ሰኞ የካቲት 15 ቀን ፩፱፰፭ አ.ም..ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ 45 ደቂቃ
CBTP
የሁለተኛ ዓመት ሕክምና
ትምህርቴን በብቃት በማጠናቀቅ ፈተናዎቹን በሙሉ በማለፍ ለሶስተኛ ዓመት እንደታጨሁ ይፋ ሆነ:: የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼም ሆኑ ሌሎች እኔን መሰሎች ሁሉ አለፉ:: መግለፅ በሚያዳግት ሁኔታ ሁላችንም
ደስ አለን:: ውጤታችን ይፋ ከሆነ በሁዋላ ታስረው እንደተለቀቁ እርግቦች ሆንን.... በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ ባሉት
ረዣዥም ዛፎች ላይ ወዲያና ወዲህ ከሚስፈነጠሩት ጉሬዛዎች ቀጥሎ እንደልባችን የምንታይ እኛ ሆንን:: በተከተሉት
ቀናት በኛ ዶርም ዉስጥ ከሰዓት ከሰዓት መሰባሰብን ልማዳችን አረግነው:: በብዛት ሙዚቃ ይኖራል::
የመሀሙድ አህመድ የቆዩ እንዲሁም የአስቴር አወቀ ለስላሳ ዘፈኖች
ዋናዎቹ ናቸው:: እነዚህን እየሰማን የባጥ የቆጡን እናወራለን:: በፈተና ወቅት ሳንሰማቸው ያመለጡንን የአለምም ሆነ ያገር ወሬዎች
ሰምተን የመረጃ ቁዋቶቻችንን እናድሳለን::
በነገራችን ላይ: በጅማ ጤና
ሳይንስ የህክምና ትምህርት መረሃ ግብር መሰረት የአመቱ ፈተና ካለቀና ውጤት ከተሰማ በሁዋላ ወደቤት መሄድ የለም! Community
Based Training Program (CBTP) ላይ ለአንድ ወር መሳተፍ አለብን:: ይህ ሕብረተሰብ ተኮር የጤና ስልጠና የትምህርታችን
አካል ነው:: በቡድን ተከፋፍለን ጤና ሳይንሱ በሚመድበን ቀበሌ በመሄድ በየቀኑ የተለያዩ ተግባራት እናከናውናለን:: በዚህ ዓመት
የምንሰራው ሥራ በዋነኘት ከነዋሪው መረጃ መሰብሰብ ይሆናል:: ስለዚህም አስቀድሞ የተዘጋጁ ጥያቄዎችን ይዘን ከቤት ቤት እንዞራለን::
እኔ ያለሁበት ቡድን የተመደበው የጅማ
ከተማ አካል የሆነ ነገር ግን ዳርቻ ላይ ያለና ከፊል ገጠራማ ቀበሌ
ውስጥ ነው:: ከቡድናችን ውስጥ በተለይ እኔና ኃይሉ የምንሰራበት ቦታ ደምበኛ ገጠር ነው:: እንዴት ይህ ቦታ በጅማ ከተማ ስር
እንደሆነ ግራ ገብቶኛል:: በዚህ አካባቢ እኔና ኃይሉ መረጃ ለመሰብሰብ በምንዘዋወርበት ወቅት ያስተዋልኩት አንድና አንድ ነገር
ቢኖር ባካባቢው የሚኖሩትን ሰዎች ስር የሰደደ ድህነት ነው:: ከዚህ በፊት ለእረፍት ወደ ራሴ የትውልድ ሰፈር ስመለስ ያስተዋልኩትን
የነዋሪ ድህነት አስታውስኩ:: ይህ ግን እጅግ በጣም የባሰ ነው:: ገጠር በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ቸርነት የዘሩትን ፍሬ ከመጠበቅ
በስተቀር ሌላ ምንም ሃብትና ንብረት የሌላቸው ምስኪን ቤተሰቦች አየሁ:: አንዳንድ ቤተሰቦች ስምንትና ዘጠኝ የሚሆኑ ልጆች ያሉበት
ሲሆን የዓመት ገቢያቸውን በምንጠይቃቸው ጊዜ የሚሰጡን መልስ "ከሶስት እስከ አራት ኩንታል በቆሎ" የሚል ነው::
ማመን ያስቸግራል..... እዚህ ገጠራማ የቀበሌ ከፍል የኤሌክትሪክ መስመር ሰንጥቆት ቢያልፍም በየቤቱ ግን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም
መብራት የለም:: ስልክም የለም:: የዉሃ መስመር የሚባል ነገር የለም:: ይህ አጋጣሚ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሀገራችን ድህነት የበለጠ
መረዳት ያገኘሁበት ይመስለኛል.....
No comments:
Post a Comment