪሴ የለም:: የቤተሰባችን ሁኔታ ባለፈው እንደገለፅኩት ምናልባትም ከኔ የባሰ ስለነበር ባሁኑ ሰዓትገንዘብ አይልኩልኝም:: ከተጨማሪ ማሰብ ወደተግባርም ከመሰማራት በሁዋላ ገንዘብ የሚያበድረኝ ሰው አገኘሁ-አባይነህ! ዛሬ ከሰዓት አውቶቡስ ተራ ትኬት ለማስቆረጥ: እሄዳለሁ:: ከቀናኝና ከተገኘ ነገ ለመሄድ ማለት ነው:: ለቤተሰብ እመጣለሁ ብዬ አልተናገርኩም:: እንደምሄድ ከአበዳሪዬ አባይነህና ከሰፈሬ ልጅ ታጠቅ በስተቀር ማንም አያውቅም:: እቤት ድንገት ከተፍ ስል ቤተሰብ ምን ይል ይሆን ብዬ አሰብኩ: ያው ይደነግጣሉ:: የተባረርኩ ሊመስላቸው ይችላል:: ይህን እንደሚያስቡ ሳስብ አንገቴን አመመኝ::

ከሰዓት በሁዋላ .........
ጅማ አውቶቡስ ተራ ደረስኩ:: በእውነቱ እዚህ አካባቢ ተገኝቼ የማውቀው ከዚህ በፊት አራት ግዜያት ብቻ ነው:: እነሱም ለመጀመሪያ ግዜ ስመጣ: ዓመቱ አጋማሽ ላይ ለእረፍት ስሄድና ስመጣ እንዲሁም ከሁለት ወራት በፊት ትምህርት ለመቀጠል ስመጣ ናቸው:: ሁሌም ቢሆን አውቶቡስ ተራ ውስጥ ብዙም የመቆየትና ቦታውን የማስተዋል ዕድል አጋጥሞኝ አያውቅም:: በዚያ ላይ ከዚህ በፊት ስሄድም ሆነ ስመጣ ከጉዋደኞቼ ከሌሎች ተማሪዎች ስለነበር በራሳችን ጨዋታ ተመስጠን አውቶቡስ ተራውን አናስተውለውም ነበር:: ዛሬ ግን ብቻዬን በግላጭ ተገኝቼ በጠራራ ፀሐይ አስተዋልኩት- አውቶቡስ ተራውን:: እውነትም በጣም ተራ ነው... ተራ ሰው ይርመሰመሳል...ተራ አውቶቡሶች ራስ የሚያዞሩ ጭሶቻቸውን እያቡለቀለቁ ይወጣሉ ይገባሉ:: ዕቃ ጫኝ ቀን በሎች አውቶቡሶቹ ላይ ዕቃ ይጭናሉ ያወርዳሉም:: በዚያ ራስ በሚመታ ፀሐይ ላባቸው እየተንተፈጠፈ ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ:: ብቻ በለት ተለት ኑሮዬ የማላየው አይነት ግርግር አየሁ:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም በድንገት ፍርሃት ፍርሃት አለኝ:: በአንድ ግዜ ብዙ ሃሳብ በአምሮዬ በተዘበራረቀ ሁኔታ ተመላለሰ:: ሃይ ስኩልን አስታወስኩ:: ሰፈራችን ውስጥ ትምህርታቸውን የሙጥኝ ብለው ሲከታተሉ ከነበሩ በጣም ጥቂት ልጆች ውስጥ አንዱ እንደነበርኩ አስታወስኩ:: የማትሪክ ፈተና ተሳክቶልኝ ወደፊት እንድራመድም ሌተ ቀን ስፅልይ እንደነበር ታወሰኝ:: የማትሪክ ፈተና ውጤት ተለቁዋል የሚል ወሬ በስማበለው ሰምቼ ከኮልፌ ትምህርት ቤቴ እስከሚገኝበት አዲስ ከተማ ድረስ ከጉዋደኞቼ ጋር በሩጫ የገሰገስነው ባይኔ መጣብኝ:: ሁሉ እንግዲህ እዚህ አሁን ያለሁበት ደረጃ ላይ ለመድረስም አልነበር? አሁን ያለሁበትን ደረጃ ግን በሚገባ መርገጥ እየቻልኩ በቸልተኘነት በትክክል ባለመርገጤ አንገዳገደኝ....አውቶቡስ ተራውን እንደገና በአይኔ ሙሉ አማተርኩት:: ከቀን በሎቹ በተጨማሪ የለበሱት የነተበና ብዙ ከመለበስ የተነሳ የቆሸሸ ወንዶች ልጆች ግማሾቹ ተቀምጠው ግማሾቹም ቆመው ሲንቀሳቀሱ ተመለከትኩ:: ግ ይዘው የተጋደሙም አሉ:: ቤት የሌላቸው በረንዳ የሚያድሩ እንደሚሆኑ አልተጠራጠርኩም.......እኔ እንግዲህ ደበረኝ ብዬ ወደቤት ለመሄድ የአውቶቡስ ትኬት ለማስቆረጥ እዚህ ቦታ ላይ ተገኝቻለሁ... በዚያው ቅፅበት ወደ ጤና ሳይንሱ ግቢ በፍጥነት መመለስ አማረኝ:: ጤና ሳይንሱ እንዳለ አሰኘኝ:: አውቶቡስ ተራው በር እላዬ ላይ የሚዘጋብኝ ይመስልስል እዚያ መቆየት አልፈለኩም:: በሩጫ መውጣት ፈለኩ:: ወደቤት ለመሄድ በማሰቤም ሆን በመገፋፋቴ ፀፀት ብጤ ዳሰሰኝ:: በውይይት ታክሲ ወደ ጤና ሳይንሱ ሸመጠጥኩ:: በምሽቱ ሳይኮሎጂ መምህራችን ፩፪ ሰዓት ተኩል ጀምሮ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል የሰጠውን ሌክቸር በጥሞናና ባፍቅሮት እንዲሁም በአክብሮት ተከታተልኩ........

Thursday, November 13, 2014

ሚድ ሴሚስተርና የአብይ ማስታወሻ


ጥቅምት ሃያ ሁለት አስራዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.

ሚድ ሴሚስተርና የአብይ ማስታወሻ
ከጥቅምት 18 እስከ 22 ባሉት ቀናት ውስጥ የ ግማሽ ሴሚስተር ፈተናዎቻችንን ወሰድን:: በእንግሊዝኛ ተጀምሮ : በኦርጋኒክ ኬሚስትሪ: ሳይኮሎጂ: ሶሺዮሎጂ :ፊዚክስ ና ማትስ ተከትሎ በ ባዮሎጂ ተጠናቀቀ:: እንግሊዝኛና ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ ሁለቱም ከብደውኝ የነበረ ሲሆን: ሳይኮሎጂ ደግሞ ስለምወደውና በደንብ ስላነበብኩም ነው መሰል ቀሎኝ ነበር:: ፊዚክስ የጠበኩትን ያህል አልከበደኝም:: ሶሺዮሎጂ ግን የማልወደው ትምህርት ከመሆኑም ሌላ ፈተናውንም በሚገባ እንደማልወጣው አስቀድሜ ስለደመደምኩ ግዜ ሳላባክን በፍጥነት ነው ከፈተናው ከፍል የወጣሁት:: ጉዋደኞቼ ሳይገርማቸው አይቀርም::  በነገራችን ላይ በሚድ ሴሚስተር ፈተና ቀናት መሃል አንድ ምሽት የአንደኛ ሴሚስተር ውጤት ወረቀቴን ባጋጣሚ መፃሕፍ ቅዱሴን ስገልጥ አየሁት:: በጣም ማስደሰት ብቻ ሳይሆን ልክ የሌላ ሰው የሆነ ያህል አስቀናኝ:: እንደገና ደግሜ እንደማላመጣው ተሰምቶኝ ይሆናል:: 3.84 ይላል አጠቃላይ ነጥቡ.....ባጠቃላይ ስለ ሚድ ሴሚስተር ፈተና ጥሩ ስሜት አልተሰማኝም:: በደንብ አልሰራሁም:: ቢሆንም ባይሆን ብዬ ለዋናው የሴሚስተር ፈተና በርትቼ ለማጥናት በሚስጥር ለራሴ ቃል ገባሁ:: 

ባዮሎጂ ፈተናችንን የወሰድን እለት ከ ቀርብ ጉዋደኞቼ አንዱ የሆነው አብይ በጠየኩት መሰረት አጀንዳዬ ላይ የሚከተለውን ፅሁፍ አሰፈረ..


መጀመሪያ ብዕሬን በግል ማስታወሻህ ላይ እንድፈትን ዕድል ስለተሰጠኝ በጣም እግዜር ይስጥልኝ:: ስዎች ከራሳቸው አፍልቀው በሚፅፉት ከገፆች አልፈው ወደ መፅሐፍት ሲሸጋገሩ መስማት እጅግ በጣም ያስደንቀኛል::  በእውነቱ
እኔ እቺን ገፅ እንኩዋን ለመሙላት በጣም ነው የማንገራግረው::

ራሴን ሳላስተዋውቅ: ብዙ ያወራሁ መሰለኝ:: አብይ ሕሩይ እባላለሁ:: ትውልዴ አዲስ አበባ ከፍተኛ 11 ቀበሌ 02 በተለምዶ ስሙ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው:: ጅማን መዋያ ማደሪያዬ ያደረኩት የካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን ወክለው ወደ ጅጤሳ ከመጡት “the magnificent three” ጋር ከመስከረም ፩፮ ፩፱፰፫ ጀምሮ ነው::

ስለራሴ ይህን ካስተዋወኩዋችሁ ዘንዳ አሁን ሰዓቱ ከምሽቱ ፮ መሆኑን ልንግራችሁ እወዳለሁ:: ዛሬ ፍፁም ነፃነት ተሰምቶኝ ነው የዋልኩት:: የ mid-semester ፈተናዎች ማሳረጊያ የሆነው ባዮሎጂን ጨርሰን በምሽቱ የቪዲዮ ትርኢት Police Academy የተባለውን አዝናኝ ፊልም ስመለከት ነው ያመሸሁት:: በእውነቱ ከሆነ ከፊልም አፍቃሪዎች መሃከል አንዱ ነኝ:: አላዘውትር እንጂ ፈተና በደረሰበት ሰሞን እንኩዋን ገብቼ ማየት የፊልም ፍላጎቴን ያረካልኛል:: የዛሬውን ምሽት show ለየት ያደረገው በቪዲዮ ማሳያው አዳራሽ በኩል ሲያልፉ እንኩዋን የሚሰቀጥጣቸው ሴቶች እህቶቻችን ሁለት ወንበር ለመጋራት መብቃታቸው ነው::


ነገ እሁድ ነው:: ጥሩ መደበሪያ ቦታ እንደሚያስፈልገኝ በማውጠንጠን ላይ ነኝ:: እንዲያውም አንድ በጣም የልብ ጉዋደኛዬ የሆነ ከአዲስ አበባ የመጣ ወዳጄን ጅጤሳን የማስጎብኘት ሃሳቡ መጥቶልኛል:: በዚሁ እሰናበታለሁ::

Sunday, November 9, 2014

ፈገግታ

በብሩህ አይኖች እይታ 
በአእምሮ ትእዛዝ ይሁንታ 
በጥርስ ድምቀት ሰጭነት 
በጉንጭ ቅላት ፍካት 
በከንፈር ስፋት ጥበት 
በዉፍረትና በቅጥነት
በአይን ዳርቻ መሸብሸብ
ገፅ በደስታ ሲከበብ 
ለተመልካች እይታ መስህብ 
እንደአበባ መአዛ: እንደ አበባ  ልዩ ሽታ 
እንደነፋስ ሽውታ: እንደፀሃይ ብልጭታ 
ፈገግታ!

ክፉን ከደግ: ሴትን ከወንድ 
ጨዋን ከሌባ: ጤነኛን ከእብድ
የረጋውን ከችኩል: አመለቢሱን ካመለኛው
ኡ ኡ ባዩን ከቀማኛው ከዘራፊው 
'ምታግባባ በአንዲት ቅፅበት እይታ 
ለልብ ለጋሽ እርጋታ...
ፈገግታ!

ሰውን የማክበር ምልክቱ: የባልንጀርነት ስሜቱ
የመውደድ ማፍቀር ማስረጃው: የታማኝነት መግለጫው
የንፁህ ልቦና ምስክሩ: የአዲስ ፍቅር ጅምሩ
የወዳጅነት መለያው: የሂወት ምግብ ማጣፈጫው
ፈገግታ...እንደአበባ ልዩ ሽታ: እንደነፋስ ሽውታ 
ለህሊና ሰጭ እርካታ: ከልብ ደራሽ ባንዳፍታ 
የደስታ ምንጭ ያላት መስህብ
ፈገግታ የሂወት ምግብ
ፈገግታ!

በር ይከፈት በፈገግታ 
ለእንግዳ ረዥም ቆይታ 
ለመስተንግዶው ድምቀት ማማር
ለእንግዳ ምቾት ለመፍጠር
ከምግብ መጠጥ በፊት ለማስታወሻ ለትዝታ
ይቅረብ ከልብ እንደልብ : ያልተሰሰተ ፈገግታ 
ፈገግታ!

ሰላም እንደምን አለህ: ሰላም እንደምን አለሽ 
እንደምን አሉልኝ አብዬ: ደህና ውለዋል እማምዬ
እንደምንድኖት ጌታዬ
ሰላም ዋላችሁ ጉዋደኞቼ
በጣም ደህና ነኝ ቤቶቼ
ባልንበት ሁሉ ለሰላምታ 
ይቅደመን ከልብ ፈገግታ!
ፈገግታ!

እግዜር ይስጥልኝ: ጌታ ይባርክህ
ብዙ ያኑርህ ያሳድግህ 
አመስግናለሁ አባትዬ 
መርቄሻለሁ እህትዬ 
ለተቀባይ ዋጋ የለው
ፈገግታዎ ከተለየው 
ለፈገግታ ይኑሩ: በፈገግታም ይናገሩ
መከራ ፊትዎን ይሰውሩ 

ፈገግታ...


መጋቢት 1982 አ.ም. የተፃፈ - በ ሳምሶን ኃይሌ:: ሃሳቡ እንዳለ ቢሆንም ያፃፃፍ ለውጥ ተደርጎበታል:: ከመጀመሪያው ግጥም የሄኛው በመጠን ያንሳል:: የመጀመሪያው ግጥም  ግንቦት 1982 አ.ም. በአዲስ ከተማ  ትምህርት ቤት በተደረገ  የተማሪዎች የግጥም ውድድር ላይ ቀርቦ ሶስተኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቡዋል::