ጥር ሁለት ቀን 1985 አ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት
ዉቦቹና በጨረቃ ይደምቁ የነበሩት ምርጦቹ የበጋ ወራት ሕዳርና ታህሳስ በ ፒሲዋን ማጠቃለያ ፈተና መምጣት ስጋት ተጀቡነው ተራ በተራ በማለፍ ስፍራቸውን ለጥር ለቀቁ:: ጥር ወር ደግሞ የያንዳችዳችን በጅጤሳ መዝለቅና አለመዝለቅ የሚወሰንበት ወር ለመሆን ታደለ:: ብርቱ የሂወት ፈተና ወቅት:: የድብልቅልቅ ስሜት ወቅት:: ባንድ በኩል አድካሚዎቹ የሌክቸር ክፍለ ጊዜያት የሚያበቁ በመሆናቸው አንፃራዊ እፎይታ ተሰምቶኛል:: በሌላ በኩል ደግሞ ለፈተናው ያደረኩትና ገና የማደርገው ዝግጅት መቼም ቢሆን እንደማይበቃ ከማወቅ የመነጨ የውስጤ መብሰክሰክ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ነው:: እነዚህን የጠቀስኩዋቸውን ስሜቶች ሌሎች ሰላሳ ምናምን የሚሆኑ ፒስዋነኞች እንደሚጋሩኝ
እርግጠኛ ነኝ::
የመጨረሻው የፒሲዋን ሌክቸር ቀን በሚቀጥለው ሮብ እንደሚሆን ተነግሮናል:: ከዚያም ሁለት ሳምንት ከጥናትና በጄም ካለ ከክለሳ መሳ ለመሳ የምንገጥምበት ግዜ ይሆናል:: ያም ሲያበቃ የዓመቱ ማጠቃለያ የፅሁፍ ፈተና በአናቶሚ ትምህርት ይጀመራል:: እንግዲህ ባወጣ ያውጣው......... እኔ ግን ምንም አልተዘጋጀሁምም ከዚህ በሁዋላም የምዘጋጅ አይመስለኝም.....
በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን ፊዚዮሎጂ ሌክቸር ላይ ስለ Color Blindness ተማርን:: የፊዚዮሎጂ መምህሩ ለናሙና ይዞ የመጣው የ Color Blindness መለያ ወረቀት ላይ የተሳሉ በነጠብጣብ የተሞሉ ክበቦች ለምሳሌነት አንዳንድ ተማሪዎችን እየጠራ ስንት ቁጥር ወይም ምን ይታያቹሃል እያለ ሲጠይቅ ከተጠያቂዎቹ አንዱ እኔ ነበርኩ:: ታዲያ እኔ ላይ ሲደርስ ሌላው ሁሉ ስምንት ይሁን አራት ቁጥር ያለውን እኔ ሶስት ቁጥር ነው ብዬ ድርቅ በማለቴ ለመጀመሪያ ግዜ Color Blind እንደሆንኩ ታወቀ:: ቀይና አረንጉዋዴ ቀለሞች አልፎ አልፎ እንደሚምታቱብኝ ቀደም ብዬ የተረዳሁ ቢሆንም አሁን በደንብ ተነቃብኝ....ወይኔ
ጥር 18 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ 21 ደቂቃ
በእውነቱ የባለፈውን ማስታወሻ ካሰፈርኩበት ከጥር ሁለት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባሳለፍኩዋቸው ቀናት የተከናወኑ ድርጊቶች ቢኖሩም ቀናቱ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ፒሲዋነኞች እጅግ አስጨናቂ እንዲሁም የአእምሮን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ቀናት ስለነበሩ እዚህ ማስታወሻ ላይ አሰፍራቸው ዘንድ ከባድ ሆነብኝ:: እጄም ይፅፍ ዘንድ ሳሳ:: ነገር ግን ይህን እላለሁ: በዚህ ሰዓት የዓመቱ ማጠናቀቂያ የፅሁፍ ፈተና መጀመሪያ ዋዜማ ላይ ከመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ ጋር የሞቀ ወሬ ይዘናል:: ጥናት የሚባል ነገር አቁመናል:: ዘራፍም ብለናል:: አልተጨነቅንም ማለት ግን አልነበረም:: ጥቂቶቹ የተናገሩትን እነሆ...
ሚሊዮን "ቀፎኛል"
አምሳሉ "እንግዲህ ጭንቅላቴን የከበደውን አናቶሚ ነገ ልገላገለው ነው: በጣም ራሴን አሞኛል"
መንጌ "ፒሲዋን መርዝ ነው ግን ሰው አይገድልም"
No comments:
Post a Comment