ጥቅምት ፪፭ ፩፱፰፫ አ.ም. ከምሽቱ ሰባት ሰዓት
በዚህ ሰዓት የ ፍሬሽማን ትምህርት ሞቅ ያለ ሲሆን የኔ የሰፈር ና የ ቤተስብ ናፍቆት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከስሟል:: የጤና ሳይንሱ ኑሮ ተስማማኝም ልበል? የግቢው ማህበረ-ነፍሳት አባላት የሆኑት ቢምቢዎች ሰውነቴን ነካክሰው የጣሉብኝ ጉብ ጉቦች ሁሉ ጠፉልኝ:: ጥሩ ነው መቼም...ግና ያው የኔ የሆኑት ራስ አመጣሽ የሀሳብ እክሎች ና ጉርብጣቶች እንደቀጠሉ ናቸው:: ከነዚህ የሚቆርቁሩ እሳቤዎች አንዱ ራሴ ያወጣሁትን ፕላን በስራ ላይ አለማዋሌ ነው:: ማስታወሻዬ: ፕላን ስል ደግሞ ትልቅ ነገር አይምሰልሽ:: መቼ ሂሳብ: መቼ እንግሊዝኛ: መቼ ባዮሎጂ.. ወዘተ እንደማጠና የሚገልፅ ሰንጠረዥ ማለቴ ነው:: በያንዳንዱ የትምህርት አይነት ያወቅነው እየበዛ የሄደ ሲሆን የትየለሌ የሆነብኝ ግን ገና ልናውቅ የሚገባን ነው:: እንግዲህ ይህን ልናውቅ የሚገባንን ነው ተቀምጠን መፃሕፍት ላይ አይናችንና ቀስረን ለዘለቄታው የምናውቀው ይሆን ዘንዳ በግብረ ህሊና እንድናትመው ኃላፊነት የተጣለብን:: ሌላው እንግዲህ የሚጠበቅብን ነገር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የ ትውስታ ማህደራችንን መክፈት ነው:: አሁን ይሄን ሁሉ እንዴት ነው ማስታወስ የሚቻለው?
ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ትንሽ ከፍ ብሎ በሚገኘው ሌክቸር ሆል ውስጥ ከኮርኒሱ ላይ ከላይ እስከ ታች የተገጠገጡትን ፍሎረሰንት አምፑሎች አብርተን እኔና እኔን መሰል የፍሬሽ ማን ህክምና ተማሪዎች ምሽቱን ስናነብ አንዳንዶቻችንም ስናንጎላጅ እንቆያለን:: የእውነት እንቅልፉ የመጣበት ቶሎ ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ይሄዳል ለመተኛት ወይም አልጋ ላይ ለማንበብ ለመሞከር (እኔ በብዛት እንደማደርገው):: የበረታ ደግሞ እስከ ምሽቱ ሰባት ወይም ስምንት ብሎም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይቆያል::
ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ትንሽ ከፍ ብሎ በሚገኘው ሌክቸር ሆል ውስጥ ከኮርኒሱ ላይ ከላይ እስከ ታች የተገጠገጡትን ፍሎረሰንት አምፑሎች አብርተን እኔና እኔን መሰል የፍሬሽ ማን ህክምና ተማሪዎች ምሽቱን ስናነብ አንዳንዶቻችንም ስናንጎላጅ እንቆያለን:: የእውነት እንቅልፉ የመጣበት ቶሎ ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ይሄዳል ለመተኛት ወይም አልጋ ላይ ለማንበብ ለመሞከር (እኔ በብዛት እንደማደርገው):: የበረታ ደግሞ እስከ ምሽቱ ሰባት ወይም ስምንት ብሎም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይቆያል::
በቀደም ለት የባዮሎጂና የኬምስትሪ ላቦራቶሪ ረፖርት ውጤት ሲታደለን እኔ ሁለቱንም አስር ከአስር ነበር ያገኘሁት:: ብርታት ብጤ ተሰምቶኛል:: ያን ብርታት የተቀዳጀሁ ቀን ታዲያ ሌላ የባዮሎጂ ላቦራቶሪ ክፍለ ግዜ ነበር::አላማው የእንሰሳትና የእፅዋትን ሴሎች በአጉሊ መነፅር ማየት ነበር:: ክጉንጫችን የውስጥ ክፍል ላይ በስንጥር ጫር አርገን በእንሰሳ ሴልነት እንድናቀርብ ኢንስትራክተሩ የነገረን ሲሆን ከኔጋ አጉሊ መነፅር የምትጋራው ሴት ልጅ ግን ጉንጭዋን ለመጫር የፈራች ይመስል ስታመነታ አየሁዋት:: ታዲያ እኔ ወንዱ አለመፍራቴን ለማሳየትም ይሁን ያ አስር ከአስሩ ውጤት የሰጠኝ የልብ ልብ ጉንጬን በውስጥ በኩል በኃይለ ጣት ጫርኩት:: ድርጊቱን ስለደጋገምኩት ጫጫርኩት ብለው ይሻላል:: በመጀመሪያ ከጥፍሮቼ ሁሉ ረዝማ በምትታየው በቀኝ ትንሹዋ ጣቴ ጥፍር የጫርኩትን ስንመለከተው ሌላ ነገር ሆኖ ተገኘ:: ከዚያ በስንጥር ጉንጬ ተልጦ እስከሚደማ ደጋግሜ በመጫር በመጨረሻ ተሳክቶልን Epithelial Cell አየን::
በዚያው ሰሞን ወደ አዲሳባው ቤታችን ስልክ መታሁ:: አባቴንና እናቴን አነጋገርኩዋቸሁ:: ገንዘብ ስጡኝም አልኩዋቸሁ:: ባጋጣሚ ቤተሰቦቼ ካሉበት ሰፈር ወደ ጤና ሳይንሱ የሚመጣ ተማሪ ስለነበር በሱ በኩል ገንዘብና ለመፃፍ የሚያያገለግሉኝ በርካታ ብዕሮች ተላኩልኝ:: ቤተሰቤ ዉስጥ ያሉ ልጅ አዋቂ ሳይባል እናቴን ጨምሮ: ከጎረቤትም አንዲት ልጅ ደብዳቤ ላኩልኝ:: አባቴ ደግሞ ግለሰብ ዝንጉ ነው በሚል የኢትዮጵያ ፖስታ አግልግሎት ድርጅትን በመጠቀም የላከው ዳብዳቤ በጅጤሳ የተማሪዎች ዲን ፅህፈት ቤት በኩል መጣ:: ምን ቢሆን ጥሩ ነው ታዲያ:: ምንም አልመሰለኝም:: ከ አንድ ወር በፊት ቢሆን ጮቤ የሚያስረግጠኝ ነበር:: ከላይ እንዳልኩት የቤተሰብ ናፍቆት ጭምብል ከላዬ ላይ ወልቆ ነበር....
No comments:
Post a Comment