ዛሬ
አኔ የምፅፈውን የምታነብ ሁሉ:: ባለፈው ሚያዚያ
አንድ ከልቤ ማህደር የተሰኘ ግጥም ካሰፈርኩ በሁዋላ በመጥፋቴ የቅርታ ልጠይቅ ይገባልና እነሆ:: ነገር ግን የጠፋሁት
በከፊል በምክንያት መሆኑን ታውቅልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ:: ከሃያ ዓመት በፊት በህይወቴ ውስጥ የተከናወንን ነገር
ለመፃፍ ስፍጨረጨር አሁን በዚህ ዘመን የሚከናወነው ነገር አንዳንዴ ወጥሮ ይይዘኛል::
ባለፉት አራት ወራት የእንጀራዬ ምንጭ የሆነውን የቀድሞ ስራዬን በመተው አዲስ ሥራ በአዲስ ቦታ በመጀመሬ ይህን ለኔም ሆነ
ለቤተስቤ በመልካም ሁኔታ ለማስኬድ ቀልቤ ሁሉ እሱ ላይ አተኩሮ ከረመ:: የቀድሞ መኖሪያችንን ለቀን አሁን አዲስ ሰፈርና ቤት
ውስጥ ነው ያለነው:: ቤተሰብ አፍርቶ ካንድ ቤት ወደ አንድ ቤት መዘዋወር እንዴት እንደሆነ የደረሰበት ያውቀዋልና ከዚህ በላይ
ማለት አልፈልግም::
አሁን እንግዲህ አዲሱ ሥራና ኑሮ ተለምዶ በተወሰነ
መልኩ መረጋጋት ላይ በመድረሴ ጣቶቼን ወደ ላፕ-ቶፕ ኪቦርድ ቀሰርኩ.....
ባለፈው ማስተዋሻዬን ያቆሙኩት የሁለተኛ ዓመት አንደኛ ሴሚስተር የህክምና ትምህርት አልቆ በነሐሴ ወር መጀመርያ ለእረፍት ወደ
ቤተሰብ ጋ እንደነጎድኩ በመግለፅ ነበር:: እነሆ ዕረፍቱ አልቆ: የዘመን መለወጫም ተከብሮ: በበነጋው ወደ ጅጤሳ ከመመለሴ የለጠቀውን
ማስፈር እጀምራለሁ:: መልካም ንባብ;::
ዕለተ ሐሙስ መስከረም 7 1985 አ.ም.
የሰሞኑ የጅማ አየር ሞቃትና ደረቅ ነው:: የቀኑ
ሙቀት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ያደክማል:: ምሽቶቹ በድፍን ጨለማ የተዋጡ ናቸው:: ከቤተሰቤ ጋር የዘመን መለወጫን ባከበርኩ በሁለተኛው ቀን መስከረም 3 ቀን ጅማ ከተማ ገባሁ:: የህክምና ትምህርቴን ለመቀጠል:: ዛሬ እንግዴህ አራተኛ ቀኔ ነው::
በነዚህ ቀናት ውስጥ የአንደኛ ሴሚስተር ፈተና ዉጤቶቻችን በደፓርትመንቱ ሃላፊ አማካይነት ተነግረውናል:: በኔ በኩል ውጤቶቹ
ምንም እንኩዋን በጣም ከፍተኛ ባይሆኑም በልቤ ሳስብ ከነበረው እጅግ በጣም የበለጡ ሆነው ስላገኘሁዋቸው ደስ ብሎኛል:: ተስፋዬ
በጣም ጨምሯል:: ለካስ በጣምም በትምህርቴ ደካማ አይደለሁም? የሚል ውስጣዊ ስሜት እየተሰማኝ ነው::
ቅዳሜ መስከረም 9 1985 አ.ም. ከምሽቱ 6
ሰዓት ከ 15 ደቂቃ
የዛሬው ቀን ፀሐያማ ሆኖ የዋለ ቢሆንም ወደ
አመሻሹ ላይ ዝናብ ጥሎ ነበር:: ዋይት ሃውስ በሚገኘው ዶርም 207 መኝታዬ ላይ ነኝ:: ወደ ስምንት የሚሆኑ የዶርሙ አባላት
ድብን ባለ እንቅልፍ ውስጥ ሲሆኑ አዳሙ ብቻ መፅሐፍ ቅዱስ እያነበበ አልጋው ላይ ቁጭ ብሉዋል:: እኔም ይህን ፅፌ ስጨርስ የአዳሙን አርአያ በመከተል መፅሐፍ ቅዱስ
አንብቤ ለመተኛት አስባለሁ:: ሰሞኑን ኃይለኛ ጉንፋን ካንዱ ወዳንዱ እየተላለፈ ጉዋደኞቼን ሁሉ ሲያስተኛቸው ያልታመምኩት እኔ
ብቻ ነኝ ማለት እችላለሁ:: ለታመሙት ጉዋደኞቼ ከጤና ሳይንሱ የተማሪዎች ምግብ ቤት የበሽተኛ ምግብ በማመላለስ ላይ እገኛለሁ::
በነገራችን
ላይ ባለፈው ነሐሴ መጀመሪያ እንደኛ እንደተማሪዎቹ ሁሉ ግብፃውያኑ መምህራኖቻችንም ለእረፍት ወደ ሀገራቸው ሄደው ነበር::
እስከዛሬ አልተመለሱም:: በዚህም የተነሳ ትምህርት ገና አልተጀመረም:: በግሌ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ ና ከግቢ ውጭ በእግር ከመዞር በስተቀር ምንም አይነት ትምህርታዊ እንቅስቃሴ አላደረኩም::
ማክሰኞ መስከረም 12 1985 አ.ም. ከምሽቱ 5
ሰዓት
የዛሬውም ምሽት ጨረቃ የለውም:: ከአዲስ አበባ
ከመጣሁ ላይኔ የናፈቀው ነገር ቢኖር የጅማ ምሽት ጨረቃ ድምቀት ነው:: ምንም እንኩዋን ለጉዋደኞቼ ውሸት ቢመስላቸውም..ምንም
እንኩዋን የሶስተኛው ዓለም ምስኪን ብሆንም..ይህ ስሜቴ ግን አተጨባጭ ነው::
ግብፆች ገና አልመጡም:: ከአንድ ሰው በስተቀር::
ይህ የሂስቶሎጅ ፕሮፌሰር ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቅ አዲስ ሰው ነው:: ዛሬ ቀን ሲያስተምረን የመጀመሪያመሪያ ስሙ መሐመድ መሆኑን ነግሮናል::
በነገራችን ላይ ጅማ ከመጣሁ ብዙም አልተከፋሁም:: እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ በቀን ውስጥ በንቃት ከሚኖረኝ ሰዓት ውስጥ አብዛኛንውን የማሳልፈው ሳልከፋ ነው::
ሳሚ፤ የጂጤሳን ሕይወት የምትከትበው ብዕርህ አትንጠፍብንሳ፡፡ ትዝታ 101 የትም አይገኝም
ReplyDelete