Tuesday, September 16, 2014

ብላቴ 9

ወጥቶ-አደር

ሚያዚያ 21 1983 አ.ም.

ሰሞኑን የመጻፍ ስሜቴ ቀዝቅዞ ስለነበር ሳልጽፍ ብዙ ቆየሁ መሰለኝ። የኢትዮጵያ ሁኔታ በየሰኮንዱ መለዋወጡን ቀጥሏል። ጦርነቱ እየከፋ መጥቷል። ብላቴ ውስጥ የሚንሽራሸሩት ወሬዎችም አይነታቸው የትየለሌ ሆኗል። ወሬዎቹ ዋነኛ ባህሪያቸው ጆሮ መንዘር ነው። በንዝረቱ ሃይል ብሎም ስለወሬው የበለጠ ለማወቅ በሚደረግ አላስፈላጊ ጥረት የሽብር ጽዋ መጎንጨት የተለመደ ነገር እየሆነ ነው። ከወሬዎቹ የተወሰኑት ምንጫቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዜናዎች ናቸው። አልፎ አልፎ አንዳንድ ተማሪዎች ራሳቸውን ለማጽናናት ይሁን ለሌላ ጥሩነቱ ከገደብ ያለፈ ወሬ ያወራሉ። ከነዚህ ወሬዎች ውስጥ “በቅርቡ ይህን ማሰልጠኛ ጣቢያ እንለቃለን፡ ሌላ 35 ሺ ጦር እኛን ተክቶ ለመሰልጠን እየተዘጋጀ ነው” የሚሉ ይገኙባቸዋል። እንደዚህ አይነት ወሬ ታዲያ ወደ ጦርነት ያለመዝመትን ምስራች ተርቦ ላለው የግቢው ሰልጣኝ ተማሪ (በሙሉ ማለት ይቻላል) ጥሩ ምግብ እንደማለት ነው። ስልጠናው ግን እንደቀጠለ ነው።

አየር ወለዶቹ የተማሪውን አልምጥ ጸባይ እየለመዱት ሄደዋል። የጠዋት ስፖርትም ሆነ ዋናውን የተግባር ስልጠና እንድንሰራ ማስገደዳቸውን አቆሙ። ሞራል አውጡ (ወደ ስልጠናው ቦታ በጋራ እየዘፈናችሁ ሂዱ) የሚባለውም  ነገር ቀረ። የሚገርመው ግን ተማሪው ደሞ በራሱ ግዜ ሞራል እያወጣ መሄድ ብቻ ሳይሆን በስልጠናው ላይ በብዛት መገኘት ጀመረ። እኔ በበኩሌ የጠዋቱን ስፖርት ሙሉ በሙሉ የተውኩት ሲሆን ስልጠናውና ወደ መስክ የሚደረገውን የእግር ጒዞ ግን ለምጄዋለሁ።

ሚያዚያ 22 1983 አ.ም.

በዛሬው እለት ስልጠና ላይ እያለን አንድ አስቀያሚ ነገር ተከሰተ። የእለቱ ስልጠና አይነት “በጓድ መከላከል” የሚል ነበር። የአምስተኛ ብርጌድ ተማሪ ሁሉ ቡቄሳ ተራራ ፊት ለፊት ተኮልኩሏል። የጠዋት ጸሃይ ፍንትው ብላ ወጥታለች። የቃል ትምህርት ከተሰጠን በኋላ በገለጻ ደግሞ መመልከት ስለነበረብን ገለጻውን የሚያሳዩት አየርወለዶች ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። የተለያዩ አይነት መሳሪያዎች ይዘዋል፡ ኤ.ኬ.ኤም፡ ክላሺንኮቭ፡ላውንቸር፡መትረየስና፡ቦምብ ። ገለጻው ተጀመረ....

የጠላትን እንቅስቃሴ ዛፍ ላይ ሆኖ እየቃኘ ለጓድ መሪው ተናጋሪ ሆኖ የሚጫወተው አየርወለድ ሲናገር ከሩቅ ይታየኛል ግን ምን እንደሚል አይሰማኝም። በገለጻው መሰረት ጓድ መሪው ዛፍ ላይ ያለው ወታደር የሚነግረውን ተንተርሶ የተለያየ መሳሪያ ለያዙት የጓዱ አባላት የ “ተኩስ!” ተእዛዝ ይሰጣል። ገለጻ ቢሆንም ተኩሱና መሳሪያዎቹ ግን እውነተኛ እንደሆኑ ልብ በል/በይ። በእርግጥ እልምታቸው ባዶ ተራራ ላይ ነው....ቡቄሳ ተራራ..

የ.ኤ.ኬ.ኤም ጥይቶች መንጣጣት ጀመሩ። የቡቄሳ ተራራን ደረት ደበደቡት። አካባቢው በድምጸቱ ተናጋ። “ተመስገን ልምምድ ነው” አልኩ በሆዴ። ቀጥሎ ደግሞ ዛፍ ላይ ያለው አየር ወለድ ለኔም ሆነ ለሌላው ተማሪ በሚሰማ ጎላ ያለ ድምጽ “የጠላት ታንክ በቅርብ ርቀት ይታየኛል!” አለ። በዚህ ግዜ ጓድ መሪው “ ላውንቸር ተኳሽ 5 ቁጥር፡ በራስህ ጊዜ አልመህ፡ አነጣጥረህ የጠላትን ታንክ ደምስስ!” አለ። ከመቅስፈት በሚያንቀጠቅጥ ሃይለኛና ከፍተኛ የድምጽ ማእበል አካባቢው ተዋጠ። ብዙዎቻችን ወደመሬት አጎነበስን።


ገለጻው ቀጠለ..ዛፍ ላይ ያለው አየር ወለድ “የጠላት እግረኛ ወታደር በ 50 ሜትር ርቀት ላይ!” በማለት ጮሆ ተናገረ፡፡ ጓድ መሪው ተቀብሎ “ቦምብ አዘጋጅተህ ወርውር...” ሲል አሁንም ከፍተኛ ድምጽ ና አቧራ የፈጠረ የ ቦምብ ፍንዳታ ተሰማ። ቦምቡ የደፈነዳበት ስፍራ ላይ አንድ ሄልሜት የቦምቡ ፍንዳታ ከፈጠረው አቧራ ጋ ወደሰማይ ሲወረወር  ተመለከትኩኝና ሰውነቴን የሚቀፍ ነገር ወረረኝ። ሰቀጠጠኝ። ወዲያው “የተጎዳ ሰው አለ መሰለኝ!” የሚል ድምጽ ከበስተጀርባዬ ሰማሁ፡፡ ስለ ገለጻው ሌክቸር ይሰጥ የነበረው አየር ወለድ ያለምንም የተለየ ስሜት ንግግሩን ቀጠለ። የተማሪው ሁሉ ቀልብ ግን ቦምቡ የፈነዳበት ቦታ ላይ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን ቦምቡ ከፈነዳበት አካባቢ እሪታ መሰል ድምጽ ተሰማ....የእርዳታ ጥሪ ነው...ቦምብ ወርዋሪው በእርግጥም አደጋ ደርሶበታል፡ የአደጋውን ምንነት ባላውቅም። ተማሪዎች በሙሉ አጉረመረምን። አካባቢዬ ቆመው የነበሩ አየር ወለዶች አንገቶቻቸውን ደፉ። “ከዚህ በኋላ ገለጻ ይቅር! አንፈልግም በቃ!” የሚሉ ድምጾች አልፎ አልፎ ከተማሪው መሃል ተሰሙ። ትንሽ ቆይቶ አንድ አየርወለድ ሻምበል፡ እጁን እያጨበጨበ ጮህ ብሎ “እንደማመጥ!” አለ። ከዚያም ጉርምርምታው ጋብ ሲል “ምናልባት እናንተ አጋጥሟችሁ ላያውቅ ይችላል። እኛ ግን በየጊዜው የምናየው ነገር ነው (የቦምቡን አደጋ ማለቱ ነው) ። ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ስህተቶች ይፈጠራሉ። ህይወትም ሊጠፋ ይችላል። የዛሬውም ሁኔታ እንደዚያው ነው። ልጁ በወቅቱ የቦምቡን ዘንግ በእሳት ካቀጣጠለ በኋላ ዘንጓ ተቀጣጥላ እስክታልቅ ስለጠበቃት ከእጁ ገና እንደወረወራት ነው የፈነዳችው፡ በዚህም እጁ ሊቆረጥ ችሏል። ህይወቱ ግን ተርፏል። “እና ገለጻውን እንቀጥላለን።” አለ......

Wednesday, September 10, 2014

ብላቴ 8

ሚያዚያ አስራ አንድ  አስራ ዘጠኝ ሰማንያ ሦስት - አርብ 

ነጎድጉዋድ  

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከ ሀምሳ አራት ደቂቃ 
ክብርት ማስተወሻዬ ሆይ: ከዚህ በፊት ከራሴ አልፌ ስለ ሀገር ጉዳይ በቁም ነገር ፅፌ ባላውቅም የጊዜው የኢትዮጵያ ሁኔታ ስለ ሀገር እንድፅፍ እያስገደደኝ ነው:: በዚህ ወቅት በተለያየ መስመር የሚሰማው ወሬ ልክ ከገመድ ወደ ገመድ እንደሚተላለፍ  የኤሌትሪክ ኃይል ከሰው ወደ ሰው እየሄደ የሚነዝር እንዲሁም ፍርሃትና ውስጣዊ ሽብር የሚያጎናፅፍ ነው:: አልፎ አልፎ ከዚህ ከብላቴ ሳልወጣ እቀር ይሆን የሚል ሃሳብ በአይነ ህሊናዬ ውልብ ይላል:: ስልጠናችንን ያለምንም የፕሮግራም መዛባት እያካሄድን ቢሆንም በቀኑ መጨረሻ ላይ የሚሰማው ወሬ ክብደት ያለውና የነገሮችን ትክክል አለመሆን የሚያመላክት ነው:: ትክክል ያልሆነው ምን እንደሆነና የት እንደሆነ ግን አላውቅም::

በዛሬው እለት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ለሕዝብ ንግግር ስለሚያደርጉ በኢትዮጵያ ያሉ መስሪያ ቤቶች በሙሉ ዝግ ናቸው:: እኛም ሰልጣኞች እሳቸው ሲናገሩ እንድናያቸው ና እንድናዳምጣቸው ተብሎ ወደ መስክ ስልጠና በመሄድ ፈንታ አንድ ዛፍ ጥላ ስር ያለ ስቅል ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠን የንግግሩን መጀመር እየጠበቅን ነው:: ንግግሩ ባልተጠበቀና ባልተገመተ ግዜና ሰዓት የመጣ ስለነበረ ሁሉም ሰው ለንግግሩ ከመጉዋጉዋት ባሻገር ስለንግግሩ የራሱን ትንቢት ያስቀመጠ ይመስለኛል: በኔ ግምት ንግግሩ በስልጣንና በኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው የሚሆነው:: ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ይለቃሉ ብዬ አልገምትም::

ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ትንሽ ቆየት ብሎ...
ሦስት ሰዓት በፈጀ ንግግራቸው ተናገሩ ብዬ የምመሰክረው አንድ ቁም ነገር ቢኖር "ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጅ እስከሆነ ድረስ ስልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ" የሚለው  ነበር:: ነገሩ ግን ላስለቃቂ ካንበሳ መንጋጋ ማን ያወጣል ስጋ ለለቃቂ የነብር ጭራ እንደሚባለው በቃላት ተውቦና ደምቆ ቢነገርም በተግባር ፈፅሞ የማይደፈር ...ነው ከ ፕሬስዳንት መንግስቱ ስልጣን መውሰድ:: ብዙ ተማሪ ንግግሩን ሙሉ በሙሉ ና ካሁን ካሁን ጠቃሚ ነገር እሰማል ይሆን በሚል በጉጉት ያዳመጠ ሲሆን በንግግሩ መጨረሻ ግን ፈታ ያለ ፊት ማየት ተስኖኝ ነበር.....

Thursday, September 4, 2014

ብላቴ 7


ሚያዚያ ስምንት አስራዘጠኝ ሰማንያ ሦስት

ቁማር....

ኣሁን እኩለ ለሊት ካለፈ 58 ደቂቃ ነው፥፥ ቅድም ልክ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ ቁማር ቆምሬ የበላሁትን 60 ብር ይዤ ወደ መኝታ ክፍሌ መጣሁ፥፥ ሰሞኑን ቁማርን በፍቅር  እየተጫወትኩ ነው፥፥ ግን ገንዘብ ለማግኘት ብዬ እንዳልሆነ እኔና አግዚአብሄር ነን የምናውቀው፥፥ የምሰራው ሌላ ነገር ሰለሌለ የሚገዳደረኝን ዳተኝነት ለመግታት እንዲሁም ጊዜ ለመግደል ስል ነው እንጂ.... ምንም ኣይነት የመቆመር ልምድ የለኝም:: በእርግጥ በልጅነቴ ሰፈር ዉስጥ ብይ ና ዘውድ-ጎፈር ትንሽ ተጫውታለሁ። ፥፥ መቆመሪያው ዶርም ከኔ ዶርም ርቆ የሚገኝ ሲሆን፥ ብዙዎቹ ተጫዋቾች ልምድ ያላቸው ቁንጮ ቆማሪዎች ናቸው። አንዳንዶቹ በድሜ ከኔ የገፉ ጡንቸኛና ጉልበተኛም ሊሆኑ ይችላሉ፥፥ ሸዋጆችም በሽ ናቸው፥፥ እኔ በበኩሌ ብዙውን ግዜ ምንም ኣይነት ስልት ወይም ማሰላሰል ሳይታከልበት ከየት እንዳመጣሁት በማላውቀው ድፍረት ንዘብ ኣሲዛለሁ፥፥ ለነገሩ ጨዋታው ማሰላሰል የሚጠይቅ አይደለም፡ ብዙውን ግዜ ወጣ-ገባ የሚባለው ነው፥፥ በዚህ መሰረት ኣንደኛው ተጫዋች ከካርታ ክምር ውስጥ ኣንዲት ስቦ ቁጥሩን ለተቀናቃኙ ሳያሳይ ይይዛል፥፥ ተቀናቃኙ ካርታዎችን በየተራ ካርድ መዛዥ  ራሱ ፊት ለፊት ይጥላል፥፥ ካርድ መዛዥ የያዘውን አይነት ካርታ ፊትለፊቱ የወደቀለት ኣሸናፊ በመሆን የተያዘውን ገንዘብ በሙሉ ይወስዳል፥፥ ዋናዎቹ ተጫዋቾች ጀርባና ዙሪያ ለሎችም ተማሪ ቆማሪዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከተጫዋቾቹ  ገንዘብ ያስይዛሉ፥፥ በድፍረት(ወይም በጭፍን) በማደርጋቸው እንስቃሴዎች በተደጋጋሚ እድለኛ የመሆኔ ነገር ለራሴ ገርሞኛል::  የዛሬው ቁማር ላይ አብሮኝ የነበረው መንጌ በኔ እድለኛነት ከመተማመኑ የተነሳ ራሱ መጫወት ትቶ እኔ በምጫወተው ሲያስዝ (ና ሲበላ) ነው ያመሸው:: 


በነገራችን ላይ ዛሬ  የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በኣል ስለሆነ ለስልጠና አልወጣንም:: በብላቴ የሚገኙ ኣየር ወለዶች እያመጹ መሆናቸውን የሆነ ሰው ሹክ ኣለኝ፥፥ ለምን እንደሆነ አልነገረኝም:: ምንም የተለየ ነገር ባለማየቴ መንገድ ላይ ኣየር ወለድ ባየሁ ቁጥር ኣተኩሬ  ስመለከት ነበር፥፥ እውነትም ኣብዛኖቹ ታጥቀዋል፡ቦምና ክላሽ፥፥ እኛን ተማሪዎችን ግን ምንም የሚሉን ነገር የለም....ተማሪው በሚያሳየው ቅጥ ያጣ ባህሪ የተሰላቹ ና እልህ ውስጥ የገቡ ስለመሰለኝ በውስጤ ስስ ሽብር ተሰማኝ:: ቢ*****ስ??





ሚያዚያ ዘጠኝ አስራዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት

ጭብጨባ.....


ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰኣት ኣካባቢ ኣንዲት ሄሊኮፕተር ብላቴ ግቢ ውስጥ ኣረፈች ኣንደኛ ብርጌድ ኣካባቢ፥፥ ካየር ወለዶቹ ኣመጽ ጋር በተያያዘ ነው መሰለኝ፥፥ ሰልጣኝ ተማሪ ከያለበት በመሄድ ሄሊኮፕተሩዋን ከበባት፥፥እንደመሰለኝ በርካታ ተማሪ ፕሬዝዳንት መንግስቱ መጥተው ይሆናል የሚል ግምት ነበረው፥፥ እኔ የቆምኩት ራቅ ብዬ ስለበር ከሄሊኮፕተሩዋ የሚወጣውን ባለስልጣን ማየት ኣልቻልኩም፥፥ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለሁ ኣንድ ኣየር ወለድ እ ወደቆምኩበት ቦታ ኣቅጣጫ መጣና ቆመ፥፥ እዚያም ለተሰበሰብነው እንዲህ አለን "እኛ የመጣውን ሰው ማን እንደሆነ ኣናውቀውም፥፥ ግን በጀኔራል ባልስልጣን ኣንመራም፥፥ሲቪል ባለስልጣን ነው የምንፈልገው፥፥ተማሪዎችም ድጋፋችሁን እንደምትሰጡን እንተማመናለን፥፥" ፥፥ከተሰበሰብነው ተማሪዎች ውስጥ "አዎ እንደግፋችሁዋለን የሚል ጭብጨባ የተቀላቀለበት የጋራ የሚመስል ድምጽ ወጣ" እንደግፋችሁዋለን የሚለው አባባል ሲገርመኝ ጭብጨባው ለምን እንደሆነ ፈጽሞ አልገባኝም። ለነገሩ ልገረም አይገባኝም።፡ጭብጨባ፡በየቦታው በዝቱዋል። ሳል ልስል ፈልጌ አፍኜ ያዝኩት። ደሞ እንዳይጨበጨብልኝ..

በወጋችን ላይ ዛሬም ቆመርኩ 56 ብር እንክት አድርጌና የ ጡንቸኞችን አይን ፍጥጫ (ብሎም ጡጫ) አምልጬ፡በውድቅት ወደ ዶርሜ እንደእገባሁ ይታወቅ.....