ጥር መጨረሻ - 1985 አ.ም.
የፒሲዋን ማጠቃለያ ፈተና ትዝታ
በዚህ ህዝበ ፒሲዋን ባይምሮ ጭንቀት በተወጠረበት ሰሞን የባዮኬሚስትሪ ጥናቴን እንድጀምር እነመንጌ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰኣት ቀሰቀሱኝ:: ተነሳሁና ከነወሰንየለው ዶርም ውሃ ኣምጥቼ ሁለተኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ከዶርማችን ፊትለፊት ፊቴን ስለቃለቅ በዚህ ውብ በሆነ ነፋሻማ ለሊት ወደባላምባራስ ሜጫ ቡና ቤት አቅጣጫ ጨረቃን በድፍን ገጽታዋ በከዋክብት መሃል ሆና ተመለከትኩ:: ደስታ ተሰማኝ:: ጨረቃን እያየሁና የባጥ የቆጡን እያሰብኩ በረንዳው ላይ ከቆየሁ በሁዋላ ከሌሊቱ ኣስራ ኣንድ ሰኣት ሲል ወደ ዶርም ገባሁ:: በዚህ ሰኣትም በእርግጥ ዶርሙ ውስጥ በንቃት የቆምኩት እኔ ብቻ እንደሆንኩ ኣስተዋልኩ:: የዶርም ታጋሪዎቼ ሁሉ ተኝተው እስትንፋሳቸው ብቻ ይሰማኛል:: የጭንቀትና የስቃይ እስትንፋሶች ከዶርሙ ኣራቱም ማዕዘኖች አየተነሱ በጆሮዬ ጠለቁ:: ምስኪን እስትንፋሶች:: ሌሊቱ ሊያበቃ የቀረው ኣንድ ሰኣት ብቻ ነው:: ይሄ ሁሉ የተኛ መንጋ አንደነበረ ይቆይ መስሎታል:: የተለመደ የፈተና ሰሞን ግርግሩን ከአፍታ በሁዋላይጀምራል:: ከእንቅልፍ የመቀስቀሴ
ምክንያት የሆነውን የባዮኬሚስትሪ ጥናት ገና ኣልጀመርኩም………..
ከላይ የፈተና ሰሞን ግርግር ብዬ ያልኩት መቸም ዘርፈ ብዙ ነው:: በተለይ ይህ የማጠቃለያ ፈተና ለመጀመሪያ
ግዜ ከውጭ በመጡ ሳይንስ ኣዋቂዎች በቃል ፈተና የምንገመገምበትም ጭምር ስለሆነ የዚህ ክስተት ፍራቻ ትልቁን ስፍራ ይይዛል:: ይህ የቃል ፈተና የጽሁፍ ፈተናዎቹ ከተጠናቀቁ በሁዋላ የሚደረግ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የሚኖረን ጭንቀት ሁለት ኣይነት እንዲሆን አድርጎታል:: የመጀመሪያው ለያንዳንዱ የጽሁፍ ፈተና የምነጨነቀው ሲሆን ሁለተኛው ለዚህ በሂወታችን የመጀመሪያ ለሆነ የቃል ፈተና የምንጨነቀው ነው:: ሁለቱም ጭንቀቶች ግዙፍና ከኣቅም በላይ በመሆናቸው ለመሸከም ኣቅም ይጠይቃሉ:: ስለዚህ ይህ ሰሞን አኔም ሆንኩ እኔን መሰል ፒሲዋነኞች አንዴት አንደምንጨነቅ ራሱ ግራ የገባን ሰሞን ነው:: በዚህ የሩጫና የግርግር ሰሞን ኣለመጨነቅ “ኣበድኩ አንዴ?” የሚል ጥያቄ በመፍጠር ከጭንቀት የተለየ ግን ክብደቱ ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ውስጥ ይከታል:: ለዚህ ስሜት ስም አጣሁለት:: በቃ መግለጽ የሚያዳግት የኣአምሮ መዋለል ልበለው? የዚህ ኣይነት ስሜት መገለጫ ኣንዱ ኣላስፈላጊና ያለቦታው የሚገለፅ ፈገግታ ነው:: ብዙ ፒሲዋነኞች ፈገግ ሲሉና ከዚህ በፊት ብለዋቸው ያማያውቁትን ደንታ ቢስ ቃላቶች ሲወረውሩ እሰማለሁ:: ጭምት የነበሩ ኣንዳንዶች: ተጫዋችና ቀልደኛ ሆነዋል:: ኮስታራና ለወትሮው ጥናት የኑሮኣቸው ኣመዛኙ ክፍል የነበሩ ኣንዳንዶች ደሞ ቴሌቪዥን ከፍል መበርከት ጀምረዋል:: በፈተናዎች መካከል ማለት ነው….
የጽሁፍ ፈተናዎች ቀጥለዋል…. ኣንዱ ፈተና ሲጠቃለል ያለምንም ትንፋሽ የሌላው ፈተና ዋዜማ ይሆናል:: ስለዚህም ኣንዱ ፒሲዋነኛ ከሌላውጋ ሲገናኝና ወግ ሲያወጋ ፈተናው ኣጀንዳ መሆኑ ቀርቶ ሌሎች በዚህ ግዜ ያማያሳስቡ ጉዳዮች ሆነዋል የሚወሩት::
አኔ በበኩሌ ሁልግዜም ቢሆን የሚያስቸግረኝ ለማጥናት ስቀመጥ ብቻ የሚከሰት የቀልብ መበታተን ና የአእምሮ መብሰክሰክ ኣሁን በዚህ የፈተና ሰሞን ከመቼውም ግዜ ልቆ እየተገዳደረኝ ነው:: ኣአምሮየዬ እንቶ ፈንቶ ሃሳቦችን ያለምንም ገደብ በቀላሉ ተቀብሎ ያስተናግዳል:: ማሰብና መቀበል ያቃተው ለፈተናው መነበብ ካለበት ወረቀት ላይ ያለውን ሀሳብ ነው….
በዚህ ሁሉ መካከል ኣንዳንዴ “ያለተስፋ አንዴት መኖር ይቻላል?” የሚለው መፅሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ጥያቄ ይመጣብኛል
ታዲያ ይህን ሁሉ በሆነበት ሰሞን ኣንድ ጠዋት የኣናቶሚ የቃል ፈተና ተራዬ ደርሶ ተፈተንኩ:: አንዳጋጣሚ ሆኖ ኣናቶሚ የሚፈትን ኣዋቂ ከሌላ ቦታ ስላልተገኘ ፈታኞቹ ፕሮፌሰር ሳላህና ሚስቱ ኤቢትሳም ነበሩ:: እምብርዮሎጂም ኣንድ ላይ ተፈተንኩ:: በውነት በጣም ደስ ያለኝ ቀን ነበር:: የተጠየኩትን ጥያቄ ሁሉንም ማለት በሚቻል መልኩ መለስኩ:: ፈተናው ኣልቆ በቃ-ሂድ ሲሉኝ ማመን ኣልቻልኩም:: በቃ ይሄው ነው? ኣልኩ በልቤ:: ከዚህ በሁዋላ ሂወቴን ሙሉ ኣናቶሚ አንደማልፈተን ወይም አንደማልማር ኣሰብኩና ኣዘንኩ:: በጣም አጅግ በጣም የምወደው ትምህርት ነበር:: አኔና የኣናቶሚ ደብተሮቼ አንዲሁም ውድ የሆኑት ኣናቶሚና አምብርዮሎጂ ስዕሎቼ ብቻችንን ቀረን:: ለሁሉም ግዜውን ይጠብቅለታል አንደተባለው የኣናቶሚ ስዕሎቼን በሜዲሲን ተማሪነቴ ሳይሆን በተፈጥሮና ስነጥበብ ኣድናቂነቴ የምመለከትበትና ግዜ ሩቅ አንደማይሆን ተስፋ ኣለኝ….
የቃል ፈተናዬን ያጠናቀኩት በፊዚዮሎጂ ነበር: የካቲት 3 ቀን 1985 ኣ.ም.:: ለገሰ የሚባል ከጥቁር ኣንበሳ ሆስፒታል የመጣ ፊዚዮሎጂስት ነበር የጠየቅኝ:: ፊቱ ዙሪያውን እውነትም ኣዋቂ በሚያሰኝ የተንዠረገገ ጺም የተሸፈነ ከኣፉ በላይ ካይኖቹ በታች ና ካፍንጫው ዳር ዳር ምንም ኣይነት መስመር የሌለው ኮስመን ያለ ሰው:: በመጀመሪያ በትርፍ ግዜዬ ምን ማድረግ አንደምወድ ጠየቀኝ:: “ስዕል መሳል” ብዬ መለስኩ:: ኣንጎል አንድስልለት ጠየቀኝ:: ግዜም ሳይፈጅብኝ ሳልኩለት:: ከዚያ ቪዡዋል ኮርቴክስ (Visual Cortex) የቱ ጋ ነው? ብሎ የፈተናውን ጥያቄ ጀመረ:: አሳየሁት:: ……
ፈተናውን ጨርሼ ስወጣ የተሰማኝ አንድና አንድ ነገር ቢኖር ወደ ሶስተኛ ኣመት ማለፌ አርግጥ እንደነበረ ነው…
በዚሁ ሰሞን ነበር የህቺን አጭር ግጥም አጀንዳዬ ላይ ያሰፈርኩት
የተጻፈው ሁሉ ላይነበብ ላይጠና
ሲከማመር በላይ በላይ ለፈተና
የዚህን ኣለም ድብቅ ሚስጥር
ያልተሰማ ጥልቅ ነገር
ኣውቀናል አስክንል ድረስ
ከምድር ኣልፈን ሰማያቱን እስክንዳስስ
አውቀት በውቀት ላይ ሲከማመር
ኣለቀ ሲባል ኣዲስ ደሞ ሲፈጠር
ጣቶች በመጻፍ ሲደክሙ
ብእሮች በጭነት ብዛት ሲጣመሙ
ቀኑ ሲመሽ ሌሊቱ ደግሞ ሲነጋ
ኣንድም ቀን አንኩዋን ሳንል ረጋ
ድንጉጥና ችኩል ሆነን
የማያልቅ ሆኖ አየታየን
ይኸው ደረሰ ኣበቃ ፒሲዋን
No comments:
Post a Comment