ሰኔ 21 ቀን 1986 አ.ም.
ሀኪም ወደመሆን…
የኔ ዉድ: ያን የሶስተኛ ዓመት መጨረሻ ገደማ
የህክምናን ትምህርት ቀጥሎ የማጠናቀቅ ፅኑ ውሳኔ በልቤ ማኖሬን የሚጠቅስ ማስታወሻ ካሰፈርኩበት ቀን በሁዋላ: ምንም ለትውስታ የሚበቃ
ክስተት ሳይኖር: ቀናቱ እንዴት እንደሄዱ ሳላውቀው: ራሴን የአራተኛ ዓመት ሕክምና ትምህርት (C-1) መጀመሪያ ሰሞን አገኘሁት::
ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ዶክተሮች ብቻ ሕክምናን
የምንማርበት: እውነተኛ የታመመ ሰው የምናነጋግርበት እንዲሁም የምንመረምርበት ዓመት….. ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ቀልድ አያውቁም::
ኩሩዎች: ቁጡዎችና ግሳፄያቸው የሚያስፈራ ናቸው:: በየጊዜውና በየሁኔታው ይገስፁናል:: በእውነቱ ሐኪምም ቢሆኑ እነዚህ የሚመቹኝ
እንደማይሆኑ ግልፅ ነው:: በእርግጥም አልተመቹኝም:: እነሱ ሲገስፁ እኔ ሲጎረብጠኝ: እነሱ ሲገስፁ እኔ ሲጎረብጠኝ: አራተኛ ዓመት
በተጀመረ በአንድ ወሩ የተሰጠኝን በሽተኛን አገላብጦ የመመርመር (Physical Exam) ፈተና ሳላልፍ ቀረሁ:: ማለትም የተዘጋጀልኝን
በሽተኛ ከበስተጀርባዬ እንደጅብራ ቆሞ ሲያየኝ ለነበረው ሀኪም(ዶ/ር ሳዲቅ) በሚያረካ መልኩ ሳላገላብጠው: ሳልመረምረው ቀረሁ::
መርምሬውም ዶ/ር ሳዲቅ ከኔ ቀድሞ በሽተኛውን መርምሮ ያወቀውን እኔ ሳላውቅ ቀረሁ:: ዶ/ር ሳዲቅ ሀበሻዊ ቁጣን ተቆጣ::
ገነፈለ:: ዘራፍ አለ:: በሽተኛው ብልብና ትንፋሽ ማዳመጫው (stethoscope) የሚሰሙ: ከሳንባዎቹ የሚፈልቁ ቀጫጭን የስትንፋስ ድምፆች (bronchial breath sounds) ነበሩት ለካ….የሳምባ ምች (Pneumonia) ተጠቂ ነበር::
ከዚህ አጋጣሚ በሁዋላ መንፈሴ ትክክል አልነበረም::
ከማንም ጋር ማውራት አልከጀልኩም:: ብቻ ቀጥታ ወደ ማደሪያዬ በማቅናት: ፊቴን ወደ ግድግዳው አዙሬ አልጋዬ ላይ ተጋደምኩና: የአይኖቼን
ቀዳዶች ፈንቅሎ ሊወጣ የሚዳዳውን ንዴት አዘል እምባ ታገልኩት...
No comments:
Post a Comment