ነሐሴ 1985 አ.ም.
ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በተዘጋጀሁበት
ዋዜማ ምሽት በጅማ ሰማይ ላይ ታንፅባርቅ የነበረችውን ግማሽ ጨረቃ ምን ግዜም አልረሳትም:: ያይኔ ምግብ የሆነች የማታስከፍል
ቆንጆ ድፍን ቀይ ጨረቃ..... ለምን እንደሆነ ባላውቅም ከዚህ ትውስታ ጋር ተያይዞ ያሳለፍኩት የሶስተኛ ዓመት የመጀመሪያው
ሴሚስተር ጉዞ ውልብ ሲልብኝ በዚህ ውስጥ ደግም እመቤትን አስታወስኩ:: እመቤት አዲስ አበባ ዮሐንስ ቤተክርስትያን አካባቢ
ያፈራት መልካም ሴት:: እመቤት ባለፈው ሴሚስተር ከመቼውም ግዜ በላቀ ከኔ: ከአብይና ከመንጌ ጋር: ቅርርብ ጨምራለች:: ብዙ
ጊዜ እኛ ወደተሰበሰብንበት ትመጣና በደስታና በሳቅ ትቀላቀላለች:: በቃ ከኛ ጋር መሆን እየተመቻት እንደመጣ መገመት
አያዳግትም:: ከተቀላቀለችን በሁዋላ እንደልቧ ታወራለች: ትስቃለች: ትጫወታለች: መራር የሆኑ ቀልዶቻችንን ትቃለዳለች:: አልፎ
አልፎም ሚስጥር ታጫውተናለች:: የአብይና መንጌን አላውቅም እኔ ግን ከአህቶቼ በስትቀር ከተቃራኒ ፆታ ጋር አብሮ መዋል መጫወት
ስላለመድኩ ነገሩ አዲስ ሆኖብኛል:: ይህን የምለው ግን ሁኔታው ለኔም እንደተመቸኝ ሳልክድ ነው::
ነሐሴ 19 ቀን ጅማን ለቅቄና ባውቶቡስ ተፈናጥጬ አዲስ አበባ ቤቴ ደንገዝገዝ ሲል
ደረስኩ:: አዲስ አበባ በሚሰነፍጥ ቀዝቃዛ አየር ተቀበለችኝ:: እዚህ አሁንም ድረስ ጠዋቱን ሙሉ ይዘንባል:: ከሰዓት ደግሞ
ደነናማ ሆኖ በጣም ይቀዘቅዛል:: ውስጥንም ያቀዘቅዛል:: በነገራችን ላይ በዚህ የእረፍት ግዜ ግጥም ለመፃፍ እቅድ አለኝ::
ጳጉሜ 1985 አ.ም.
እነሆ 1985 ሊፈፀም የቀሩት ጥቂት ቀናት
ናቸው:: ከዚያ በሁዋዋላ ያበሻው ፀደይ ወር መስከረም ብቅ ይላል:: መስከረምን በእውነት በጣም እወደዋለሁ:: ልጅነቴን
የሚያስታውሰኝ ወር ነው:: አደይ አባባን ያስታውሰኛል:: ኩልል ያለ ውሃ የሚፈልቅባቸው ምንጮችንም ያስታውሰኛል:: ሰፈሩ
መንደሩ ሁሉ አረንጉዋዴ መሆኑንም አይዘነጋኝም:: ከጉዋደኞቼ ጋር ሆነን በቀለም
አይነትና በቁጥር የበዙ ቢራቢሮዎችን ስናባርር ትዝ ይለኛል....
በወላጆቼ (በኛ) ቤት ውስጥ የዘመን መለወጫን ለማክበር
የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሌላው ግዜ የበለጠና ቀልቤን የሳበ ነው:: ለምን እንደሆነ አልገባኝም:: ላለፉት ጥቂት ቀናት ቤት
ውስጥ የአውራ ዶሮ ድምፅና ኩኩሉ እየሰማሁ ነው:: ከጉዋዳ የሚወጣው የበዓሉ ለት የሚሰራውን ዶሮና ስጋ ወጥ ለማጣፈጥ ተብለው የተዘጋጁ
ቅመማ ቅመሞች: በርበሬና ቅቤ ሽታ መቼም ለጉድ ነው:: እየበሰለ ያለ ጠላ ሽታም አልፎ አልፎ በነፋስ መልክ ወደ ሳሎን ቤት
ይመጣል::
በነገራችን ላይ የኛ ቤት ማታ ማታ ሞቅ ይላል:: በየቀኑ
ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ረዘም ያለ የቡና ስነስርዓት ይጀመራል:: ከእህቶቼ አንዷ ቡናውን የማዘጋጀት ኃላፊነት ትወዳለች::
ከሰል ይቀጣጠላል: ሰፊ ሮሆቦት ሳሎኑ መሃል ላይ ይሰየማል: ጀበና ይመጣል: ቡና ይቆላል: ፈንድሻም ይንዶሾዶሻል:: እጣንና
ዑድ ይጨሳል:: በቡናው መሃል እራት ይቀርባል:: የቡናው ስርዓት ቢያንስ ሁለት ሰዓት ያህል የውስዳል:: በመሃል ቀልድ ሳቅ
ጨዋታ ይደራል:: የቡናው ስነ ስርዓት ሲጠናቀቅም ቀስ በቀስ ሁሉም ወደየመኝታው ይሄዳል:: አባታችን ብቻ የራድዮኑን ጣቢያ
እየቀያየረ የእንግሊዝኛ ወሬ ሲያዳምጥ ሌሊቱን ያጋምሳል:: እኔም ሳሎን ውስጥ ከተዘረጋልኝ ታጣፊ አልጋ ላይ ተንጋልዬ አብሬው
በርቀት አዳምጣለሁ.....
No comments:
Post a Comment