Wednesday, January 29, 2014

የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ

ጥቅምት ፩፱፰፫ አ.ም. በዚያው ሰሞን...

የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ


በቀዩ የሸክላ አዳራሽ ዉስጥ ያድሩ የነበሩ ነገር ግን የህክምና ተማሪ ያልሆኑ ልጆች  የየዲፓርትመንቶቻቸው ልጆች ወዳሉባቸው ሌሎች የሸክላ አዳራሾች እንዲዛወሩ ተደረገ:: በዚህም ምክንያት ይሄኛው የለመድኩት አዳራሽ ይበልጥ ሰፋብኝ::

ባለፈው ባዮሎጂ ቤተ ሙከራ ፀጉር በማይክሮስኮፕ  ያየን ሰሞን እንደአጋጣሚ ሆኖ አብዛኞቹ ኢንስትራክተሮች የተለያዩ የቤት ስራዎችን ሰጥተውን ነበር:: የእንግሊዝኛው ኢንስትራክተር የምንፈልገውን አርስት መርጠን በእንግሊዝኛ የቃል ንግግር እንድናዘጋጅ አዝዞን ነበር:: ፊዚክስ እንደዚሁ ከሶስት ላይብረሪ ብቻ ከሚገኙ የተለያዩ መፃህፍት ዉስጥ ጥያቄዎች ሰርተን መልሱን እንድናዘጋጅ ነግሮን ነበር:: ባለው የቁጥር ውሱንነት የተነሳ መፅሃፎቹ ሰርኩለሽን ዴስክ ጀርባ ተቀምጠው በየተራ የሚወጡ ናቸው:: መፅሃፍቱን ለማግኘት አንድ ሁለት ግዜ ሞክሬ ሁሉም ቀድመው በተገኙ ሌሎች እኔን መሰሎች በመወሰዳቸው እድለኛ ልሆን አልቻልኩም:: ሂሳብም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚሰራ ነገር ነበር::

ታዲያ እንዚህን ሁሉ በቅጡ ሳልሰራ የሳምንቱ ማብቂያ ደረሰና ያሰብኩት ሊሆን ባለመቻሉ መጠነኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥ ተሰማኝ:: ቅዳሜ ማታ ተስፋ መቁረጥ ያመጣውን የድካም ስሜት ተጎናፅፌ አልጋዬ ላይ ተጋድሜ ሳለ በቁመናው ረዘም ያለውና ከእኔ አጠገብ የላይኛው አልጋ ላይ የሚተኛው ተማሪ መጣ:: በቅፅል ስሙ ጆን ኬኔዲ እየተባለ የሚጠራው ልጅ ነው:: ጆን ኬኔዲ  እንደመጣ አልጋዬ ጫፍ ላይ ተቀመጠና በቀጥታ ወደ ቁም ነገሩ ገባ:: በዚያው ሰሞን ሁኔታዬን ሲከታተል እንደነበረና እንቅስቃሰዬ እንደቀነሰ አይነት የተሰማዉን ነገረኝ::  "ምንድን ነው? ችግር አለ እንዴ? ስለ ትናንሽ ችግሮች የምታስብ  ከሆን እርሳቸው ባክህ": አለኝና: እኔ ምንም ሳልጠይቀው "ስማ! በቃ እኔ ና አንተ ዛሬ የ ጥናት ፕሮግራም እናውጣና እኔ ቢዚ አደርግሃለሁ: አለኝ:: እንዲህ ነችና! ከዚያም በፍጥነት አንድ የሆነ ፕሮግራም ነደፍን:: ከነገ ጀምሮም ፕሮግራሙን በሥራ ላይ ለማዋል ቃል ተገባባን:: ሌላም ብዙ ነገር ተነጋገርን:: ጆን ኬኔዲ ባለፈው አመት በ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቨትረነሪ ሳይንስ ትምህርቱን ሲከታተል እንደቆየና እንደገና በማመልከት ሕክምና መርጦ እዚህ እንደመጣ ነገረኝ:: "የ አንድ ዓመት የስራ ልምድ ካለው ሰው ጋ ነው የማወራው አልኩ በሆዴ" ታዋቂ ሰው ያነጋገርኩ ያህል ደስ አለኝ:: ልበ ሙሉነትም ተሰማኝ:: ቀደም ሲል ይዞኝ የነበረውም ድብርት ለቀቀኝ:: ከአልጋዬ ተነሳሁና ወደ አዳራሹ መሃል ሄጄ ሰፊውን ክፍልና አልጋዎቹን አንድ ባንድ ቃኘሁዋቸው:: በዚህ ሰፊ ክፍል ውስጥ መኝታ ቤት የሚጋሩኝን ሀኪም ጨቅሎች አሰብኩአቸው:: ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍሎች የመጡ ሲሆኑ ከአዲስ አበባ የሄድነው በቁጥር እንበዛለን መሰለኝ:: በመቀጠል ከጎጃም ክፍለ ሀገርም በርከት ያሉ ለጆች አሉ:: ከአዳራሹ መግቢያ በር በስተግራ ባለው ጥግ በኩል ሶስት ከ ሐረር ከተማ የመጡ ልጆች አሉ:: በጣም ይግባባሉ:: ከሐረር ልጆቹ ቀጥሎ ወደኔ አልጋ አቅጣጫ ሁለት ከወለጋ ክፍለ ሀገር የመጡ ልጆች አሉ:: ሁለቱም የታችኛው አልጋ  ላይ የሚተኙ ሲሆኑ ከነሱ በላይ ካሉት ተደራቢ አልጋዎች ላይ ሁለት ከጎጃም ከፍለ ሀገር የመጡ ልጆች አሉ::  ከነሱ አጠገብ አሁንም ወደኔ አቅጣጫ ሁለት ከወሎ ክፍለ ሀገር ከደሴ የመጡ  ልጆች ሲኖሩ ከነሱ ለጥቆ የ ጆን ኬኔዲ: ና ከኔው ሃይ ስኩል የመጡት ሁለት ልጆች አልጋዎች አሉ:: ከኔ በስተቀኝ አንድ ከወሊሶ ከተማ  የመጣ ልጅ ሲኖር ከሱ አጠገብ ከእኤርትራ  የመጣ አንድ ቀጭን ረዥም ልጅ አለ:: ከሌሎቻችን ዘግይቶ በቅርብ ነው ወደ ጅማ የመጣው:: ከሱ ቀጥሎ ደግሞ ሌላ አንድ የጎጃም ለጅ አለ......እያለ ይቀጥላል

Tuesday, January 21, 2014

የመጀመሪያ ግንዛቤ

ጥቅምት ፩፩ ፩፱፰፫ አ.ም.

የመጀመሪያ ግንዛቤ 


ዛሬ አመሻሹ ላይ ከተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ (ጃምቦ ምግብ ቤት) ራት ተመግቤ ስወጣ አንድ የ ነርሲንግ ተማሪ የሆነ ወጣት ከአዲስ አበባ የተላኩ አምስት ደብዳቤዎችን ሰጠኝ:: እርሱ በግል ችግር ዘግይቶ ገና መምጣቱ ነው:: ሶስቱ ደብዳቤዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ዓመት ከገቡ የ ሃይ ስኩል ጉዋደኞቼ የተላኩ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከሰፈር አብሮ አደጎቼ ነበሩ:: ብዙም ግዜ ሳላጠፋ ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ በመሄድ  አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ ደብዳቤውቹን  አንድ ባንድ አነበብኩዋቸው:: የሁሉም ደብዳቤዎች አጠቃላይ መንፈስ ሰላምታ ነው:: እየረሳሁት የነበረውን የሰፈርና የቤተስብ ናፍቆት በትዝታ ትጎትቼ እንደገና ተጋተርኩት:: ወደ ትምህርቱ ትኩረት በማድረግ በኩል ደህና ተሽሎኝ ነበር:: እንደመጀመሪያው ብዙ ሃሳቦች በአንድ ግዜ የሚመጡብኝ አባዜ ትቶኝ ነበር:: ከሩቅ ትዝታ ለመውጣት ስል ስለ ጅጤሳ ማሰብ ጀመርኩ ለምሳሌ የ ትናንትና ውሎዬን.....

የትናንትናውን ከሰዓት  የህክምና ተማሪዎች በሙሉ ያሳለፍነው ባዮሎጂ ላቦራቶሪ ውስጥ ነበር:: ትምህርት ከጀመርን የመጀመሪያው ላቦራቶሪ ክፍለ ግዜ  መሆኑ ነው:: የ ክፍለ ግዜው ዋና መንፈስ በማይክሮስኮፕ መመልከት  ነበር:: ለመጀመሪያ ግዜ ከማይክሮስኮፕ አጉሊ መነፅር በታች ቅንጣት ፀጉር አኑሬ ተመለከትኩ: እንደሌሎቹ ተማሪዎች:: ማይክሮስኮፑ አንድ ለአንድ ስለማይበቃ ፀጉሩን ያየነው በቡድን ሆኖ በየተራ ነው:: እኔ ባጋጣሚ ከሴቶቹ አንዱዋ ጋ ስለነበርኩ የፀጉር ቅንጣት ለማግኘት አልተቸገርኩም:: ሌክቸር ላይ የሚፈጥነውና ሲናገር የትግርኛ ለዛ ያለው የባዮሎጂ ኢንስትራክተር ፀጉሩን በማይክሮስኮፕ ካየን በሁዋላ ሀተታ (Report) እንድንፅፍ ባዘዘን መሰረት እኔም ፃፍኩ:: ግን ዛሬ ሳስበው አንድ የከነከነኝ ነገር አለ:: በሀተታው መጨረሻ ላይ ግንዛቤ (Conclusion) ብዬ ያስቀመጥኩት እንዲህ ይነበባል በእንግሊዝኛ... "Black hair appears brown under microscope":: ለራሴ አሳቀኝ:: የሳኩበት አንዱ ምክንያት ዘሬ የፀጉሩ ቅንጣት ባለቤት የሆንችውን ልጅ በቅርብ ርቀት ና በትኩረት የማየት ዕድል ስለገጠመኝ ነው: ቅድም አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቅምጠን ነበር ምሳ የበላነው:: የልጅቱዋ ፀጉር ጠቆር ይላል እንጂ ለካ ቡና አይነት ነው!

ናፍቆት ውስጥ ላለመግባት መታገሌን ቀጥያለሁ.....በነገራችን ላይ ትናንትና ማታ ለሁለተኛ ግዜ የመብራት አገልግሎት ተቁዋርጦ ነበር:: ደግነቱ መፅሐፍት ቤት ውስጥ አልነበርኩም:: አንድ ጅማ ውስጥ የማውቃቸው ቤተሰብ ቤት ውስጥ ነበርኩ:: እኔ የነበርኩበት ሰፈር መብራት  ስለነበረ ወደ ጅጤሳ ስመለስ ነው ኤሌክትሪክ መቁዋረጡን ያወቅሁት:: ቀስ በቀስ የተገነዘብኩት ነገር መብራት ብቻ ሳይሆን ዉሃም በተደጋጋሚ ይቁዋረጣል:: ዛሬ ቀን እንኩዋ የተማሪዎች ምግብ ቤት ዉስጥ የእጅ መታጥቢያም ሆነ ጉርሻን ከጉሮሮ ማውረጃ የሚሆን የመጠጥ ዉሃ አልነበረም:: ምሳ በደረቁ ተበላ:: እኔም ፀጉር በላሁ.....ባይኔ

የጤና ሳይንሱ ግቢ መቸም ሰፊ ነው:: እኛ ወንዶቹ ከምናድርበት ቀይ የሸክላ አዳራሽ አንስቶ ሴቶች ና ከፍረሽ ማን ባሻገር ያሉ ተማሪዎች የሚኖሩበት ዋይት ሃውስ የሚሰኝ ህንፃ ለመድረስ አንድ አስር ደቂቃ ይፈጃል መሰል:: በመጀመሪያ ከኛ ማደሪያ ወጥቼ በ ዛፎች መሃልና በመፀዳጃ ቤቶቹ ጎን: ብዙ ቀደምት የእግር ጉዞዎች በሰሩት ቀጭን የእግር መንገድ ላይ እራመዳለሁ:ከዚያም በመፅሕፍት ቤቱ ጎን አድርጌ በቀኝ የተማሪዎች ሻይ ቤት በግራ የጤና ሳይንሱን ዋና መግቢያ በር በርቀት እያየሁ አልፍና ወደ ነርሲንግ ደፓርትመንት ህንፃ የሚወስድ የእግር መንገድ ላይ እወጣለሁ: እዚህ መንገድ ላይ ዳር ዳሩን የተከረከመ ፅድ ያለ ሲሆን በቀኝ የ ምርቃት ስታዲዮም እየተገነባ ያለበትበት የጎደጎደ ቦታ በግራ ደግሞ መሃሉ ላይ የባንዲራ ምሶሶ የቆመበት አነስተኛ ሜዳማ ስፍራን አልፎ ስንጀምር የተመዘገብንበት የ ሸክላ ህንፃ ይታየኛል:: በዚህ የሽክላ ህንፃ ውስጥ የተማሪዎች ጉዳይ ቢሮ ና ክሊኒክም ይገኛል::በነርሲንግ ህንፃ ስር ባለ ሰፊ መተላለፊያ ኮሪዶር አልፌ በመቀጠል በቀኝ የኛን ሌክቸር ሆል በግራ ደግሞ ባዮሎጂ ላቦራቶሪን አልፋለሁ: ሁለቱም ከብሎኬት የተሰሩ ናቸው:: ከዚያም አቅጣጫዬን ወደ ቀኝ በማድረግ ወደ ዋይት ሃውስ አቀናለሁ:: ረጅም የእግር መንገድ ነው ይሄ:: ጎዳና ብለው ይሻላል:: በሁለቱም ጎኑ በሳር የተሸፈነ ወጣ ገብ መሬት ሲኖር በቀኝ አልፎ አልፎ ዛፎች አሉ:: የዓመቱ መግቢያ በመሆኑ ነው መሰል ሳሩ ርዝመቱ የዋዛ አይደለም:: በቅርቡ ይታጨዳል የሚል ግምት አለኝ....

መልካም.....ቸር ይግጠመን

Tuesday, January 14, 2014

የመጀመሪያው ዳፍንት

ጥቅምት ፬  ፩፱፰፫ አ.ም.


የመጀመሪያው ዳፍንት...

ትናንትና የጤና ሳይንሱን ግምብ አጥር በውጭ በኩል ተደግፌ ቆሜ ሳለ በእድሜ ከኔ እኩል የሆኑ ወይም የሚያንሱ ጮርቃ ወንዶች ቁጥራቸው አራት በሚሆን አውቶቡሶች ታጭቀው ሲንቀሳቀሱ አየሁ:: መሬት ላይ ብዛት ያላቸው ሰዎች ቁመው አንዳንዶቹም ከአውቶቡሶቹ ጎን እየሮጡ እጃቸውን በማወዛወዝ ሲሰናብቷቸው  ተመለከትኩ:: አንዳንድ በእድሜ የገፉ ሴቶች እና እናቶች ያለቅሳሉ:: የአውቶቡሶቹ መድረሻ የብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ካምፕ እንደሆነ ምንም አልተጠራጠርኩም:: ከዚያም ወደ ጦርነት:: በእውነቱ እጅግ አዘንኩ:: ያን ትዕይንት እያየሁ ታዲያ በውስጤ ሲብሰለሰሉ የነበሩ ጥቃቅን ና እንቶ ፈንቶ ችግር ተብዬ ሃሳቦችን ይዞ መቀጠል የማይመስል ሆኖ ታየኝ:: ስለዚህም በዚያው ቅፅበት እንደ ሲጋራ ቁሩ ወደ መሬት ጥዬ ረገጥኩዋቸው:: የኛ ቅምጥል አልኩት ራሴን:: ደሞ እኔን ብሎ በረባ ባልረባው አሳቢ:: ከዚያ ትዕይንት ጀምሮ ወደፊት ጤና ሳይንሱ ውስጥ እያለሁ ለሚያጋጥሙኝ መሰናክሎች እጅ ላለመስጠት በውስጤ ለራሴ ቃል ገባሁ:: ማትሪክን ባላልፍና እዚህ ባልመጣ ኑሮ የኔም እጣ ፈንታ እንዲህ ነበር ማለት ነው? እዉነት የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዬን ባላልፍ ምን ነበር የማደርገው? የተዘጋጀሁበት ጥያቄ ስላልነበር ዘለልኩት::


ከላይ የገለፅኩትን ቃል መግባት ተከትሎ ምሽት ላይ የኤሌትሪክ መብራት በጤና ሳይንሱ  በሙሉ በመቁዋረጡ ዳፍንት ሰፈነ:: ጅማ ከመጣሁ የመጀመሪያዬ የሆነው ይህ ዳፍንት ሲከሰት መፃፍት ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብዬ ነበር:: በነገራችን ላይ መፃህፍት ቤቱም ልክ እንደኛ ማደሪያ የተሰራው ከ ቀይ ሸክላ ሲሆን በስፋት ግን ይበልጣል:: ሌሎች እኔን መሰሎች ሲገቡ ስላየሁ እንጅ እኔ በቁም ነገር የማነበው ነገር ኖሮኝ አልነበረም:: ቀደም ብዬ እንዳልኩት ምንና እንዴት እያነበቡ እንደሆነ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው::ግን አለ አይደል ማን ከማን ያንሳል! ማን ገብቶ ማን ይቀራል.... የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ...አይነት  አበሻዊ ፉክክር ውስጤን ጎብኝቶት ኑሮ ጅጤሳን በረገጥሁ በሁለት ሳምንቴ በዚያ ሰዓት  መፅሐፍት ቤት ተገኘሁ :: ለነገሩ የተቀመጥኩት ሆን ብዬ ዳርቻ ላይ ስለነበር ወጭና ወራጁን የጎሪጥ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ ሳይ ነበር: ዳፍንት አቁዋረጠኝ እንጂ......ለጨለማ አዲስ ባልሆንም ከዚህ በፊት የማዉቀው መለስ: ለስለስ ያለ ነበር:: ይሄኛው ለየት አለብኝ:: ስለዚህም ዳፍንት አልኩት:: ባገራችን አይን ቢወጉ አይታይም እንደሚባለው:: ከቅፅበት በፊት በነበረው ብርሃንና በዳፍንቱ መሃል ያለው ትየለሌ ልዩነት በውስጤ ግዙፍ ድንጋጤን በመንዛቱ ከመጮህ መለስ ያለ ድምፅ ሳይወጣኝ አለቀረም:: እርግጠኛ ግን መሆን አልቻልኩም:: ምክንያቱም በተመሳሳይ ግዜ ብዙ ጭዋሂዎች ነበሩ:: ብቻ ምንነታቸው ያልታውቁ በርካታ ድምፆች ነበሩ:: በለው! ለማንኛውም እኔ ቀደም ብዬ ወደ ማሰልጠኛ የሚሄዱትን ወጣቶች እያየሁ ለእክል ላለመረታት የገባሁትን ትኩስ ቃል በመንተራስ ልቤን አይዞህ እንግዲህ ቼ በል! አልኩት::  በእውነቱ የበለጠ ግን ያጠነከረኝ ዳፍንቱ ሚዛናዊ: ማለትም ሁሉንም ተማሪ ያካተተ መሆኑ ነው:: "ዋናው ማንም አለማንበቡ ነው".....አልኩ በሆዴ:: እንደውም እንኩዋን ጠፋ! ልክ ጠይቄ ያስጠፋሁት ነው የመሰለኝ:: (እርገጥ ነው በሁዋላ እንደሰማሁት አንዳንድ የመኝታ አዳራሻችን ውስጥ ሆነው ሲያነቡ የነበሩ ተማሪዎች ዳፍንቱ በሰፈነበት ቅፅበት  በተጠንቀቅ ላይ የነበሩ ሻማዎችን እንደለኮሱ ተስተውሏል)::ብርሃን ተመልሶ እንዲመጣ ብመኝም ግን ትንሽ ሁሉም እስከሚተኛ ዘግየት ቢል አልኩ በልቤ:: ምን አሷሸኝ: እኔን በዚያ ወቅት  ያሰኘኝ የሸክላው አዳራሽ በር ጋ ወይም ሌላ የሆነ ቦታ ተቅምጦ ሰብሰብ ብሎ በተፈጠረው ጨለማ ቧልት ማውራት ና መሳሳቅ....... ነገ ግን በቃ የምሬን መማር እጀምራለሁ::


በነገራችን ላይ ጤና ሳይንሱን ከረገጥኩበት ቀን አንስቶ እስከአሁን ድረስ ግቢዉን: የወደፊት ጉዋደኞቼን: ትምህርቶቹንና አስተማሪዎቹን ስለማመድና ሳጠና ነበር:: ቀርቤ ያነጋገርኩዋቸው ተማሪዎች በሙሉ በባህሪ ሸጎች ናቸው:: ምንም አይሉም:: ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ናቸው:: ከነሱ ውስጥ አራት ሴቶችም አሉባቸው:: ከሚያስተምሩን ውስጥ በተደጋጋሚ ያየሁት የዲፓርትመንት ኃላፊ የሆነውን ተስፋልደትን ነው:: ሂሳብ ያስተምረናል:: እስካሁን ባየሁት ፀባዩም ሆነ የማስተማር ችሎታው ተመችቶኛል.....


Tuesday, January 7, 2014

አስራ አራት ብሬ

ካለፈው የቀጠለ...ጅ.ጤ. ሳ.   አስራ አራት ብሬ

ጥቅምት ፬  ፩፱፰፫ አ.ም.


ባለፈው አስራ አራት ብር ጠፋብኝ:: የንብረት ማቆሪያ ሳጥኔን አስተዋልኩት:: አልተሰበረም:: ቢሆንም የመጀመሪያ ጥርጣሬዬ ያነጣጠረው አንድ ቀላ ያለ ጢማም ወጣት ላይ ነው::  ጢማም ሲባል ደግሞ ቀላል ጢም አይደለም:: የጢም ጎፈሬ ብለው ይሻላል:: የሱ አልጋ ከኔ አልጋ በሶስት ረድፍ ወደ በሩ ይርቃል:: የህክምና ተማሪ አይደለም እያሉ ሌሎቹ ተማሪዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ:: እኔ ግን እስካሁን ቀርቤ አላነጋገርኩትም:: የተለያዩ መፍቻዎች ና ፔንሳዎች  ያሉበት አነስተኛ ሳምሶናይት መሰል ቦርሳ ዘርግቶ ሲመለከት አይቼዋለሁ:: ሳጥን መስበሪያ ቢሆንስ? ሌክቸር ላይ አላየሁትም:: ማነው? ምን እያረገ ነው የሚዉለው? የሚሉ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሱብኛል:: ይሄው ሰው በእድሜ ከአብዛኞቻችን በለጥ የሚል ይመስላል:: በሰውነትም ቢሆን ተለቅ ያለና ፈርጣማ ይመስላል:: ስፖርት ይሰራል መሰለኝ:: ከሁለት ቀናት በፊት ከዳራሹ ጥቂት ራቅ ብላ ካለች አንዲት አጭር ቧንቧ ስር በርከክ ብሎ ገላውን ሲታጠብ አይቼዋለሁ:: በቀዝቃዛ ውሃ ማለት ነው:: ማንም ሌላ ሰው እንደዚያ ሲያደርግ አላየሁም:: በምንኖርበት የሸክላ አዳራሽ አካባቢ አመርቂ የገላ መታጠቢያ ስለሌለ ቢኖርም ዉሃ አልባ ሊሆን ስለሚችል : እኔም ሆንኩ ብዙዎቹ ሌሎች ልጆች የምንታጠበው በሳምንት አንዴ ወደከተማው በመውረድ አዌቱ የተሰኝ ገላ መታጠቢያ ማዕከል ዉስጥ ነው:: አንድ ብር ያስከፍላል:: ደግነቱ ትንሽዬ የገላ ሳሙና ይሰጣሉ::


አሁንም ስለ ቀዩ ሌባ ሊሆን የሚችል ሰው እያሰብኩ ነው:: እቺን ይወዳል! እራሴው በፈጠርኩት ጥርጣሬ ስጋት ዉስጥ ገባሁ አይደል እንዴ? ቆይ አስራ አራት ብሬን የወሰደው እሱ መሆኑን ባውቅስ? ሄጄ ብሬን ስጠኝ ልለው? ኦ...አላደርገውም! ይህን ያህል እንኩዋን ደፋር አይደለሁም:: ጭራሽ ብር እንደጠፋብኝ እንዲሰማ አልፈልግም:: በቃ! ወስዶትም ከሆነ ይጥቀመው:: እንዴ! ለነዚያ ለሐረር ልጆች አስራ አራት ብር ጠፋብኝ ብዬ ነግሬያቸዋለሁ! ድንገት ከ ሌባው ጋ ቢያወሩስ? ቶሎ ብዬ ይቅርታ አርጉልኝ ሐሰት ነው እላቸዋለሁ:: 

አሁን በኪሴ ዉስጥ... ሰባ የሚሆን ሳንቲም አለ:: ከቤቴ የዛሬ አስራ አምስት ቀን ስወጣ ወደ ዘጠና የሚሆኑ ብሮች ነበሩኝ:: ዘጠና ብር በብችኛ ኃላፊነት ሳስተዳድር የመጀመሪያ ግዜዬ ስለነበር ልቤ ጮቤ ረግጦ በስንት ግዜ አንደምጨርሰው ግምቱ አልነበረኝም:: ወላጆቼንም ባይ ባይ ከማለት ውጪ መቼ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚልኩልኝ: አንዴት አንደሚልኩልኝ ምንም አይነት ውይይት ሳላደርግ ነው ወደ ጅማ የሚገሰግሰው አውቶቡስ ላይ የተሳፈርኩት:: አሁን ስለ አስራ አራት ብሩ መጥፋት ደውዬ ልንገራቸው? ወይስ አልንገራቸው? ከነገርኩዋቸው ሌላ ጥያቄ ይመጣል:: አስራ አራት ብሩ አንዴት ጠፋ ሳይሆን ዘጠናው ብር እንዴት በ አስራ አምስት ቀን ዉስጥ አስራ አራት ብር ሆነ የሚል ነው:: እውነት ግን እንዴት በአስር ቀን ውስጥ ሰባ ስድስት ብር አጠፋሁ? ወደሁዋላ ተመልሼ አውቶቡስ ላይ ከወጣሁ ጅምሮ ያከናወንኩዋቸውን ገንዘብ ነክ ድርጊቶች ለመቃኘት ሞከርኩ:: የመጀመሪያው ወጪ አዲስ አበባ ካራ ቆሬ አካባቢ ያለ ኬላ ላይ ለበላሁት ጮርናቄ ና ለጠጣሁት ሻይ የከፈልኩት ሰባ አምስት ሳንቲም ነው:: አንድ ብር እንኩዋን አይሞላም:: ወልቂጤ ላይ ምሳ: ሰኮሩ ላይ እራት እንዲሁም አልቤርጎ...አውቶቡሱ ብልሽት ደርሶበት በመዘግየቱ ጅማ ገብቼ አላደርኩም:: በማግስቱ ረፋዱ ላይ ከሌሎች እንደኔው ፍሬሽ ማን ከሚጀምሩ ልጆች ጋር ጅማ ደረስኩ:: ጥቂት ተዋውቀንም ስለነበር ምሳ አንድ ላይ በላን: ጅማ ራስ ሆቴል:: እስከዚያ ድረስ ታዲያ ከዘጠና ብሩ ላይ ያጎደልኩት ሃያ ብር አልሞላም:: በእርግጥ በ ፐርሰንት ቢሰላ የዘጠና ብሩን ሩብ ይሆናል:: ትልቁ ወጪ የራስ ሆቴል ምሳ ሲሆን ከነ ለስላሳ መጠጡ ስድስት ብር ከሃምሳ ነበር:: 

በዚህ በገንዘቡ አጠፋፍ ሃሳብ ላይ እያለሁ የቤተስብ:የሰፈሬ ና የሰፈር ጉዋደኞቼ ሃሳብ መጥቶ ድቅን አለብኝ:: የናፍቆት ጎርፍ ድንገት አጥለቀለቀኝ:: ስለአንዲት የአይን ፍቅር ዉስጥ ስለገባሁባት የሰፈር ልጅ ሁሉ አሰብኩ:: ልጅቱዋ መልኩዋ ቀይ ሲሆን ደም ግባት ምን እንደሆነ ጠንቅቄ ባላውቅም ሲባል በሰማሁት እስከ ጥግ ያላት ይመስለኛል:: ረዥም ና ሉጫ ነው ፀጉሩዋ:: ታዲያ ከዚህች ቀይ ልጅ ቀጥሎ ባይኔ ሙሉ አተኩሬ ያየሁት ይሄን ቀዩን ፀጉራም ሌባ ነው:: እርግጥ ነው ሌብነቱን ገና አላረጋገጥኩም.....

ይቀጥላል..

Wednesday, January 1, 2014

ስንጀምር

ጅ.ጤ.ሳ.  ስንጀምር

ጥቅምት ፬ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም. 


የአንደኛ አመት ሕክምና ተማሪዎች የሆንነው ወንዶች በሙሉ ታጭቀን ከምንኖርበት ከ ሸክላ የተሰራ አዳራሽ ውሃ ልክ ላይ ተቀምጬ ይህን ማስታወሻ ሳሰፍር ከስድስት ወራት በፊት የ ሃይ ስኩል ተማሪ አያለሁ ስለ ሐኪምነት የነበረኝ አመለካከት ትዝ አለኝ:: ሕፃናት ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ተብለው ሲጠየቁ በአንደኝነት "ዶክተር" ብለው በሚመልሱበት በዚህ ዘመን በኔ ህሊና ዉስጥ የነበረው የሃኪም ምስል የ ፕሮፌሰር አስራትን ሂወት ታሪክ የሚ ገልፅ "አስራት የበሽታ መቅሰፍት"በሚል ርዕስ በወቅቱ የተፃፈ የጋዜጣ ላይ ፅሁፍን መሰረት ያደረገ እንዲሁም በተመሳስይ ግዜያት ውስጥ  ያነበብኩዋቸው "አንድ ለአምስት" ና "ዶክተር ዔሪካ ቨርነር" የተሰኙ ልቦለድ መፅሀፎች ዉስጥ ያሉ ሀኪም ገፀ ባህሪዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር:: በዚያ በለጋነቴ ወቅት ሐኪምን የሳልኩት በኦፕራሲዮን ክፍል ዉስጥ ተአምር ሲሰራ የሚውል ከዚያም ወጥቶ ላቦራቶር ውስጥ በማይክሮስኮፕ ሴሎች ላይ ምርምር የሚያደርግ ከዚያም ሱፉን ለብሶ: ክራቫቱን ላላ አርጎ አውቶሞቢሉን አያሽከረከረ.........መኖሪያ ቤቱ ውስጡ ቀርቶ በረንዳው እንኩዋ የተዋበና ሰፊ.........ቅጥር ገቢው በሳር ና በአበቦች የተዋበ.........

የህክምና ትምህርት ለመማር የመጣሁበት ጅማ ጤና ሳይንስ ለማደሪያ ብሎ ለኔና ለሌሎች ቁጥራቸው ሀምሳ ለሚሆን ወጣት ወንዶች ያዘጋጀልን ግዙፍ ከሸክላ የተሰራ አዳራሽ ስለሃኪም በጭንቅላቴ የሳልኩትን ድምጥማጡን አጥፍቶታል:: በዚህ አጥር ግቢ በሚያህለው ና ጣራው ከሰማይ ትንሽ ብቻ ዝቅ በሚለው  ወለለ-ሊሾ አዳራሽ ውስጥ ተደራራቢ የብረት አልጋዎች በሁለት ትይዩ ረድፎች ጥግ ጥግ ይዘው የአግድሞሽ ተደርድረዋል:: ከየ አልጋዎቹ ፊት ለፊት ለግል ንብረት ና ልብስ ማስቀመጫ ታስበው ለያንዳንዳችን የተሰጡ ቁም ሳጥን አይሉዋቸው ቁጭ ሳጥኖች አሉ:: አነሱም ተደራራቢ ናቸው:: ባለሁለት ተካፋች የሆኑት እነዚህ ቁም-ቁጭ ሳጥኖች እያንዳንዳቸው መሃል  ለመሃል በተንጠለጠሉ በቀለም ና በአይነት እንዲሁም በግዝፈት የተለያዩ ቁልፎች ተከርችመዋል:: ዉስጣቸው የተቀመጡትን ውድ ንብረቶች ለመከላከል መሆኑ ነው:: የአዳራሹ መሃል ከአልጋ ና ከሳጥን ነፃ ቢሆንም አለፍ አለፍ ብለው የወረቀት ቅዳጆች ና ሌሎች የተለያዩ አይነት ቆሻሾች ይታዩበታል:: መረማመጃም ነው:: ቀኑን ሙሉ አይነተ ብዙ ቀጫጭንና ዉዥንብር ውስጥ ያሉ ከሚመስሉት የህክምና ተማሪዎች በተጨማሪ ከሌሎች ደፓርትመንቶች ጉዋደኞቻቸውን ለመጎብኘት የሚመጡ ተማሪዎች ይመላለሱበታል:: ብርሃን ወደ አዳራሹ የሚገባው  ከጣራው ጥቂት   ዝቅ ብለው በረድፍ በተቀመጡት መዝጊያ የሌላቸው መስኮቶች አልፎ ነው:: ቁመቱ ሶስት ተደራርበው የቆሙ ሰዎችን የሚያህለው የአዳራሹ በር ባለ ሁለት ተካፋች አረንጉዋዴ የ አንጨት መዝጊያ ያለው ሲሆን  ነፋስና መጠነኛ ብርሃን ያስገባል:: ምሽት ላይ ከጣሪያው ጥቂት ዝቅ ብለው ዙሪያውን የተንጠለጠሉ ፍሎረሰንት አምፑሎች በሙሉ ስለሚበሩ ነጭ ብርሃን ይሰፍናል:: አልፎ አልፎ የተበላሹ አምፑሎች ብልጭ ድርግም ሲሉ ይታያሉ:: አንዳንዶቹ አምፑሎች ሲበሩ የማያቁዋርጥ ጥዝዝ.. የሚል ድምፅ ያወጣሉ:: ድምፁን ሰምተው ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት የተለያዩ ነፍሳቶች ምሽት ላይ አዳራሹን ይሞሉታል:: ቢራቢሮ በማታ ለመጀመሪያ ግዜ ያየሁት እዚሕ አዳራሽ ውስጥ ነው:: ደሞ ግዝፈታቸው! ወፍ ያካክላሉ:: አይናቸውን ወዲያ ወዲህ ሲያማትሩ አያቸዋለሁ:: አንዳንዴ እንዳያዩኝ ሁሉ እፈራለሁ:: የሚመጡብኝ እየመሰለኝ:: ተለቅ ተለቅ ያሉ ጥንዚዛዎችም አሉ:: እነዚህ ሲበሩ ታዲያ ትንንሽ ሄሊኮፕተሮች እንጂ የምናውቃቸውን ጥንዚዞች አይመስሉም::  ከዳራሹ ውስጥ ሆኘ በመስኮቶቹ ወደ ዉጭ ስመለከት አንድ ያስተዋልኩት ነገር ከዳራሹ በቅርብ ርቀት ከሚገኙት ግዙፍ ዛፎች ለይ አየዘለሉ መስኮቶቹ ላይ የሚቀመጡ ዎፎች, አሞሮች ና ጉሬዛዎች አሉ:: ጉድ! አንዳንድ ግዜም ዛፎቹ በነፋስ ኃይል ጣሪያውን ያሹታል:: 

ባለፈው ሰኞ  መስከረም ፪፰ የ ፍሬሽ ማን ትምህርት ሀ ብለን ጀመርን:: ቀደም ብዬ ውዥንብር ውስጥ ያሉ እንዳልኩዋቸው ወጣቶች እኔም ዉዥንብር ዉስጥ በመሆኔ ከተማርነው እስካሁን የገባኝ ነገር የለም:: ግልፅ አልሆነልኝም:: ሳይንሱ ቢቀርና  እንዴት ጥናት አንደሚጠና ብማር ደስ ይለኛል:: ነገሩ ሁሉ ግራ ነው:: እስካሁን ሰሌዳው ላይ ፅፎ የሚያስገለብጥ መምህር አላየሁም:: ሁሉም ወደ ክፍሉ ውስጥ ከገባ ጀምሮ እስከሚወጣ ያወራል:: ሰሌዳው ላይ የሆነ ነገር ሲሞነጫጨር ይታየኛል:: አንድ እኔ ከመጣሁበት ሃይ ስኩል የመጣና አሁን የሁለተኛ ዓመት ሕክምና ተማሪ የሆነ ልጅ ይህ ሌክቸር የሚባለው እንደሆነ አጫውቶኛል:: መምህርም እንደማይባል: ሌክቸረር ወይም ኢንስትራክተር እንደሚባል አውግቶኛል:: ከሌክቸረር አፍ እየነጠቁ በፍጥነት ወረቀት ላይ ለማስፈር የሚደረገው ግብ ግብ አልተመችኝም:: ትናንትና በሌክቸር መሃል ባጋጠመኝ ድንገተኛ አልገባ ማለት ባይኖቼ ወዲያ ወዲህ ስቀላምድ አንድ ከኔ ጎን የተቀመጠ ኮስመን ያለ ወጣት "Ok": "Did you get me?" የሚሉ ሐረጎች ደብተሩ ላይ አስፍሮ አየሁ:: ይሄ በቃ እሳት ነው! አልኩ በሆዴ:: አንዱዋም አትቀረው! የጠዋቱ የ ሌክቸር ከፍለ ግዜ አብቅቶ ምሳ ከተበላ በሁዋላ ምን እንደሚደረግ ደሞ ጠፋኝ:: አብረዉኝ እኔ ባለሁበት አይነት ወጀብ ውስጥ የሚተራመሱ አናዳንድ የህክምና ተማሪዎች ላይብረሪ ውስጥ ተቀምጠው በስነስርዓት መፅሐፍ ሲያነቡ አይቻለሁ:: ወይኔ! ስለምን ይሆን የሚያነቡት? እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው....

መልካም ..ይቀጥላል

(ቀናት: ወራት ና አመታት በኢትዮጵያ አቆጣጣጠር ናቸው)