ወጥቶ-አደር
ሚያዚያ 21 1983 አ.ም.
ሰሞኑን የመጻፍ ስሜቴ ቀዝቅዞ ስለነበር ሳልጽፍ ብዙ ቆየሁ መሰለኝ። የኢትዮጵያ ሁኔታ በየሰኮንዱ መለዋወጡን ቀጥሏል። ጦርነቱ
እየከፋ መጥቷል። ብላቴ ውስጥ የሚንሽራሸሩት ወሬዎችም አይነታቸው የትየለሌ ሆኗል። ወሬዎቹ ዋነኛ ባህሪያቸው ጆሮ መንዘር ነው።
በንዝረቱ ሃይል ብሎም ስለወሬው የበለጠ ለማወቅ በሚደረግ አላስፈላጊ ጥረት የሽብር ጽዋ መጎንጨት የተለመደ ነገር እየሆነ ነው።
ከወሬዎቹ የተወሰኑት ምንጫቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዜናዎች ናቸው። አልፎ አልፎ አንዳንድ ተማሪዎች ራሳቸውን ለማጽናናት
ይሁን ለሌላ ጥሩነቱ ከገደብ ያለፈ ወሬ ያወራሉ። ከነዚህ ወሬዎች ውስጥ “በቅርቡ ይህን ማሰልጠኛ ጣቢያ እንለቃለን፡ ሌላ 35 ሺ
ጦር እኛን ተክቶ ለመሰልጠን እየተዘጋጀ ነው” የሚሉ ይገኙባቸዋል። እንደዚህ አይነት ወሬ ታዲያ ወደ ጦርነት ያለመዝመትን ምስራች ተርቦ ላለው የግቢው ሰልጣኝ ተማሪ (በሙሉ ማለት ይቻላል) ጥሩ ምግብ እንደማለት ነው። ስልጠናው ግን እንደቀጠለ ነው።
አየር ወለዶቹ የተማሪውን አልምጥ ጸባይ እየለመዱት ሄደዋል። የጠዋት ስፖርትም ሆነ ዋናውን የተግባር ስልጠና እንድንሰራ
ማስገደዳቸውን አቆሙ። ሞራል አውጡ (ወደ ስልጠናው ቦታ በጋራ እየዘፈናችሁ ሂዱ) የሚባለውም ነገር ቀረ። የሚገርመው ግን ተማሪው ደሞ በራሱ ግዜ ሞራል እያወጣ መሄድ
ብቻ ሳይሆን በስልጠናው ላይ በብዛት መገኘት ጀመረ። እኔ በበኩሌ የጠዋቱን ስፖርት ሙሉ በሙሉ የተውኩት ሲሆን ስልጠናውና ወደ መስክ
የሚደረገውን የእግር ጒዞ ግን ለምጄዋለሁ።
ሚያዚያ 22 1983 አ.ም.
በዛሬው እለት ስልጠና ላይ እያለን አንድ አስቀያሚ ነገር ተከሰተ። የእለቱ ስልጠና አይነት “በጓድ መከላከል” የሚል ነበር።
የአምስተኛ ብርጌድ ተማሪ ሁሉ ቡቄሳ ተራራ ፊት ለፊት ተኮልኩሏል። የጠዋት ጸሃይ ፍንትው ብላ ወጥታለች። የቃል ትምህርት ከተሰጠን
በኋላ በገለጻ ደግሞ መመልከት ስለነበረብን ገለጻውን የሚያሳዩት አየርወለዶች ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። የተለያዩ አይነት መሳሪያዎች
ይዘዋል፡ ኤ.ኬ.ኤም፡ ክላሺንኮቭ፡ላውንቸር፡መትረየስና፡ቦምብ ። ገለጻው ተጀመረ....
የጠላትን እንቅስቃሴ ዛፍ ላይ ሆኖ እየቃኘ ለጓድ መሪው ተናጋሪ ሆኖ የሚጫወተው አየርወለድ ሲናገር ከሩቅ ይታየኛል
ግን ምን እንደሚል አይሰማኝም። በገለጻው መሰረት ጓድ መሪው ዛፍ ላይ ያለው ወታደር የሚነግረውን ተንተርሶ የተለያየ መሳሪያ ለያዙት
የጓዱ አባላት የ “ተኩስ!” ተእዛዝ ይሰጣል። ገለጻ ቢሆንም ተኩሱና መሳሪያዎቹ ግን እውነተኛ እንደሆኑ ልብ በል/በይ። በእርግጥ
እልምታቸው ባዶ ተራራ ላይ ነው....ቡቄሳ ተራራ..
የ.ኤ.ኬ.ኤም ጥይቶች መንጣጣት ጀመሩ። የቡቄሳ ተራራን ደረት ደበደቡት። አካባቢው በድምጸቱ ተናጋ። “ተመስገን ልምምድ
ነው” አልኩ በሆዴ። ቀጥሎ ደግሞ ዛፍ ላይ ያለው አየር ወለድ ለኔም ሆነ ለሌላው ተማሪ በሚሰማ ጎላ ያለ ድምጽ “የጠላት ታንክ
በቅርብ ርቀት ይታየኛል!” አለ። በዚህ ግዜ ጓድ መሪው “ ላውንቸር ተኳሽ 5 ቁጥር፡ በራስህ ጊዜ አልመህ፡ አነጣጥረህ የጠላትን
ታንክ ደምስስ!” አለ። ከመቅስፈት በሚያንቀጠቅጥ ሃይለኛና ከፍተኛ የድምጽ ማእበል አካባቢው ተዋጠ። ብዙዎቻችን ወደመሬት
አጎነበስን።
ገለጻው ቀጠለ..ዛፍ ላይ ያለው አየር ወለድ “የጠላት እግረኛ ወታደር በ 50 ሜትር ርቀት ላይ!” በማለት ጮሆ ተናገረ፡፡
ጓድ መሪው ተቀብሎ “ቦምብ አዘጋጅተህ ወርውር...” ሲል አሁንም ከፍተኛ ድምጽ ና አቧራ የፈጠረ የ ቦምብ ፍንዳታ ተሰማ። ቦምቡ የደፈነዳበት ስፍራ ላይ አንድ ሄልሜት የቦምቡ ፍንዳታ ከፈጠረው አቧራ ጋ ወደሰማይ ሲወረወር ተመለከትኩኝና ሰውነቴን የሚቀፍ ነገር ወረረኝ። ሰቀጠጠኝ። ወዲያው “የተጎዳ
ሰው አለ መሰለኝ!” የሚል ድምጽ ከበስተጀርባዬ ሰማሁ፡፡ ስለ ገለጻው ሌክቸር ይሰጥ የነበረው አየር ወለድ ያለምንም
የተለየ ስሜት ንግግሩን ቀጠለ። የተማሪው ሁሉ ቀልብ ግን ቦምቡ የፈነዳበት ቦታ ላይ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን ቦምቡ ከፈነዳበት
አካባቢ እሪታ መሰል ድምጽ ተሰማ....የእርዳታ ጥሪ ነው...ቦምብ ወርዋሪው በእርግጥም አደጋ ደርሶበታል፡ የአደጋውን ምንነት ባላውቅም። ተማሪዎች
በሙሉ አጉረመረምን። አካባቢዬ ቆመው የነበሩ አየር ወለዶች አንገቶቻቸውን ደፉ። “ከዚህ በኋላ ገለጻ ይቅር! አንፈልግም በቃ!”
የሚሉ ድምጾች አልፎ አልፎ ከተማሪው መሃል ተሰሙ። ትንሽ ቆይቶ አንድ አየርወለድ ሻምበል፡ እጁን እያጨበጨበ ጮህ ብሎ “እንደማመጥ!”
አለ። ከዚያም ጉርምርምታው ጋብ ሲል “ምናልባት እናንተ አጋጥሟችሁ ላያውቅ ይችላል። እኛ ግን በየጊዜው የምናየው ነገር ነው (የቦምቡን
አደጋ ማለቱ ነው) ። ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ስህተቶች ይፈጠራሉ። ህይወትም ሊጠፋ ይችላል። የዛሬውም ሁኔታ እንደዚያው ነው።
ልጁ በወቅቱ የቦምቡን ዘንግ በእሳት ካቀጣጠለ በኋላ ዘንጓ ተቀጣጥላ እስክታልቅ ስለጠበቃት ከእጁ ገና እንደወረወራት ነው የፈነዳችው፡ በዚህም እጁ ሊቆረጥ ችሏል። ህይወቱ ግን ተርፏል። “እና ገለጻውን እንቀጥላለን።” አለ......
No comments:
Post a Comment