Wednesday, May 28, 2014

ብላቴ 4



መጋቢት ፪፱ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም.
የብላቴ ፋሲካ ና የኔ መከፋት

*ስለዛሬው ቀን ከማወራ ይልቅ በትናንትናው እለት ከየኮሌጁ የመጡ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች አዘጋጅተውት ስለነበረው የትንሣዔ ዋዜማ ክብረ በዓል በጥልቀት ብተነትን ደስ ባለኝ:: ነገር ግን ዝግጅቱ በጣም የጎላ: የግድ ትዝታ የሚጥል  ና ባልፅፈውም እንኩዋን ልረሳው የማልችል መስሎ ስለተሰማኝ ያለብዙ ብእር በትንሹ ብቻ ነካ አድርጌ ላልፈው ወሰንኩኝ:: ከሁሉም ከሁሉም ክርስትያኞቹ የስቅለት ዝማሬና ወረብ በሚያከናውኑበት ጊዜ እንደከበሮ የተጠቀሙት እውነተኛ ከበሮ ሳይሆን ለውሃ ማስቀመጫ ተብለው ለየጉዋዱ የታደሉ ጀሪካኖችን መሆኑን ልብ በል/ይ:: ክብረ በዓሉ የተካሄደበት የመሰብሰቢያ ኬስፓን ለወትሮው ሙቀት ለመቀነስ በሚል ከውስጡ በጥጥ አንኩዋሮች የተለበጠ ቢሆንም ትናንትና ግን በአሉን ምክንያት በማድረግ ከጥግ እስከ ጥግ በተወጠሩ የሰልጣኝ ተማሪዎች አንሶላዎች ተሸፍኖ ነበር:: ጧፍ በብዛት ነበር: ከየት እንደመጣ ባላውቅም:: ማርያም ልጇን ክርስቶስ እየሱስን አቅፋ ያለችበት ትልቅ ስዕል ዳር ዳሩን ነጠላ ለብሶ መድረኩ ላይ ይታይ ነበር:: ስዕሉ ፊትለፊትና ዙሪያ ሻማዎች ና ጧፎች ይበሩ ነበር:: ሰልጣኝ ተማሪ ግጥም ብሎ ነበር:: አሁንም ከየት እንደመጣ የማላውቀው ቤተክርስትያን በሄድኩባቸው ጥቂት የቀድሞ ጊዜያት ሽታውን የማስታውሰው እጣን ና ነድ ክፍሉን አውዶት ነበር:: "አማን በአማን" የሚለው የትንሣዔ መዝሙር ሲዘመር ብዙ ተማሪዎች ጥልቅ ስሜት ውስጥ ገብተው እንደነበር አስተውያለሁ:: በዚያ የፍሎረሰንት ነጭ ብርሃን በሰፈነበት አዳራሽ ውስጥ ክብ ሰርተው በስሜት የሚዘምሩ ተማሪዎች ብዙዎቹ ላብ በላብ ሆነውና አይኖቻቸው ሰፍተው በአካል በዚያ ቦታ ላይ ይሁኑ እንጂ በመንፈስ መጥቀውና ና ተለይተው: በጋራ በሚሰማው ጉልህ ዝማሬ  ውስጥ የያንዳንዱ ጮህ ማለት የሚታወቀው አንገቶታቸው ላይ ባሉት የተወጠሩ ደም ስሮቻቸው አማካይነት ነበር.....በዕለቱ የጅማ ጤና ሳይንሶቹን ጨምሮ መንፈሳዊ ትምህርት የመስጠት ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ከየኮሌጁ የመጡ አውራ ኦርቶዶክስ አማኞች እንዲሁም አንኩዋር ዲያቆናት በብዛት ነበሩ:: አቤት የመዝሙር መዓት! እርግጠኛ ነኝ በብላቴ ታሪክ እንዲህ አይነት መንፈሳዊ ስብሰባ ተደርጎ አያውቅም.........ይህ ታዲያ ትናንት አለፈ

በአንፃሩ የዛሬው ቀን እጅግ የከፋ ነው:: በፋሲካ ቀን ከቤቴ ውጭ በጣም ርቄ የሰው ልጅ ብዙም የማይደርስበት ጫካ ውስጥ ነኝ:: ውስጥ ቢሆኑ ሙቀቱ አቅላጭ: ውጭ ቢወጡ እንዳውም ፀሀዩዋ ተጨምራ የምትቀውር: እሩቅ ልመለከት ቢባል አፈር የለበሰ ሜዳ ላይን እስኪታክት: በቆንጥር ተከትሎ ብሎም ተራራ....ፍፁም ደስ ያማይልና ተስፋ የሚሰርቅ ሁኔታ:: ሙት ሙት የሚል ቀን ነው የሆነብኝ:: የልቤ ምት እንዲሁም የህልውና መሻቴ ቁልቁል ወረደብኝ:: ደበረኝ:: ሕክምናም ሆነ አማካሪ የሌለው ነገር-በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ሌላም በርካታ እንደኔ የደበራቸው ተማሪዎች አሉ:: ነገ መጥቶ ያው የተለመደው ወታደራዊ ትምህርት እስከሚቀጥል ቸኮልኩ:: ይገርማል ወታደራዊ ትምህርት ከሌላ ነገር ተሽሎ ተገኘ......ያለፈውን ዓመት የቤታችንን ፋሲካ አስታወስኩ:: የማትሪክን ፈተና ወስጄ: ከደብተርና ከጥናት ነፃ ሆኘ የአዲስ አበባ በጋ ከመግባቱ ሁለት ወር ቀደም ብሎ ብዙም ባልሞቀ ና ብዙም ባልቀዘቀዘ ነፋሻ አየር በጣም በተረጋጋ ና ሂወት በተሞላ ሁኔታ ነበር ፋሲካን ያሳለፍኩት.....

አሁን ደግሞ ቆም አልኩና ብላቴ ከመጣሁ ጀምሮ ስለሚሰሙኝ አዳዲስ ስሜቶች አሰብኩ:: በራሴ ፍላጎት ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት የሆኑ የፀባይ ለውጦች እያሳየሁ ይመስለኛል:: ከተስፋ መቁረጥ የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ:: ለምሳሌ ቀልድ አስጠልቶኛል:: ከባድ ነው ቀልድ ፈርቶ ከሰው ጋ ተደባልቆ መኖር: አብረው የማይሄዱ ነገሮች:: ዝም ማለት እፈልጋለሁ:: ታየኝ እኮ እኔ ዝም ስል:: ለብቻዬ መሆንም አማረኝ:: ይሄም አጉል ይመሰለኛል:: መገረም ትቻለሁ:: ለራሴና ለጤናዬ የማደርገው ጥንቃቄ ቀንሷል....


*አንባቢ ሆይ ዛሬ ላይ ሆኘ ዘመን በፈጠረው ድረ ገፅ ከላይ ያለውን ፅሁፍ ከማስተወሻ ደብተሬ ላይ ስገለብጥ ና በምልሰት ግዜውን ስቃኝ በማስታወሻው የመጀመሪያ አንቀፅ ውስጥ የሰፈረው ሁነት የሆነበት ቀን ማህበረ ቅዱሳን የተባለው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ስብስብ የተመሰረተበት እለት እንደሆነ አስታወስኩ:: ይህ ትክክል ካልሆነ አርመኝ::

No comments:

Post a Comment