ጅ.ጤ.ሳ. ስንጀምር
ጥቅምት ፬ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.
የአንደኛ አመት ሕክምና ተማሪዎች የሆንነው ወንዶች በሙሉ ታጭቀን ከምንኖርበት ከ ሸክላ የተሰራ አዳራሽ ውሃ ልክ ላይ ተቀምጬ ይህን ማስታወሻ ሳሰፍር ከስድስት ወራት በፊት የ ሃይ ስኩል ተማሪ አያለሁ ስለ ሐኪምነት የነበረኝ አመለካከት ትዝ አለኝ:: ሕፃናት ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ተብለው ሲጠየቁ በአንደኝነት "ዶክተር" ብለው በሚመልሱበት በዚህ ዘመን በኔ ህሊና ዉስጥ የነበረው የሃኪም ምስል የ ፕሮፌሰር አስራትን ሂወት ታሪክ የሚ ገልፅ "አስራት የበሽታ መቅሰፍት"በሚል ርዕስ በወቅቱ የተፃፈ የጋዜጣ ላይ ፅሁፍን መሰረት ያደረገ እንዲሁም በተመሳስይ ግዜያት ውስጥ ያነበብኩዋቸው "አንድ ለአምስት" ና "ዶክተር ዔሪካ ቨርነር" የተሰኙ ልቦለድ መፅሀፎች ዉስጥ ያሉ ሀኪም ገፀ ባህሪዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር:: በዚያ በለጋነቴ ወቅት ሐኪምን የሳልኩት በኦፕራሲዮን ክፍል ዉስጥ ተአምር ሲሰራ የሚውል ከዚያም ወጥቶ ላቦራቶር ውስጥ በማይክሮስኮፕ ሴሎች ላይ ምርምር የሚያደርግ ከዚያም ሱፉን ለብሶ: ክራቫቱን ላላ አርጎ አውቶሞቢሉን አያሽከረከረ.........መኖሪያ ቤቱ ውስጡ ቀርቶ በረንዳው እንኩዋ የተዋበና ሰፊ.........ቅጥር ገቢው በሳር ና በአበቦች የተዋበ.........
የህክምና ትምህርት ለመማር የመጣሁበት ጅማ ጤና ሳይንስ ለማደሪያ ብሎ ለኔና ለሌሎች ቁጥራቸው ሀምሳ ለሚሆን ወጣት ወንዶች ያዘጋጀልን ግዙፍ ከሸክላ የተሰራ አዳራሽ ስለሃኪም በጭንቅላቴ የሳልኩትን ድምጥማጡን አጥፍቶታል:: በዚህ አጥር ግቢ በሚያህለው ና ጣራው ከሰማይ ትንሽ ብቻ ዝቅ በሚለው ወለለ-ሊሾ አዳራሽ ውስጥ ተደራራቢ የብረት አልጋዎች በሁለት ትይዩ ረድፎች ጥግ ጥግ ይዘው የአግድሞሽ ተደርድረዋል:: ከየ አልጋዎቹ ፊት ለፊት ለግል ንብረት ና ልብስ ማስቀመጫ ታስበው ለያንዳንዳችን የተሰጡ ቁም ሳጥን አይሉዋቸው ቁጭ ሳጥኖች አሉ:: አነሱም ተደራራቢ ናቸው:: ባለሁለት ተካፋች የሆኑት እነዚህ ቁም-ቁጭ ሳጥኖች እያንዳንዳቸው መሃል ለመሃል በተንጠለጠሉ በቀለም ና በአይነት እንዲሁም በግዝፈት የተለያዩ ቁልፎች ተከርችመዋል:: ዉስጣቸው የተቀመጡትን ውድ ንብረቶች ለመከላከል መሆኑ ነው:: የአዳራሹ መሃል ከአልጋ ና ከሳጥን ነፃ ቢሆንም አለፍ አለፍ ብለው የወረቀት ቅዳጆች ና ሌሎች የተለያዩ አይነት ቆሻሾች ይታዩበታል:: መረማመጃም ነው:: ቀኑን ሙሉ አይነተ ብዙ ቀጫጭንና ዉዥንብር ውስጥ ያሉ ከሚመስሉት የህክምና ተማሪዎች በተጨማሪ ከሌሎች ደፓርትመንቶች ጉዋደኞቻቸውን ለመጎብኘት የሚመጡ ተማሪዎች ይመላለሱበታል:: ብርሃን ወደ አዳራሹ የሚገባው ከጣራው ጥቂት ዝቅ ብለው በረድፍ በተቀመጡት መዝጊያ የሌላቸው መስኮቶች አልፎ ነው:: ቁመቱ ሶስት ተደራርበው የቆሙ ሰዎችን የሚያህለው የአዳራሹ በር ባለ ሁለት ተካፋች አረንጉዋዴ የ አንጨት መዝጊያ ያለው ሲሆን ነፋስና መጠነኛ ብርሃን ያስገባል:: ምሽት ላይ ከጣሪያው ጥቂት ዝቅ ብለው ዙሪያውን የተንጠለጠሉ ፍሎረሰንት አምፑሎች በሙሉ ስለሚበሩ ነጭ ብርሃን ይሰፍናል:: አልፎ አልፎ የተበላሹ አምፑሎች ብልጭ ድርግም ሲሉ ይታያሉ:: አንዳንዶቹ አምፑሎች ሲበሩ የማያቁዋርጥ ጥዝዝ.. የሚል ድምፅ ያወጣሉ:: ድምፁን ሰምተው ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት የተለያዩ ነፍሳቶች ምሽት ላይ አዳራሹን ይሞሉታል:: ቢራቢሮ በማታ ለመጀመሪያ ግዜ ያየሁት እዚሕ አዳራሽ ውስጥ ነው:: ደሞ ግዝፈታቸው! ወፍ ያካክላሉ:: አይናቸውን ወዲያ ወዲህ ሲያማትሩ አያቸዋለሁ:: አንዳንዴ እንዳያዩኝ ሁሉ እፈራለሁ:: የሚመጡብኝ እየመሰለኝ:: ተለቅ ተለቅ ያሉ ጥንዚዛዎችም አሉ:: እነዚህ ሲበሩ ታዲያ ትንንሽ ሄሊኮፕተሮች እንጂ የምናውቃቸውን ጥንዚዞች አይመስሉም:: ከዳራሹ ውስጥ ሆኘ በመስኮቶቹ ወደ ዉጭ ስመለከት አንድ ያስተዋልኩት ነገር ከዳራሹ በቅርብ ርቀት ከሚገኙት ግዙፍ ዛፎች ለይ አየዘለሉ መስኮቶቹ ላይ የሚቀመጡ ዎፎች, አሞሮች ና ጉሬዛዎች አሉ:: ጉድ! አንዳንድ ግዜም ዛፎቹ በነፋስ ኃይል ጣሪያውን ያሹታል::
ባለፈው ሰኞ መስከረም ፪፰ የ ፍሬሽ ማን ትምህርት ሀ ብለን ጀመርን:: ቀደም ብዬ ውዥንብር ውስጥ ያሉ እንዳልኩዋቸው ወጣቶች እኔም ዉዥንብር ዉስጥ በመሆኔ ከተማርነው እስካሁን የገባኝ ነገር የለም:: ግልፅ አልሆነልኝም:: ሳይንሱ ቢቀርና እንዴት ጥናት አንደሚጠና ብማር ደስ ይለኛል:: ነገሩ ሁሉ ግራ ነው:: እስካሁን ሰሌዳው ላይ ፅፎ የሚያስገለብጥ መምህር አላየሁም:: ሁሉም ወደ ክፍሉ ውስጥ ከገባ ጀምሮ እስከሚወጣ ያወራል:: ሰሌዳው ላይ የሆነ ነገር ሲሞነጫጨር ይታየኛል:: አንድ እኔ ከመጣሁበት ሃይ ስኩል የመጣና አሁን የሁለተኛ ዓመት ሕክምና ተማሪ የሆነ ልጅ ይህ ሌክቸር የሚባለው እንደሆነ አጫውቶኛል:: መምህርም እንደማይባል: ሌክቸረር ወይም ኢንስትራክተር እንደሚባል አውግቶኛል:: ከሌክቸረር አፍ እየነጠቁ በፍጥነት ወረቀት ላይ ለማስፈር የሚደረገው ግብ ግብ አልተመችኝም:: ትናንትና በሌክቸር መሃል ባጋጠመኝ ድንገተኛ አልገባ ማለት ባይኖቼ ወዲያ ወዲህ ስቀላምድ አንድ ከኔ ጎን የተቀመጠ ኮስመን ያለ ወጣት "Ok": "Did you get me?" የሚሉ ሐረጎች ደብተሩ ላይ አስፍሮ አየሁ:: ይሄ በቃ እሳት ነው! አልኩ በሆዴ:: አንዱዋም አትቀረው! የጠዋቱ የ ሌክቸር ከፍለ ግዜ አብቅቶ ምሳ ከተበላ በሁዋላ ምን እንደሚደረግ ደሞ ጠፋኝ:: አብረዉኝ እኔ ባለሁበት አይነት ወጀብ ውስጥ የሚተራመሱ አናዳንድ የህክምና ተማሪዎች ላይብረሪ ውስጥ ተቀምጠው በስነስርዓት መፅሐፍ ሲያነቡ አይቻለሁ:: ወይኔ! ስለምን ይሆን የሚያነቡት? እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው....
መልካም ..ይቀጥላል
(ቀናት: ወራት ና አመታት በኢትዮጵያ አቆጣጣጠር ናቸው)
No comments:
Post a Comment