ህዳር ፲ ቀን ፩፱፰፬ አ.ም.
ሁለተኛ ግንዛቤ
ባለፉት ቀናት የሚድ ሴሚስተር ፈተና ውጤቶቻችንን አወቅን:: በኔ በኩል ከሂሳብ በስተቀር ውጤቶቼ በሙሉ ደካማ ነበሩ:: የጠበኩት ቢሆንም እውነት ሆኖ ሳየው ደነገጥኩ:: ብዙ ሌሎች ተማሪዎች በልጠውኛል:: ከሐይ ስኩል; በሁዋላ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥመኝ የመጀመሪያው ነበር: ማለቴ በትምህርት በሌሎች ብዙ ተማሪዎች መበለጥ::መንፈሴ ሲጎዳ ተሰማኝ:: ሂሳብ ከ ሃምሳ ጥያቄ አርባ ስድስቱን በትክክል በመመለስ የኔ ውጤት ከፍተኛው ሳይሆን አይቀርም:: ሂሳብ መምህራችን ተስፋ ልደት ቢሮው አስጠርቶ “አንቺ ኮ አንበሳ ነሽ” ሲለኝ
ማመን አልቻልኩም:: ምን ዋጋ አለው በሌሎቹ ውጤቶች የተጎዳውን ስሜቴን ሊጠግነው አልቻለም:: የጠቅላላ ፈተና ዉጤቴን ካወኩ በሁዋላ ድብርት በተከተሉት ቀናት እየተጫጫነኝ መጣ:: ለማንበብም ሆነ ለመፃፍ ያለኝ ሞራል ከበፊቱ የበለጠ ዝቅ አለ:: አንዳንዶቹን መምህራን ማየት ሁሉ አስጠላኝ:: ትንሽም ቢሆን ላቦራቶሪ ስንሄድ ይሻለኛል:: ምናልባት ላቦራቶሪ ውስጥ ከንባብ ና ከማዳመጥ ይልቅ ድርጊት ስለሚበዛ ይሆናል:: ሆኖም የያዘኝ ድብርት እየጠነከረ መጥቶ ለምንም ነገር ዝግጁ አለመሆን ደረጃ ላይ ደረስኩ::
ዛሬ አንድ ሃሳብ መጣልኝ:: ቤተሰብ ጋር ለጥቂት ቀናት ቆይቼ ለመመለስ አሰብኩ:: በእውነቱ የቤተሰብ ናፍቆት የለብኝብም ግን ከዚህ አካባቢ ለሁለት ለሶስት ቀንም ቢሆን መራቅ ድብርቴን ያሽለው ይሆናል ብዬ አሰብኩ::ይህን እፁብ ድንቅ የሆነ ሃሳብ ለማመንጨት በመቻሌ ራሴን ከፍ ከፍ አደረኩት:: ስር ከሰደደ ችግር የተወለደ ሃሳብ:: ችግሩ ግን ሃባ ሳንቲም በኪሴ የለም:: የቤተሰባችን ሁኔታ ባለፈው እንደገለፅኩት ምናልባትም ከኔ የባሰ ስለነበር ባሁኑ ሰዓትገንዘብ አይልኩልኝም:: ከተጨማሪ ማሰብ ና ወደተግባርም ከመሰማራት በሁዋላ ገንዘብ የሚያበድረኝ ሰው አገኘሁ-አባይነህ! ዛሬ ከሰዓት አውቶቡስ ተራ ትኬት ለማስቆረጥ: እሄዳለሁ:: ከቀናኝና ከተገኘ ነገ ለመሄድ ማለት ነው:: ለቤተሰብ እመጣለሁ ብዬ አልተናገርኩም:: እንደምሄድ ከአበዳሪዬ አባይነህና ከሰፈሬ ልጅ ታጠቅ በስተቀር ማንም አያውቅም:: እቤት ድንገት ከተፍ ስል ቤተሰብ ምን ይል ይሆን ብዬ አሰብኩ: ያው ይደነግጣሉ:: የተባረርኩ ሊመስላቸው ይችላል:: ይህን እንደሚያስቡ ሳስብ አንገቴን አመመኝ::
ከሰዓት በሁዋላ .........
ጅማ አውቶቡስ ተራ ደረስኩ:: በእውነቱ እዚህ አካባቢ ተገኝቼ የማውቀው ከዚህ በፊት አራት ግዜያት ብቻ ነው:: እነሱም ለመጀመሪያ ግዜ ስመጣ: ዓመቱ አጋማሽ ላይ ለእረፍት ስሄድና ስመጣ እንዲሁም ከሁለት ወራት በፊት ትምህርት ለመቀጠል ስመጣ ናቸው:: ሁሌም ቢሆን አውቶቡስ ተራ ውስጥ ብዙም የመቆየትና ቦታውን የማስተዋል ዕድል አጋጥሞኝ አያውቅም:: በዚያ ላይ ከዚህ በፊት ስሄድም ሆነ ስመጣ ከጉዋደኞቼ ና ከሌሎች ተማሪዎች ጋ ስለነበር በራሳችን ጨዋታ ተመስጠን አውቶቡስ ተራውን አናስተውለውም ነበር:: ዛሬ ግን ብቻዬን በግላጭ ተገኝቼ በጠራራ ፀሐይ አስተዋልኩት- አውቶቡስ ተራውን:: እውነትም በጣም ተራ ነው... ተራ ሰው ይርመሰመሳል...ተራ አውቶቡሶች ራስ የሚያዞሩ ጭሶቻቸውን እያቡለቀለቁ ይወጣሉ ይገባሉ:: ዕቃ ጫኝ ቀን በሎች አውቶቡሶቹ ላይ ዕቃ ይጭናሉ ያወርዳሉም:: በዚያ ራስ በሚመታ ፀሐይ ላባቸው እየተንተፈጠፈ ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ:: ብቻ በለት ተለት ኑሮዬ የማላየው አይነት ግርግር አየሁ:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም በድንገት ፍርሃት ፍርሃት አለኝ:: በአንድ ግዜ ብዙ ሃሳብ በአምሮዬ በተዘበራረቀ ሁኔታ ተመላለሰ:: ሃይ ስኩልን አስታወስኩ:: ሰፈራችን ውስጥ ትምህርታቸውን የሙጥኝ ብለው ሲከታተሉ ከነበሩ በጣም ጥቂት ልጆች ውስጥ አንዱ እንደነበርኩ አስታወስኩ:: የማትሪክ ፈተና ተሳክቶልኝ ወደፊት እንድራመድም ሌተ ቀን ስፅልይ እንደነበር ታወሰኝ:: የማትሪክ ፈተና ውጤት ተለቁዋል የሚል ወሬ በስማበለው ሰምቼ ከኮልፌ ትምህርት ቤቴ እስከሚገኝበት አዲስ ከተማ ድረስ ከጉዋደኞቼ ጋር በሩጫ የገሰገስነው ባይኔ መጣብኝ:: ያ ሁሉ እንግዲህ እዚህ አሁን ያለሁበት ደረጃ ላይ ለመድረስም አልነበር? አሁን ያለሁበትን ደረጃ ግን በሚገባ መርገጥ እየቻልኩ በቸልተኘነት በትክክል ባለመርገጤ አንገዳገደኝ....አውቶቡስ ተራውን እንደገና በአይኔ ሙሉ አማተርኩት:: ከቀን በሎቹ በተጨማሪ የለበሱት የነተበና ብዙ ከመለበስ የተነሳ የቆሸሸ ወንዶች ልጆች ግማሾቹ ተቀምጠው ግማሾቹም ቆመው ሲንቀሳቀሱ ተመለከትኩ:: ጥግ ይዘው የተጋደሙም አሉ:: ቤት የሌላቸው ና በረንዳ የሚያድሩ እንደሚሆኑ አልተጠራጠርኩም.......እኔ እንግዲህ ደበረኝ ብዬ ወደቤት ለመሄድ የአውቶቡስ ትኬት ለማስቆረጥ እዚህ ቦታ ላይ ተገኝቻለሁ... በዚያው ቅፅበት ወደ ጤና ሳይንሱ ግቢ በፍጥነት መመለስ አማረኝ:: ጤና ሳይንሱ እንዳለ አሰኘኝ:: አውቶቡስ ተራው በር እላዬ ላይ የሚዘጋብኝ ይመስልስል እዚያ መቆየት አልፈለኩም:: በሩጫ መውጣት ፈለኩ:: ወደቤት ለመሄድ በማሰቤም ሆን በመገፋፋቴ ፀፀት ብጤ ዳሰሰኝ:: በውይይት ታክሲ ወደ ጤና ሳይንሱ ሸመጠጥኩ:: በምሽቱ ሳይኮሎጂ መምህራችን ከ ፩፪ ሰዓት ተኩል ጀምሮ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል የሰጠውን ሌክቸር በጥሞናና ባፍቅሮት እንዲሁም በአክብሮት ተከታተልኩ........