ሐምሌ 1 ቀን 1985 አ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ 40 ደቂቃ
ባለፈው ሰኔ መጨረሻ ላይ በዋለው ቅዳሜ: በ 1983 አ.ም አብረውን
ትምህርታቸውን ጀምረው የነበሩ የዲፕሎማ መረሃ ግብር ተማሪዎች ሁሉ ተመረቁ:: አንዳንዶቹ የቅርብ ጉዋደኞቻችን ነበሩ::
ስለዚህም ከነሱጋ በመለያየታችን ሆድ ባሰን:: ሰሞኑንም ጉዋዛቸውን ሽክፈው ግቢውን እየለቀቁ ነው......
በዚህ ቀዝቃዛ የክረምት ምሽት ላይ የተለመደውና በተደጋጋሚ ከመከሰቱ የተነሳ
እንደወንድም ወይም እህት የተላመድኩት የኤሌትሪክ ኃይል መቁዋረጥ ተከስቶ ስለነበር ማጥናትና ማንበብ አይቻልም ነበር:: እሰይ!!!
ስለዚህም በዚህ ትምህርታቸውን በትጋት ለሚከታተሉ መጥፎ ለኔ ግን ሸጋ በሆነ አጋጣሚ ከእመቤትና ፅጌረዳ ጋር ረዘም ያለ የእግር
ጉዞ እያደረግን ተናፈስን:: አየሩ መቸም ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም ርጋታ የተላበሰ እንዲሁም ባፍንጫና ባፍ ሲምጉት የሆነ ደስ የሚል
ነገር ይዞ ወደውስጥ የሚገባ ስነበር ተመችቶኛል:: ከሴቶቹ እንደተለያየሁ አራቱን ጉዋደኞቼንና የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼን አብይ: መንግስቱ:
ሚሊዮንና አምሳሉን አገኘሁዋቸው:: ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እንደምናደርገው ዛሬም ወደ ግሪን ሆቴል ሄደን እየጣንና እየተጨዋወትን
አመሸን: ኡፍፍፍ...በቃ በጣም ነው ደስ ያለኝ:: እኔ ትምህርት ሳይሆን የሄን ነው የምፈልገው:: ከጉዋደኛጋ መሳቅ:
መጫወት: መቦለት: ማውራት:መቃለድ: መቀለድ: እንደገና መሳቅ........ ወደ ጤና ሳይንሱ ስንመለስ የኤሌትሪክ ኃይል ወደቀድሞ ሁኔታው
ተመልሶ ስለነበር አንዳንድ የጥናትና ፅሁፍ ግልበጣ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለ-ተማሪዎችን ማየት ይቻል ነበር::
ሐምሌ 3 ቀን 1985 አ.ም
ዛሬ ጠንከር ያለ የሐምሌ ዝናብ አረንጉዋዴይቱን ጅማን ደበደባት:: ሐምሌ ሐምሌነቱን ለጅማ አሳወቃት:: መጣሁ: ያዥ እንግዲህ! አላት:: ጅማም ይህን ተቀብላ ክረምት ክረምት መሽተት ጀመረች:: ይበልጥ
አረንጉዋዴ ሆነች::በየቦታው እሸት በቆሎ መታየት ጀመረ:: ሻይ የሚጠጣ በረከተ:: ወፍራም ልብሶች ተማሪዎች ላይ ፊጥ ብለው
ይታዮ ጀመር:: የቤተ መፅሀፍቱ ሙቀት መቀነሻ ቬንትሌተሮች ስራቸውን አቆሙ:: ስለዚህም ቤተመፅሃፍቱ ውስጥ የርምጃና የመፅሀፍ
ገለጣ ድምፆች በቬንትሌተሮቹ ዝዝ...ዝታ መሸፈናቸው ቀርቶ ይሰሙ ጀመር:: ጠዋትም ማታም አየሩ መቀዝቀዝ ጀመረ..........
እንደ አምናው የፊዚዮሎጂ ትምህርት በአንድ መስጠሊ ግብፃዊ መምህር የተነሳ
ሊደብረኝ የሚሞክረውን የማይክሮባዮሎጂ ትምህርት እንዴት አድርጌ ቀልቤን እንደምሰጠው ግራ ገብቶኛል:: ሰውየው በጭራሽ
አልጣመኝም:: ነካ ነካ ነው የማስተማር ዘዴው:: ከትምህርቱ በተጉዋዳኝ ከፍል ውስጥ በላይበላዩ ሲጃራ ያጨሳል::: እያንዳንዱን
ሲጃራ አጭሶ ሲጨርስ እሳቱን የጫማው ሶል ላይ ያጠፋና ቁሩውን በመስኮት ወደውጭ ከወረወረ በሁዋላ ከያዘው ባኮ ውስጥ ሌላ
አውጥቶ በላይተር ይለኩሳል:: ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀው ነገር ነው::
ባጠቃላይ ከሁለተኛ ዓመት ይልቅ የሻላል ብዬ የተማመንኩበት የሶስተኛ ዓመት
ትምህርት ይባስ ብሎ ደረቅና የማይስብ እየሆነብኝ ነው::
ሐምሌ 5 ቀን 1985 አ.ም
እኔና ጉዋደኛዬ ቤተማርያም ዛሬ ምሽት ላይ ተአምር በመሰለ ሁኔታ ከሌባ ጡጫና ዝርፊያ
አመለጥን:: ነገሩ ባጭሩ እንዲህ ነው:: እኔና ቤተማርያም የዛሬውን የሌክቸር ሆልና የላይብረሪ ጥናታችንን አጠናቀንና አንድ
ላይ ሆነን ወደ ዶርማችን ስንመለስ ወደ ዋይት ሃውስ ህንፃ የሚያመራው ቀጭን መንገድ ላይ በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ 45 ላይ
ሁለት ሰውነታቸው ገዘፍ ያሉ ሰዎች ከፊትለፊታችን ወደኛ አቅጣጫ እየተራመዱ አለፉን:: ጨዋታ ይዘን ስለበር አላስተዋልናቸውም::
ሰላሳ ሰኮንድም ያህል ሳይቆይ ከበስተጀርባችን ከፍተኛ ጩኸት ሰማንና ፊታችንን ወደሁዋላ በማዞር ባለንበት ቀጥ ብለን ቆምን::
ወዲያውኑ ከየአቅጣጫው የጤና ሳይንሱ ዘበኞችና ሌሎች ተማሪዎች ወደ ተጮኸበት አቅጣጫ ሲሮጡ አየናቸው:: በትክክል እኛን አልፈው
የሄዱት ግዙፍ ሰዎች ሌቦች ነበሩ ማለት ነው! እኔ በበኩሌ ካለሁበት ቆሜ ሌቦቹ ወደ በጨለማ ወደተሸፈነው ጫካው ውስጥ እየሮጡ
ሲጠፉ ይታየኝ ነበር:: ማንም የተከተላቸው የለም: ያ አደጋ አለውና:: እኔና ቤተማርያም ከሁዋላችን የነበሩትና በሌቦች ጥቃት
የተሰነዘረባቸው ተማሪዎች ባይኖሩ ኖሮ የነሱ እጣ ፈንታ የኛ ይሆን እንደነበር በማሰብ ተሸማቀቅን...ኡ
No comments:
Post a Comment