Wednesday, November 2, 2016

የቀዶ ጥገና አንድ ሳምንት ነሐሴ 22 -26 1987 አ.ም.

ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 1987 አ.ም.
እኔና እኔ ያለሁበት ቡድን ዛሬ በጠዋት የአምስተኛ ዓመት የቀዶጥገና (Surgery) አታችመንት ጀመርን:: በደፓርትመንት ኃላው በዶ/ር አለምሰገድ ቢሮ ተገኝተን ከእርሱ መመሪያና ምክር ተቀበልን::  ዶ/ር አለምሰገድ ሰባት ሳምንት በሚፈጀው ቀጣዩ የቀዶ ጥገና ልምምድና ሥራ (attachment) የሚከናወኑ ተግባራትና ከኛ የሚጠበቀውን ዝግጅት አስረዳን:: የመጨረሻ ዓመት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ጠንክረን እንድናጠና አስጠነቀቀን::  በዚህ እለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና መኝታ ክፍል በመሄድ የተመደቡልኝ ህሙማን ተዋውቄና በማግስቱ ተመልሼ እንደማያቸው ቃል ገብቼ ተመለስኩ:: አሁን እንደአምናው በሽተኛ መቅረብ በፍፁም አይከብደኝም:: አራተኛ ዓመት ሲጀመር የመጀመሪያውን ህመምተኛ ለማናገር የነበረኝን ፍርሃት እስካሁን አልረሳውም:: ዛሬ ሁሉ ቀላል ነው:: ደሞ ህመምተኛ ማናገር ምን ይከብዳል?

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 1987 አ.ም.
ዛሬ ከዶ/ር ግዛውጋ ቀላል ቀዶ ጥገና አደረግን Herniotomy & Hernioraphe of Epigastric Hernia:: ለመጀመሪያ ግዜ በቀዶ ጥገና ግርዛት (Circumcision) ያየሁትም ዛሬ ነው:: ከሰዓት በሁዋላ ወደ ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና መኝታ ክፍል በመሄድ የተመደቡልኝን ህሙማን በሙሉ መርምሬና መዝገባቸውን አገላብጬ እንዲሁም የበኩሌን ዘገባ ስለእያንዳንዳቸው ፅፌ አጠናቀኩ:: ለነገ ተዘጋጀሁ::

ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 1987 አ.ም.
ዶ/ር ግዛው ዛሬ ሁሙማኑን በሙሉ እየዞረ ጎበኘ: መረመረ:: እኛም ስለህመምተኞቻችን የዘገብነውን አነበነብንለት:: ይሆናል ያልነውን የላቦራቶር መርመራና አስፈላጊ ሕክምና ጠቆምን: ተናገርን:: እሱም አንዳንዱን ሲከለክል አንዳንዱን ደግሞ ይሁን አለ:: የከለከለውንም ለምን እንደከለከለ አስተማረ:: ከዚያም ከሰዓት ሆነ:: ዘመኑ እና ዮናስ የሚባሉት የኔ ቡድን አባላት ሴሚናር አዘጋጆች ነበሩ:: ይህ በሆነ አርስት ላይ መፅሐፍ አገላብጦና አንብቦ ለታዳሚ የሚቀረብበት ዝግጅት ነው:: በዝግጅቱ መጨረሻ ላይ ታዳሚ ከበድ ያለ ጥያቄ ሊሰነዝር ይችላልና አቅራቢ ሲኮን ያሳስባል:: ዘመኑ እና ዮናስ ዶ/ር አለምሰገድ ባለበት አቀረቡ:: ምንም የተለየ ነገር ሳይኖር ተጠናቀቀ:: በዚህ ቀን ምሽት በቀዶ ጥገና ድንገተኛ ህሙማን የሚታዩበት ክሊኒክ ውስጥ ተረኛ ነበርኩ:: እስከምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል በዚያ ቆየሁ::

ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 1987 አ.ም.
በዚህ ቀን ደግሙ ከባድ ቀዶ ሕክምና ክፍል (Operating Theatre) ውስጥ ነበርኩ:: ሁለት ቀዶ ጥገናዎች ተደረጉ:: አንደኛው የሆድ ቀዶ ጥገና ሲሆን ህመምተኛዋ ለአንድ አመት ያክል ግዙፍ እባጭ በሆዷ ተሸክማ የቆየች ናት::  ሌላኛው  አንዲት ትንሽ ሴት ሕፃን ልጅ እጇን አንድ አዋቂ ሳያስበው በመጥረቢያ ቆርጦት ነው:: ታሪኩ ቢዘገንነኝም ቁስሏ ሲሰፋና ሲዘጋ እያገዝኩ ተመለከትኩ:: ታዲያ ዛሬ ቀዶጥገና ከሕክምና ትምህርቶች ሁሉ የሚስብ ሆኖ ታየኝ:: ቅፅበታዊ ቀዶ ጠጋኝ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ:: ለዚህም ነው ቀዳጁን ዶ/ር ሚናስን አራተኛ ዓመት እያለሁ በጣም የተደሰትኩበት የህክምና ትምህርት ምን እንደሆነ ሲጠይቀኝ ቀዶ ጥገና! ብዬ የመለስኩለት:: እሱም በጣም ከት ብሎ ሳቀ:: መልሴ የታሰበበት እንዳልሆነ ገብቶታል::


አርብ ነሐሴ 26 ቀን 1987 አ.ም.

ዛሬ ጠዋት በታማሚ አልጋ ዙሪያ ቆመን የምንማርበት ከፍለግዜ (Bed Side) ነበረን:: ህመሙ Gastric outlet obstruction (GOO ብለን አሳጥረን የምንጠራው) ነበር:: አስተማሪው ቀዳጅ ሀኪም ዶ/ር ሚናስ ነበር:: ከሰዓት በሁዋላ ደግሞ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን ስለ አንድ በሽታ ሕክምና በቻ በጥልቀት የምንወያይበት ክፍለግዜ (Management Session) ነበር:: ትምህርቱ ጅማ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ እየታከመ ያለ ወይም ታክሞ የነበረ እውነተኛ ህመምተኛ ላይ ተንተርሶ የሚሰጥ ነው:: የዛሬው ያተኮረው a case of traumatized patient and head injury ላይ ነበር:: አስተማሪው ቀዳጅ ሀኪም ዶ/ር ግዛው ነበር::

No comments:

Post a Comment