ግንቦት መጀመሪያ 1985 አ.ም.
ከመጋቢት 7 አስከ ሚያዚያ አጋማሽ አዲሳበባ በተሰቦቼ ጋር ያሳለፍኩትን አረፍት አጠናቅቄ ወደ ዉዷ ጅጤሳ ተመለስኩ:: የሶስተኛ አመት ትምህርቴንም ጀመርኩ::
አጠቃላይ በሆነ እይታ የዚህን
አመት ጅምር ብዙም ደስ የሚል ወይም የሚስብ ነገር አጣሁበት:: ዓመቱ ስሙ PC-2 (ፒሲ ቱ) ይባላል:: ትምህርቶቹ በአይነትና በብዛት ከፒሲ-ዋን ትምህርቶች የሚልቁ ሲሆን በርካታ ከህክምና ጋር በቀጥታ እንዴት አንደሚገናኝኙ ያልገቡኝ ትምህርቶችንም ያካትታል:: ከህክምና ጋር በቀጥታ የሚገናኙትና በግብፆች የሚሰጡን እንደነፓቶሎጂና ፋርማኮሎጂ ያሉት የሚስቡ ቢሆንም ተነበው ለመታወስ ሃይልና ጥረት የሚጠይቁ ይመስላል:: ባለፈው እራሴን ለመግለጽ አንደሞከርኩት የንባብ ሀይልና ጥረት አኔ ዘንድ ያሉ ነገሮች አይደሉም::
ከላይ ከህክምና ጋር የማይገናኙ ያልኩዋቸውን ትምህርቶች የሚያስተምሩን መምህራን በሙሉ አበሾት ሲሆኑ ሀኪም አለመሆን ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ አጅግ በጣም በርካታ ሃሳቦችን በበርካታ ትራንስፓረንት ሺቶች ላይ አስፍረው ነው ወደ ሌክቸር ሆል የሚመጡት:: ወደ ክፍሉ እንደገቡ የትራንስፓረንት ሺት ማስቀመጫ ፕሮጀክተር ላይ የመጀመሪያውን ሺት ያኖሩና ጽሁፉ ከሚንጸባረቅበት ነጭ ጨርቅ ላይ አይናቸውን ተክለው እንዲሁም በከፊል ለኛ
ለታዳሚዎቹ ጀርባቸውን ሰጥተው መናገር ይጀምራሉ:: ከዚያም አንዱን ትራንስፓረንት ሺት ሲያነሱና ሌላኛውን ሲያስቀምጡ ብሎም ሲናገሩ ቆይተው ክፍሉን ለቀው ይወጣሉ:: የዚህ ኣይነቱ ሂደት ድምር ውጤት ትምህርት ነው ለማለት ይክብደኛል:: ይልቅስ አኔና ሌሎች ብዙ የ ፒሲ-ቱ ተማሪዎችን ሰነፍ: የደነዘዝንና: የትምህርት ጥላቻ ያለን እንድንሆን አየገፋፋን ነው:: እውነት ለመናገር ሁላችንም እጅግ ከባድ የሚባለውን ፒሲዋንን አልፈን የመጣን ስለሆንን ፒሲ-ቱ ላይ ዘና ማለት እንጂ መጨነቅ ምናምን ገለ-መለ አንፈልግም:: እነዚህ ህክምና አልቦ ትምህርቶች ሲታከሉ ደግሞ የሚሆነውን ለማሰብ አይከብድም:: አኔና ጓደኞቼ እንደዚህ አይነት ትምህርቶች የሚሰጡበት ክፍለ ግዜ ላይ ክፍል አካባቢ አለመገኘትን እንደ ፋሽን ከያዝነው ቆየን....
ግንቦት 14 ቀን 1985 አ.ም.
ምናብ
ዛሬ ለምን አንደሆነ በቅጡ ባይገባኝም ከወትሮው እጅግ በተለየ ሁኔታ በዝምታ ነው የዋልኩት:: በቃ ዝም ማለት አማረኝ:: ከሰዎች ጋር ከመነጋገር ይልቅ በውስጤ የማስበውን ሀሳብ ማስታመም ፈልግሁ:: ይህ መቼም ከባድ ነው:: ምክንያቱም ሰዎች በውስጤ የማስበውን ስለማይረዱ መንገድ ላይም ሆነ ሌላ ቦታ ስንገናኝ በማነጋገር የብቸኝነቴን አጥር በርቅሰው ይገባሉ:: ዝም ማለት የፈግሁበትን ምክንያት ጠረጠርኩ: ምናልባት ኪሴ ባዶ በመሆኑ ይሆናል:: ይህ ግን በተደጋጋሚ እንደውም ያለማቁዋረጥ የሚከሰት ስለሆነ አንዴት ዝም ያስብለኛል? አንግዲህ የእጦት መደጋገም: ማድረግ አለመቻልን በማሳሰብ ልቤን አስከፍቶት ይሆናል:: አውነቱን ለመናገር ባሁኑ ሰኣት የመግዛት አቅሜ እሮብና ቅዳሜ ለጫማ ማስጠረጊያ ከማውላቸው ሁለት የምሳ ላይ ዳቦዎች የዘለለ አይደለም፥:: ባያሳፍርም ቅስም ያጣምማል:: በቃ በረዥሙ ከፋኝ:: የመኖር ጉጉቴ ባይቀንስም አንዳንድ ትምህርት ነክ ነገሮችን ለመስራት የሚያስችል ጉልበት ኣጣሁ::ተፈጥሮኣዊ ባህሪዬ የነበረው ሌክቸር ማዳመጥ ራሱ ሃይል የሚጠይቅ ሆነብኝ:: መጻፍማ አይታሰብም:: ብቻ ባጠቃላይ አእምሮዬ ንቃት ሰውነቴ ደግሞ ብርታት ጎደለው:: ተደጋጋሚ
የኪስ ባዶነት በፈጠረው መከፋት የተነሳ::ግን አኔ ብቻ ነኝ አንዴ ኪሰ ባዶ የሆነ? ኣይመስለኝም:: ክርስትያን አንደመሆኔ መጠን በእግዚኣብሄር ተስፋ ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ ባውቅም ይህን ስሜት ግን አሁን ልቀዳጀው አልቻልኩም:: አንዳውም መንፈሳዊ ሁኔታ ከልቤ ጭራሽ ጠፋ:: አሁን አኔ የማስበው የዚህን ኣለም ተጨባጭ ሁኔታ አንጂ በእግዚኣብሄር አንድ ነገር ይሆናል የሚል ነገር አይደለም:: ወይኔ ተስፋ ቆረጥኩ ማለት ነው? ወደፊቱ ጨልሞ ታየኝ ማለት ነው? እኮ ኪስ ባዶ በመሆኑ ምክንያት?......ሳልሳሳት አልቀርም:: ልክ ነው አምነት ትዕግስትና ተስፋ ያስፈልገኛል .......
No comments:
Post a Comment