ምልሰት.....የመጀመሪያው አመፅ
ከህዳር ፮ ፩፱፰፫ እስከ መጋቢት ፩፬ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም. ማስታወሻ ለመፃፍ መስነፌን ልብ በል/በይ:: አሁን በዚህ ዘመን እዚህ ብሎግ ላይ ይህን በማሰፍርበት ወቅት በታህሳስ ጥርና የካቲት ወራት ፩፱፰፫ አ.ም. ለምን ማስታወሻ እንዳላሰፈርኩ ላስታውስ አልቻልኩም:: ከህዳር ፮ ፩፱፰፫ በሁዋላ የተከሰቱት ዋና ዋና ጉዳዮች የክሪማስን ፈተና: የሁለት ሳምንት የቤተሰብ ጋ እረፍትና እንዲሁም ከጥቂት ልጆች በስተቀር የሁላችንንም ወደ ሁለተኛው ሴሚስተር ማለፍ ይጨምራሉ:: ከሁሉም የበለጠው ዋናው ክስተት ግን ከእረፍታችን ጥቂት ቀደም ብሎ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች አመፅ ነበር:: የጤና ሳይንሱ የመጀመሪያ የህክምና ተመራቂዎች ሊቀ መንበር መንግስቱ ሃይለማርያም በተገኙበት መመረቃቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ይህ ብሶታዊ አመፅ በርካታ ተማሪዎችን ለእስር ቤት ዳርጉዋል:: የአመፁ ዋና ምክንያት ገና ለገና ሊቀመንበሩ ይመጣሉ በሚል:ትኩረት ሁሉ ወደ ምርቃቱ ስነስርዓት ተደርጎ የለተለት እንቅስቃሴዎች ችላ በመባላቸው በተለይ በተማሪዎች ምግብ ቤት ውስጥ ኃይለኛ የጥራት ጉድለት በመከሰቱ ነው:: ምንም የማልረሳው ነገር ቢኖር የምርቃቱ ቀን በእጣ ከየባቹ ምርቃቱ ላይ እንዲገኙ ከተፈቀደላቸው አምስት አምስት ተማሪዎች በስተቀር ሌሎቻችን በሌሊት ቅጥር ግቢውን ለቀን እንድንወጣ ተፈርዶብን እየተደናበርን በጨለማ ከየመኝታ ክፍላችን መልቀቃችን ነው:: ለምሳም እንዳንመጣ ተነግሮን ነበር:: ለነገሩ የምርቃቱ ቀን ማታ በትልቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ላባለስልጣኖች የተደረገ ግብዣ ስለነበር ለተማሪዎች እራትም አልተዘጋጀም:: የተማሪዎች መከፋት እየባሰ ሄዶ የገነፈለው ግን በምረቃው ማግስት እሁድ በተማሪዎች ምግብ ቤት እራት ሰዓት ላይ ዘወትር በሚቀርበው ስጋ (ዜርፎር) ፋንታ ልሙጥ ሽሮ በመዘጋጀቱ ነው:: በቦታው የነበርኩ ባይሆንም እንደሰማሁት ሁለት የአራተኛ ዓመት ሕክምና ተማሪዎች ኩሽናው ውስጥ በመግባት በከፍተኛ ወኔና ድፍረት በልሙጥ ሽሮ የተሞላውን ጎላ ድስት ባፍጢሙ ደፉት:: ከዚያም እራት ለመመገብ ሰልፍ ይዞ የነበረው ተማሪ በሙሉ ወደ ምግብ ቤቱ በመግባት ፈንታ ግልብጥ ብሎ ወደ ጤና ሳይንሱ የተለያዩ ህንፃዎች በመሄድ መስኮቶቻቸውን በድንጋይ መሰባባበር ጀመረ:: አንዳንድ ተማሪዎች የመኪኖች መስታወቶች ላይ ሳይቀር ይወረውሩ ነበር:: ይህን ተከትሎ አመሻሹ ላይ የጤና ሳይንሱ ሹማምንት ባደረጉት የድረሱልን ጥሪ በርካታ አረንጉዋዴ ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች ጤና ሳይንሱን በመውረር ያገኙትን ተማሪ በጡጫ: በርግጫና በዱላ በማለት ከግቢው ማስወጣት አልፎም በመኪና እየጫኑ ወደ እስር ቤት መውሰድ ጀመሩ:: ትንሽ ትንሽ ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ የታሰሩ ተማሪዎች በማግስቱ ተፈተው ነበር:: ከኛ ከአንደኛ ዓመት ተማሪዎች መካከል ሳይቀር የታሰሩ ነበሩ:: የግርግሩ ትኩሳት በማግስቱ የበረደ ቢሆንም ና ትምህርት ቢቀጥልም ከሁለት ሳምንት በሁዋላ አንዳንድ ተማሪዎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት መወሰድ ጀመሩ:: ለካ ውስጥ ውስጡን የጤና ሳይንሱ ሹማምንት ከአካባቢው የደርግ ደህንነት ጋር በመተባበር በአመፁ ጎልተው የታዩ ተማሪዎችን ዝርዝር በምግብ ቤቱ ኃላፊዎች ጠቁዋሚነት ሲያዘጋጁ ከርመዋል:: በጥቆማ ማሰሩ ሲጀመር ነበር ታዲያ እኔና ጉዋደኞቼ የተጠማነውን የቤተብና የወዳጅ ናፍቆት ለመወጣት ወደየቤታችን የገስገስነው:: እኛ ከእረፍት እስከምንመለስ በነበረው ጊዜ የአንዳንድ ተማሪዎች ቀስ በቀስ መታሰር የወለደው ሌላ ሁሉን አቀፍ የተማሪዎች አመፅ ጎልቶ ወጣ:: ወደ አስራ አምስት የሚሆኑ ተማሪዎች የመጀመሪያው አመፅ ዋና አንቀሳቃሽ ናችሁ ተብለው ታስረው ነበር :: የቀረው ተማሪ በሙሉ የታሰሩት ካልተፈቱ ትምህርታችንን አንማርም ብሎ ሲል የጤና ሳይንሱ ሽማምንት ደግሞ ተማሪዎችን እንደዛ የምትሉ ከሆነ ጤና ሳይንሱን ለቃችሁ ወደየቤታችሁ ሂዱ አሉዋቸው:: ተማሪዎችም በአንድነት የመልቀቂያ ክሊራንስ ማስፈረም ጀመሩ:: በዚህን ጊዜ ነው የጅማ አካባቢ ኢሰፓ ሊቀመንበር የሆኑት ዳዲ ሁንዴ የተባሉ ባለስልጣን በጉዳዩ በመግባት ሁኔታውን እንዲበርድ ያደረጉት ሲባል ሰምቻለሁ:: ይመስለኛል የታሰሩት ልጆች በማስጠንቀቂያ ተለቀቁ ና ትምህርት አፍታም ሳይቆይ እንደ በፊቱ ቀጠለ:: የምግብ ቤቱም ሁኔታ ብዙም መሻሻል ሳያሳይ ሕይወት ቀጠለ....ታዲያ እኔ ሌሎች የባሱ አመፆች ወደፊት እንደሚመጡ በማላውቅበት በዚያ ሰዓት ያ የምግብ ቤት አመፅ የመጨረሻው መስሎ ተሰምቶኝ ነበር.......