Sunday, March 13, 2016

ነሐሴ 1985 አ.ም.

ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በተዘጋጀሁበት ዋዜማ ምሽት በጅማ ሰማይ ላይ ታንፅባርቅ የነበረችውን ግማሽ ጨረቃ ምን ግዜም አልረሳትም:: ያይኔ ምግብ የሆነች የማታስከፍል ቆንጆ ድፍን ቀይ ጨረቃ..... ለምን እንደሆነ ባላውቅም ከዚህ ትውስታ ጋር ተያይዞ ያሳለፍኩት የሶስተኛ ዓመት የመጀመሪያው ሴሚስተር ጉዞ ውልብ ሲልብኝ በዚህ ውስጥ ደግም እመቤትን አስታወስኩ:: እመቤት አዲስ አበባ ዮሐንስ ቤተክርስትያን አካባቢ ያፈራት መልካም ሴት:: እመቤት ባለፈው ሴሚስተር ከመቼውም ግዜ በላቀ ከኔ: ከአብይና ከመንጌ ጋር: ቅርርብ ጨምራለች:: ብዙ ጊዜ እኛ ወደተሰበሰብንበት ትመጣና በደስታና በሳቅ ትቀላቀላለች:: በቃ ከኛ ጋር መሆን እየተመቻት እንደመጣ መገመት አያዳግትም:: ከተቀላቀለችን በሁዋላ እንደልቧ ታወራለች: ትስቃለች: ትጫወታለች: መራር የሆኑ ቀልዶቻችንን ትቃለዳለች:: አልፎ አልፎም ሚስጥር ታጫውተናለች:: የአብይና መንጌን አላውቅም እኔ ግን ከአህቶቼ በስትቀር ከተቃራኒ ፆታ ጋር አብሮ መዋል መጫወት ስላለመድኩ ነገሩ አዲስ ሆኖብኛል:: ይህን የምለው ግን ሁኔታው ለኔም እንደተመቸኝ ሳልክድ  ነው::

ነሐሴ 19  ቀን ጅማን ለቅቄና ባውቶቡስ ተፈናጥጬ አዲስ አበባ ቤቴ ደንገዝገዝ ሲል ደረስኩ:: አዲስ አበባ በሚሰነፍጥ ቀዝቃዛ አየር ተቀበለችኝ:: እዚህ አሁንም ድረስ ጠዋቱን ሙሉ ይዘንባል:: ከሰዓት ደግሞ ደነናማ ሆኖ በጣም ይቀዘቅዛል:: ውስጥንም ያቀዘቅዛል:: በነገራችን ላይ በዚህ የእረፍት ግዜ ግጥም ለመፃፍ እቅድ አለኝ::

ጳጉሜ 1985 አ.ም.
እነሆ 1985 ሊፈፀም የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው:: ከዚያ በሁዋዋላ ያበሻው ፀደይ ወር መስከረም ብቅ ይላል:: መስከረምን በእውነት በጣም እወደዋለሁ:: ልጅነቴን የሚያስታውሰኝ ወር ነው:: አደይ አባባን ያስታውሰኛል:: ኩልል ያለ ውሃ የሚፈልቅባቸው ምንጮችንም ያስታውሰኛል:: ሰፈሩ መንደሩ ሁሉ አረንጉዋዴ መሆኑንም አይዘነጋኝም::  ከጉዋደኞቼ ጋር ሆነን በቀለም አይነትና በቁጥር የበዙ ቢራቢሮዎችን  ስናባርር ትዝ ይለኛል....

በወላጆቼ (በኛ) ቤት ውስጥ የዘመን መለወጫን ለማክበር የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሌላው ግዜ የበለጠና ቀልቤን የሳበ ነው:: ለምን እንደሆነ አልገባኝም:: ላለፉት ጥቂት ቀናት ቤት ውስጥ የአውራ ዶሮ ድምፅና ኩኩሉ እየሰማሁ ነው:: ከጉዋዳ የሚወጣው የበዓሉ ለት የሚሰራውን ዶሮና ስጋ ወጥ ለማጣፈጥ ተብለው የተዘጋጁ ቅመማ ቅመሞች: በርበሬና ቅቤ ሽታ መቼም ለጉድ ነው:: እየበሰለ ያለ ጠላ ሽታም አልፎ አልፎ በነፋስ መልክ ወደ ሳሎን ቤት ይመጣል::

በነገራችን ላይ የኛ ቤት ማታ ማታ ሞቅ ይላል:: በየቀኑ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ረዘም ያለ የቡና ስነስርዓት ይጀመራል:: ከእህቶቼ አንዷ ቡናውን የማዘጋጀት ኃላፊነት ትወዳለች:: ከሰል ይቀጣጠላል: ሰፊ ሮሆቦት ሳሎኑ መሃል ላይ ይሰየማል: ጀበና ይመጣል: ቡና ይቆላል: ፈንድሻም ይንዶሾዶሻል:: እጣንና ዑድ ይጨሳል:: በቡናው መሃል እራት ይቀርባል:: የቡናው ስርዓት ቢያንስ ሁለት ሰዓት ያህል የውስዳል:: በመሃል ቀልድ ሳቅ ጨዋታ ይደራል:: የቡናው ስነ ስርዓት ሲጠናቀቅም ቀስ በቀስ ሁሉም ወደየመኝታው ይሄዳል:: አባታችን ብቻ የራድዮኑን ጣቢያ እየቀያየረ የእንግሊዝኛ ወሬ ሲያዳምጥ ሌሊቱን ያጋምሳል:: እኔም ሳሎን ውስጥ ከተዘረጋልኝ ታጣፊ አልጋ ላይ ተንጋልዬ አብሬው በርቀት አዳምጣለሁ.....

Tuesday, March 8, 2016


ሐምሌ 30 ቀን 1985 አ.ም.

 

ባለፈው ሰሞን  አንድ ቆየት ያለ ከእናቴ የተላከ ደብዳቤ ደረሰኝ:: ከተፃፈ አንድ ወር ይሆነዋል:: ደብዳቤው ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ እናቴ ስልክ ደውላ ፈልጋኝ ነበር አሉ:: እንዳጋጣሚ ሆኖ አልተገናኘንም:: የደወለችበት ዋናው ምክንያት በባንክ ቤት በኩል ሃምሳ ብር እንደላከችልኝ ልትነግረኝ ነበር:: ሸጋ ዜና ነው:: ይህንኑ ብር ከባንክ ቤት ከተቀበልኩ በሁዋላ ከመንጌጋ ወደ ጅማ መርካቶ በመሄድ አንድ ጨርቅ ሱሪ በግማሹ ገዛሁ:: በተረፈው ጉዋደኞቼን ሰብስቤ ሻይና የበቆሎ ጥብስ ጋበዝኩበት…..የሄው ነው ያምሳ ብሩ ታሪክ::

 

በዚህ ቀፋፊ የሐምሌ ቀን በትክክል ምን ተሰምቶኝ እንደሆን ለመናገር ባልችልም የሚከተለውን የስንኝ ቁዋጠሮ ግን አሰፈርኩ….

 

ሃሳብ ከሃሳብ ተጋጭቶ አንዳች ነገር ላይፈጥር

እርስ በርሱ ሲተካካ በላይ በላይ ሲደረደር

ሁሉ ነገር ባዶ ሲሆን የማይጠቅም ሲመስል

የሚያስበው ነገር አጥቶ አእምሮ ባየር ሲዋልል

ዓለም ሁሉ ከንቱ ሲሆን የማይረባ

ጭብጥ የሌለው ከቁምነገር የማይገባ

ደስታ ነገር ሳቅ ጨዋታ ጭልጥ ሲል

ባዘኔታ ተለውጦ በቁዘማ ሲጠቃለል

አየር ለጫንቃ ሲከብድ..ወኔ ስፈራርስ ሲናድ

አእምሮ ነገር ሲያሳድድ..አንድም ላያገኝ የሚወደድ

ሁዋላም በራሱ ሲፈርድ..በምንም ሃሳብ ላይጠመድ

እንቅልፍ እልም ብሎ ሲጠፋ

ጭንቀት በምትክ ሲስፋፋ

ከቶ መጥፎ ነው የሚመር

አንድ ቀን ኑሮ ሲደብር

 

ከዚህ የስሜት ጢቅታ በተቃራኒ ደግሞ ሐምሌ መጨረሻ ላይ አየሩ መልካም እየሆነ የመጣ መስሎ ተሰምቶኛል:: ዝናብ ከዘነበ ጠዋት ብቻ ነው:: ከሰአትና ምሽት ላይ አየሩ ቀዝቀዝ ይልና መጠነኛ ነፋስ ሽው.. ሿ ስል ይሰማል::

 

በአሁኑ ሰዓት በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ ያሉት የህክምና ተማሪዎች ብቻ ናቸው ማለት እችላለሁ:: ከሁለተኛ ዓመት ላቦራቶሪ ተማሪዎች በስተቀር ሁሉም የዲፕሎማ መረሃ ግብር ተማሪዎች ለእረፍት ወደየመጡበት ሄደዋል:: እኛም ብንሆን ከሁለት ሳምንት በሁዋላ እረፍት እንወጣለን:: ቀሪውን ክረምትና አዲስ አመት እንቁጣጣሽን ከቤተሰቦቻችን ጋር እናሳልፋለን ማለት ነው:: ይህ መቼም እጅግ ደስ የሚል አጋጣሚ ነው:: ተስፋም ነው::  በበኩሌ ለአብዛኞቹ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቶችም ሆነ መምህራን ካደረብኝ ብርቱ ጥላቻ የተነሳ እረፍትንም ሆነ ባጠቃላይ ከዚህ አካባቢ ለተወሰነ ግዜ መለየትን ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ስሻ ነበር:: ተመስገን ነው:: ለነገሩ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቶች ደስ የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ:: ግን የሚያስተምሩት ሰዎች ላይ ቅሬታና የሻከረ ግምት አለኝ:: ለምሳሌ አንዳንዶቹ እንደ ማይክሮባዮሎጂ መምህር ያሉት ሲጀመር ባህሪያቸው አይስማማኝም:: ጠማማ ሆኖ ነው ለኔ የሚታየኝ:: አንዳንዴ እኔ ራሴን መቼ ይሆን መምህር የማመሰግነው? ብዬ እጠይቀዋለሁ:: ችግሩ የኔ ብቻ ይሆን እንዴ? ግን ደግሞ ወደ ሁዋላ ተመልሼ በጣም የምወዳቸውና የማከብራቸውን መምህራኖቼን አስታውስና እፅናናለሁ:: ለምሳሌ የአስራ አንደኛና አስራሁለተኛ ክፍል ፊዚክስ መምህሬ የነበረውን ህንዳዊውን ሚስተር ናየርን መቼም አልረሳውም:: እዚህ ጅጤሳ ፍሬሽማን ሂሳብ ያስተማረኝን ተስፋልደትን እንዲሁም ያለፈው ዓመት አናቶሚ  ፕሮፌሰሬን ግብፃዊውን ሳላህን በልቤ ከፍተኛ ሰፍራ እሰጣቸዋለሁ:: እነዚህን ሰዎች ሁሉ በበኩሌ አንድ የሚያደርጋቸው ሆኔታ አለ እላለሁ:: ሁሉም የሚያስተምሩትን ትምህርት እጅግ አዋቂዎች: በስራቸው ታታሪዎችና ዘወትር ለሌሎች ቀና አሳቢዎች ነበሩ….