Friday, August 14, 2015

እሁድ መስከረም 17 ቀን 1985 አ.ም.

ያባይ ልጆች መጡ እንደገና!
ግብፆቹ መምህራኞቻችን እረፍታቸውን ጨርሰው ጅማ እንደደረሱ ወሬ ሰማሁ:: “እሰይ!” ማለት ይገባኝ እንደነበር ባውቅም በነሲብ የተሰማኝ ስሜት ግን ወደ ግራ የወገነ የልብ መደናገጥ ነበር-ሀቅ ልናገር ከተባለ:: ወሬውን እንደ መልካም ወይስ እንደ መጥፎ ዜና መቁጠር እንዳለብኝ ማወቅ ሊሳኝ ዳዳኝ:: ማለቴ እኔም ሆንኩ ጉዋደኞቼ ከእረፍት መልስ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ እየቦዘንን ስለነበር ግብፆቹ መጥተው ትምህርት መጀመሩ ደስ የሚል ቢሆንም የፒሲዋንን የጥናት ኃላፊነትና የጉሮሮ ለጉሮሮ ትንቅንቅ ግን እንዲሁ ተቻኩዬና እጆቼን ዘርግቼ አቅፈው ዘንድ የሚፈቅድ ልብ አልነበረኝም:: እናም በዚህ የአደይ አበባ ፍካት ጡዘት ላይ በደረሰበት የወርሃ መስከረም አጋማሽ ከባልንጀሮቼ ጋር በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥም ሆነ ከግቢው ውጭ መቦዘኑና መፈንጨቱ እንዲያው ትንሽ ቢቀጥል ደስ ባለኝ.....በአንደኛው ሴሚስተር ከነበረኝ ልምድ በመነሳት የፒዋንን እንደገና መጀመር ሳስበው እንደዚህ ካለ ፀደይ: እንዲህ ካለ በአበቦች ከታጀበ የበጋ መጀመሪያ: እንዲህ ካለ ነፃ ቡረቃ ተነጥቄ የዚህ ተቃራኒ ወደ ሆነ የኑሮ ጥቁር የምወሰድ መሰለኝ::: በቃ የክረምቱ ግዜ አበቃ......በቃ የፀደዩ ወራት አበቃ......ወርቅ ቢጫማውን የጅማ ፀሐይ ጥልቀት እንደልቤ ለመመልከት ዕድል ይኖረኝ ይሆን? ሙሉ ቀይ ጨረቃን በዛፍ ቅርንጫፎች መካከል ለማየትስ? የጅማን ደረቅ ምሽ ንፋስ ሽዉታና በሱም ምክንያት የሚወዛውዙትን ዛፎች ድምፅስ እሰማ ይሆን? በቃ ከዚህ በሁዋላ እኮ ታሰርኩ! ጎበዝ! በግብፆች ቁጥጥር ስር ልገባ ነው:: በተለይም በማይመቸኝ በፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር ማሂ  ስር! ያባይ ልጅ ያለህ! 
የኔ ነገር ለካ እነሱም ካባይ ናቸው.....

የኔ ውድ የሆንሽ ማስታወሻዬ.... ይልቅ አሁን ይህን አይነት ወሬዬን ልተውና ትናንት እኔና ጉዋደኞቼ የመስቀል ዋዜማን እንዴት እንዳከበርን ለተርክልሽ......


እኔ ጉዋደኞቼና መስቀል

በነገራችን ላይ በዶርም ቁጥር 207 ውስጥ ያለነው ልጆች 10 ስንሆን ክፍሉ ግን ለ12 ልጆች ታስቦ የተሰራ ስለነበር 12 ሎከሮች አሉት:: ከሁለቱ ትርፍ ሎከሮች ውስጥ አንደኛው ዘወትር ክፍት የነበረ ሲሆን አንደኛው ግን ለብዙ ጊዜ የተቆለፈ ነበር:: እኔና ጉዋደኞቼ ታዲያ “እስቲ ውስጡ ምን ይኖር ይሆን?” በሚል ጉጉት ትናንትና ከፈትነው:: በርከት ያሉ ልብሶችና ጥቂት አንሶሎች ደብተሮችና ሌሎቹም ቁሳቁሶች የሎከሩን መከፈት ተከትለው ተንከባለሉ ! የሁላችንም አይንና ልብ ያረፈው አንሶላውና ልብሶቹ ላይ ነበር:: ጅማ ገበያ ላይ ያላቸውን ዋጋ ጠንቅቀን እናውቅ ነበርና:: በዚያ ላይ የመስቀል ዋዜማ ነው:: ወይ የእግዚአብሔር ነገር! የማን ይሆን ልብሱ? የሁሉም ጥያቄ ነበር:: እኛ እዚህ ዶርም ከመግባታችን በፊት ይኖሩበት የነበሩት ያለፈው ዓመት ኢንተርንሺፕ ሀኪሞች እንደነበሩ በሰከነ ውይይት ደረስንበት:: አሁን ተመርቀው በግቢ ውስጥ የሉም:: ወደ ሥራ ዓለም በየአቅጣጫው ተበታትነዋል:: አሀ! የዚህ ልብስ ጌታ ባሁኑ ሰዓት ሃኪም ሲሆን በወር 835 ብር እየበላ ይሆናላ ይሄኔ! በዚህ ነፃ እሳቤ በመታገዝ በቀጣዮቹ ሰዓታት ውስጥ አንሶላውና ልብሶቹ ወደ ገንዘብ ተቀየሩ:: ደንገዝገዝ ሲል የጅማን ከተማ መሃል ለመሃል ሰንጥቀን ጠለቅንባት.....እኔና ጉዋደኞቼ:: በታክሲ  ጩኸት: በሙዚቃ ቤት ሜጋ ስፒከር ድምፅ እንዲሁም ባመትባል ዋዜማ የከተሜ ግርግር ታጅበን ከፈረንጅ አራዳ መልስ : በየጆካ ሆቴል ጀምረን: ካንዱ ቡና ቤት ወዳንዱ እየተሸጋግርን እጅግ በጣም የምንወደውን ቀይ ቪኖ ስንጠጣ ስንደንስና ስንወራጭ አስከ እኩለ ሌሊት በስቲያ አመሸን.... ያ ያምና ኢንተርን የዛሬ ዶክተር እግዜር ይስጠው:: እንጀራ ይውጣለት:: 

የምሽቱ አየር ደረቅና እጅግ በሚመች መልኩ ቀዝቀዝ ያለ ስለነበር ካንዱ ቡና ቤት ሞቅ ብሎን ወጥተን ወደሚቀጥለው እስክንደርስ ሞቅታው በረድ ይልልን ነበር....

No comments:

Post a Comment