Wednesday, September 10, 2014

ብላቴ 8

ሚያዚያ አስራ አንድ  አስራ ዘጠኝ ሰማንያ ሦስት - አርብ 

ነጎድጉዋድ  

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከ ሀምሳ አራት ደቂቃ 
ክብርት ማስተወሻዬ ሆይ: ከዚህ በፊት ከራሴ አልፌ ስለ ሀገር ጉዳይ በቁም ነገር ፅፌ ባላውቅም የጊዜው የኢትዮጵያ ሁኔታ ስለ ሀገር እንድፅፍ እያስገደደኝ ነው:: በዚህ ወቅት በተለያየ መስመር የሚሰማው ወሬ ልክ ከገመድ ወደ ገመድ እንደሚተላለፍ  የኤሌትሪክ ኃይል ከሰው ወደ ሰው እየሄደ የሚነዝር እንዲሁም ፍርሃትና ውስጣዊ ሽብር የሚያጎናፅፍ ነው:: አልፎ አልፎ ከዚህ ከብላቴ ሳልወጣ እቀር ይሆን የሚል ሃሳብ በአይነ ህሊናዬ ውልብ ይላል:: ስልጠናችንን ያለምንም የፕሮግራም መዛባት እያካሄድን ቢሆንም በቀኑ መጨረሻ ላይ የሚሰማው ወሬ ክብደት ያለውና የነገሮችን ትክክል አለመሆን የሚያመላክት ነው:: ትክክል ያልሆነው ምን እንደሆነና የት እንደሆነ ግን አላውቅም::

በዛሬው እለት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ለሕዝብ ንግግር ስለሚያደርጉ በኢትዮጵያ ያሉ መስሪያ ቤቶች በሙሉ ዝግ ናቸው:: እኛም ሰልጣኞች እሳቸው ሲናገሩ እንድናያቸው ና እንድናዳምጣቸው ተብሎ ወደ መስክ ስልጠና በመሄድ ፈንታ አንድ ዛፍ ጥላ ስር ያለ ስቅል ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠን የንግግሩን መጀመር እየጠበቅን ነው:: ንግግሩ ባልተጠበቀና ባልተገመተ ግዜና ሰዓት የመጣ ስለነበረ ሁሉም ሰው ለንግግሩ ከመጉዋጉዋት ባሻገር ስለንግግሩ የራሱን ትንቢት ያስቀመጠ ይመስለኛል: በኔ ግምት ንግግሩ በስልጣንና በኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው የሚሆነው:: ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ይለቃሉ ብዬ አልገምትም::

ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ትንሽ ቆየት ብሎ...
ሦስት ሰዓት በፈጀ ንግግራቸው ተናገሩ ብዬ የምመሰክረው አንድ ቁም ነገር ቢኖር "ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጅ እስከሆነ ድረስ ስልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ" የሚለው  ነበር:: ነገሩ ግን ላስለቃቂ ካንበሳ መንጋጋ ማን ያወጣል ስጋ ለለቃቂ የነብር ጭራ እንደሚባለው በቃላት ተውቦና ደምቆ ቢነገርም በተግባር ፈፅሞ የማይደፈር ...ነው ከ ፕሬስዳንት መንግስቱ ስልጣን መውሰድ:: ብዙ ተማሪ ንግግሩን ሙሉ በሙሉ ና ካሁን ካሁን ጠቃሚ ነገር እሰማል ይሆን በሚል በጉጉት ያዳመጠ ሲሆን በንግግሩ መጨረሻ ግን ፈታ ያለ ፊት ማየት ተስኖኝ ነበር.....

No comments:

Post a Comment