ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ - አሁንም አልጋዬ ላይ
ትናንትና ከደቡብ እዝ ሙዚቃ ዝግጅት በሁዋላ ወደ ብላቴ አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ቁጥራቸው ወደ ስልሳ በሚጠጋ አውቶቡሶች ተጭነው ደረሱ:: የሐይ ስኩል ጉዋደኛዬ ከፈለኝ መምጣቱን ከሰው ሰማሁ:: ከፈለኝ በጣም የቅርብ ጉዋደኛዬ ነው:: ከ ማትሪክ በሁዋላ እኔ ወደ ጅማ ስሄድ እሱ ጎንደር ሄደ- ሁለታችንም ሕክምና ለማጥናት:: በእርግጥ የጎንደር የህክምና ተማሪዎች የመጀመሪያ ዓመት ኮርሶቻቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚወስዱ በመሆኑ ከፈለኝ የመጣው ካዲሳበባ ነው:: ገና አላገኘሁትም:: እስካየው ቸኩያለሁ..
ዛሬ በወታደራዊው ደንብ መሰረት ስራችንን የጀመርነው ከሌሊቱ ፩፩ ሰዓት ነው:: ጠዋት ጠዋት አየር ወለዶቹ ዱብ ዱብ ያስብሉናል:: ለሰውነት ጥንካሬና ወባን ለመከላከል ጥሩ ነው ይላሉ:: ባለፉት ቀናት ይጫጫነኝ የነበረው የቀን እንቅልፍ እየተወኝ ነው ስለው እንደገና ጀመረኝ :: ማቅለሽለሽም ነበረኝ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ትቶኛል::
መጋቢት ፪፬ ፩፱፰፫ አ.ም.
......................ትናንት ከፈለኝን ያለበት አንደኛ ብርጌድ ድረስ ሂጄ አገኘሁት::
እውነተኛውን የውትድርና ትምህርት ዛሬ ጀመርን:: የብዙ ተማሪዎች ከወታደራዊ ስነስርዓት ውጭ መሆን (የአንዳንዱ እንደውም ከሲቪል ስነስርዓትም ጭምር ውጭ መሆን) አየር ወለድ አሰልጣኞቻችንን ተፈታተናቸው: አስቆጣቸው! ዛሬ በምሳ ሰዓት አንዳንድ ተማሪዎች የራሳቸውን ቅርጥፍ አድርገው ከበሉ በሁዋላ እዚያው በቆረጣ ሰልፍ ይዘው እንደገና ወደ ሜንስ ቤቱ በመግባት በፈፀሙት የድጋሚ መብላት ድርጊት (አፈር ይብሉና) ሌሎች ክፍላቸው ሆነው በስነሥርዓት ተራ ይጠብቁ የነበሩ ተማሪዎችን ሳይበሉ ለመዋል ዳረጋቸው:: ይህን ተከትሎ ከሰዓት በሁዋላ የኛ ብርጌድ አዛዥ የሆነው ሻምበል ኦልቀባ ለታ እጅግ በጣም በመበሳጨቱ ፎሌን ቆጠራ ላይ አንዳንድ ጠንካራና የንዴት ቃላት ሁላችንም ላይ አወረደብን:: በሁዋላ እንደሰማሁት በየብርጌዱ በተመሳሳይ ሁኔታ አየር ወለዶች በብስጭት ተማሪውን ሲናገሩ ና ሲጮሁበት ነበር አሉ:: ባለፈው እንዳልኩት በጫማ ጥፊና በርግጫ ቢሉን ደስ ባላቸው ግን ""ጫፋችንን እንዳይነኩ" ታዘዋል::
ንዴትና ብስጭት ሰፍኖበት የነበረው ከሰዓት ተጠናቆ ደንገዝገዝ ሲል እራት ደሞ በላን:: አሁን በሥርዓት ነበር የተበላው:: ግን እንጀራዋ አነሰች::
ጊዜያዊ መፀዳጃ ና ገላ መታጠቢያ ቤቶች ከእንጨት ባፋጣኝ እየተሰሩ ነው:: ይህም ለብላቴ አዲስ ነው:: ከዚህ በፊት ሰልጥነው የወጡት ወታደሮች በሙሉ የሚፀዳዱት ዙሪያቸውን ካለው ቆንጥርና ጫካ ውስጥ ሲሆን የሚታጠቡትም ወንዝ ውስጥ ነበር መሰለኝ:: የ ኮሌጅ ተማሪ ወታደር ግን "ሞልቃቃ" ነው::
በነገራችን ላይ ዛሬ ማታ ከራት በሁዋላ ወታደራዊ ትምህርት ነበረን:: አርእስቱ በጭለማ ስለማጥቃትና ስለመከላከል ሲሆን በገለፃ የታገዘ ነበር:: ገለፃ ስል ግን የውሸት አይደለም ሁሉም ነገር እውነተኛ ነበር:: ላውንቸር ሲተኮስ በቅርብ አየሁ:: በርካታ አብሪ ጥይቶች ተተኮሱ:: ፈንጂዎችም ፈነዱ:: ከየክፍላችን ተነስተን ወደገለፃው ስፍራ ስንሄድ የነበረው ጨለማ እጅግ በጣም ድቅድቅ ስለነበር እጅ ለጅ ተያይዘን ነበር የምንራመደው....
No comments:
Post a Comment