Sunday, June 26, 2016

ጥቅምት 15 ቀን 1987 አ.ም

አራተኛ ዓመት አጋማሽ
አራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት ከተጀመረ አምስት ወር ሆነው:: እግዚአብሔር ይመስገን አሁን በስቴቶስኮፔ በማዳመጥ ከወትሮ የተለዩ የሰውነት ውስጥ ድምፆችን መለየት ችያለሁ:: በሽተኛን በእጄ እየደባበስኩ (palpation) ከወትሮው የተለቀ ጉበትና (Hepatomegally) የረዘመ ቆሽት (Splenomegally) በፍጥነት መለየት ችያለሁ:: ባለፉት አምስት ወራት ያለፍኩባቸው የቀዶ-ጥገናም (Surgery) ሆነ የውስጥ-ደዌ (Internal Medicine) ተግባራዊ ልምምዶች (Attachments) መልካም ነበሩ:: እንደፈራሁዋቸው ከባድ ወይም ስንክሳር የበዛቸው አልነበሩም:: ክፉና ተቆጪ መምህር አልገጠመኝም:: ባለፈው የጠቀስኩትን በሽተኛን አገላብጦ የመመርመር ፈተና የፈተነኝ ዶክተር ሳዲቅ እንኩዋን እንደገና በውስጥ-ደዌ ተግባራዊ ልምምድ  ስንገናኝ ፈፅሞ የተለየ ሰው ነው የሆነብኝ:: እንዲያውም በጣም የተረጋጋ: መካሪና ታላቅ ወንድማዊ ሆኖ አገኘሁት::

በነዚህ እያንዳንዳቸው አስር ሳምንታት በፈጁ ተግባራዊ ልምምዶች ወቅት የገጠመኝ አንዳችም የተለየ: ወይም ያልተጠበቀ ነገር አልነበረም:: ሁለቱንም ልምምዶች ስንጨርስ ተግባራዊ ፈተና (Practical Exam) ወሰድን:: ፈተናዎቹ እውነተኛ በሽተኞችን በሽታቸውን ጠይቆና መርምሮ: ለሚፈትነው መምህር የህመማቸውን ምንነት (Diagnosis) እንዲሁም በሽታውን ለማጣራት መደረግ ያለባቸውን የላቦራቶርም ሆነ የራጅ ምርመራ አይነቶችን (Diagnostic Tests) መዘርዘር ይጠይቃሉ::  ጥያቄና መልሱ የሚካሄደው እዚያው በሽተኛው የተኛበት አልጋ በቀኝ በኩል በመቆም ነው:: ፈታኙ መምህር በቦታው ከመድረሱ በፊት በሽተኛውን ለማነጋገርና ለመርመር የአንድ ሰዓት ጊዜ ይሰጣል::

በሁለቱም ፈተናዎች የደረሱኝ  የተለመዱና ቀለል ያሉ ኬዞች (Cases) ነበሩ: የውስጥ-ደዌ ፈተና በጉበት ታማሚ ላይ ሲሆን የቀዶ-ጥገና ደግሞ ሽንቱን መሽናት ባቃተው ታማሚ  (A  case of urinary retention) ላይ ነበር:: ባጠቃላይ ፈተናዎቹ  በጥሩ ሁኔታ ነው የሄዱት: ውጤቱን ግን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው::

ዛሬ ደግሞ የፅሁፍ ፈተና ወሰድን:ቀዶ-ጥገና. ቀለል ብሎ ተሰማኝ:: እርግጠኛ አይደለሁም ግን ምናልባት ፈተናው ከባድ ሆኖ እኔ ክብደቱን ማወቅ ተስኖኝ ሊሆንም ይችላል.....ለውስጥ-ደዌ ፈተና የፊታችን አርብ እንቀመጣለን:: ከዚያ በሁዋላ የሁለት ሳምንት እረፍት ይኖረናል:: እኔም ወደ አዲስ አበባ እሄዳለሁ::


ቅዳሜ መጋቢት 16 1987 አ.ም.

ሞሚናና የ አራተኛ ዓመት መጨረሻ
ዛሬ በጣም ያዘንኩበት ቀን ነው:: በጣም የምወዳትና የማከብራት እጀግ በጣም የቅርብ ጉዋደኛዬ ሞሚና የነርሲንግ ትምህርቱዋን አጠናቃ እኔንም ሆነ ጅጤሳን ተሰናብታ ሄደች:: ሞሚናን በጣም አቀርባት: በመልካምነቱዋ እወዳትና ከሁሉም በላይ ደግሞ በሥራዋ : በአላማዋ አከብራት ነበር:: ሞሚና ልክ እንደኔ የአማርኛ ስነ-ፅሁፍ በተለይም ግጥም ትወዳለች ትፅፋለችም:: ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር የማድረግ ጥማት አላት:: አብረዋት የተመረቁት የነርሲንግም ሆነ የሌላ ዘርፍ የዲፕሎማ ተማሪዎች በውስጣቸው በተፈጠሩ ጥቃቅን አለመግባባቶች የተነሳ በጋራ አንድ የምረቃ መፅሄት ማሳተም ተስኖዋቸው ሳለ ሞሚና ግዜዋን (ገንዘቡዋንም ይመስለኛል) ሰውታ የተራራቁትን ተመራቂዎች አስተባብራ ግሩም የሆነ መፅሄት እንዲታተም አድርጋለች:: በመፅሄቱ ውስጥ ከሰፈሩት ፅሁፎች ውስጥ አየነው በተባለ ተመራቂ የተፃፈ C'est la vie (That is Life) የተሰኘ የእንግሊዝኛ መጣጥፍ አይረሳኝም:: ከኔ ሌላ ብዙ ፅሁፉን ያነበቡ ተማሪዎች ሲያደንቁት ሰምቻለሁ::


ሞሚና ተሰናብታኝ ስንለያይ ሆዴ ውስጥ የሆነ ነገር ሲራወጥ ተሰማኝ:: በተለይ ደግሞ ከምረቃው (Graduation) ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ባሉት ቀናቶች በተደጋጋሚ  አብረን ያሳለፍናቸው የሻይና የቡና ጊዜያት አይረሱኝም:: እንደወትሮአችን ሁሉ ብዙ ነገሮችን አወጋን:: ሞሚናን የተለሁበት ወቅት የአራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርቴን ለማጠናቀቅ ፈተና ለመውስድ ሽር ጉድ የምልበት ወቅት በመሆኑ የኔን ሁኔታ ከባድ አድርጎታል:: ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሁዋት ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ መንሱር ሱቅ አጠገብ ነበር..........

Sunday, June 5, 2016

ሰኔ 21 ቀን 1986 አ.ም.

ሀኪም ወደመሆን…

የኔ ዉድ: ያን የሶስተኛ ዓመት መጨረሻ ገደማ የህክምናን ትምህርት ቀጥሎ የማጠናቀቅ ፅኑ ውሳኔ በልቤ ማኖሬን የሚጠቅስ ማስታወሻ ካሰፈርኩበት ቀን በሁዋላ: ምንም ለትውስታ የሚበቃ ክስተት ሳይኖር: ቀናቱ እንዴት እንደሄዱ ሳላውቀው: ራሴን የአራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት (C-1) መጀመሪያ ሰሞን አገኘሁት:: ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ዶክተሮች ብቻ  ሕክምናን የምንማርበት: እውነተኛ የታመመ ሰው የምናነጋግርበት እንዲሁም የምንመረምርበት ዓመት….. ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ቀልድ አያውቁም:: ኩሩዎች: ቁጡዎችና ግሳፄያቸው የሚያስፈራ ናቸው:: በየጊዜውና በየሁኔታው ይገስፁናል:: በእውነቱ ሐኪምም ቢሆኑ እነዚህ የሚመቹኝ እንደማይሆኑ ግልፅ ነው:: በእርግጥም አልተመቹኝም:: እነሱ ሲገስፁ እኔ ሲጎረብጠኝ: እነሱ ሲገስፁ እኔ ሲጎረብጠኝ: አራተኛ ዓመት በተጀመረ በአንድ ወሩ የተሰጠኝን በሽተኛን አገላብጦ የመመርመር (Physical Exam) ፈተና ሳላልፍ ቀረሁ:: ማለትም የተዘጋጀልኝን በሽተኛ ከበስተጀርባዬ እንደጅብራ ቆሞ ሲያየኝ ለነበረው ሀኪም(ዶ/ር ሳዲቅ) በሚያረካ መልኩ ሳላገላብጠው: ሳልመረምረው ቀረሁ:: መርምሬውም ዶ/ር ሳዲቅ ከኔ ቀድሞ በሽተኛውን መርምሮ ያወቀውን እኔ ሳላውቅ ቀረሁ:: ዶ/ር ሳዲቅ ሀበሻዊ ቁጣን ተቆጣ:: ገነፈለ:: ዘራፍ አለ:: በሽተኛው ብልብና ትንፋሽ ማዳመጫው (stethoscope) የሚሰሙ: ከሳንባዎቹ የሚፈልቁ ቀጫጭን የስትንፋስ ድምፆች (bronchial  breath sounds) ነበሩት ለካ….የሳምባ ምች (Pneumonia) ተጠቂ ነበር::

ከዚህ አጋጣሚ በሁዋላ መንፈሴ ትክክል አልነበረም:: ከማንም ጋር ማውራት አልከጀልኩም:: ብቻ ቀጥታ ወደ ማደሪያዬ በማቅናት: ፊቴን ወደ ግድግዳው አዙሬ አልጋዬ ላይ ተጋደምኩና: የአይኖቼን ቀዳዶች ፈንቅሎ ሊወጣ የሚዳዳውን ንዴት አዘል እምባ ታገልኩት...