Tuesday, February 25, 2014

የመጀመሪያው አመፅ


ምልሰት.....የመጀመሪያው አመፅ 

ከህዳር ፮ ፩፱፰፫ እስከ መጋቢት ፩፬ ቀን ፩፱፰፫ አ.ም. ማስታወሻ ለመፃፍ መስነፌን ልብ በል/በይ:: አሁን በዚህ ዘመን እዚህ ብሎግ ላይ ይህን በማሰፍርበት ወቅት በታህሳስ ጥርና የካቲት ወራት ፩፱፰፫ አ.ም. ለምን ማስታወሻ እንዳላሰፈርኩ ላስታውስ አልቻልኩም:: ከህዳር ፮ ፩፱፰፫ በሁዋላ የተከሰቱት ዋና ዋና ጉዳዮች የክሪማስን ፈተና: የሁለት ሳምንት የቤተሰብ ጋ እረፍትና እንዲሁም ከጥቂት ልጆች በስተቀር የሁላችንንም ወደ ሁለተኛው ሴሚስተር ማለፍ ይጨምራሉ:: ከሁሉም የበለጠው ዋናው ክስተት ግን ከእረፍታችን ጥቂት ቀደም ብሎ በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች አመፅ ነበር:: የጤና ሳይንሱ የመጀመሪያ የህክምና ተመራቂዎች ሊቀ መንበር መንግስቱ ሃይለማርያም በተገኙበት መመረቃቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ይህ ብሶታዊ አመፅ በርካታ ተማሪዎችን ለእስር ቤት ዳርጉዋል:: የአመፁ ዋና ምክንያት ገና ለገና ሊቀመንበሩ ይመጣሉ በሚል:ትኩረት ሁሉ ወደ ምርቃቱ ስነስርዓት ተደርጎ የለተለት እንቅስቃሴዎች ችላ በመባላቸው በተለይ በተማሪዎች ምግብ ቤት ውስጥ ኃይለኛ የጥራት ጉድለት በመከሰቱ ነው:: ምንም የማልረሳው ነገር ቢኖር የምርቃቱ ቀን በእጣ ከየባቹ ምርቃቱ ላይ እንዲገኙ ከተፈቀደላቸው አምስት አምስት ተማሪዎች በስተቀር ሌሎቻችን በሌሊት ቅጥር ግቢውን ለቀን እንድንወጣ ተፈርዶብን እየተደናበርን በጨለማ ከየመኝታ ክፍላችን መልቀቃችን ነው:: ለምሳም እንዳንመጣ ተነግሮን ነበር:: ለነገሩ የምርቃቱ ቀን ማታ በትልቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ላባለስልጣኖች የተደረገ ግብዣ ስለነበር ለተማሪዎች  እራትም  አልተዘጋጀም:: የተማሪዎች መከፋት እየባሰ ሄዶ የገነፈለው ግን በምረቃው ማግስት እሁድ በተማሪዎች ምግብ ቤት እራት ሰዓት ላይ ዘወትር በሚቀርበው ስጋ (ዜርፎር) ፋንታ ልሙጥ ሽሮ በመዘጋጀቱ ነው:: በቦታው የነበርኩ ባይሆንም እንደሰማሁት ሁለት የአራተኛ ዓመት ሕክምና ተማሪዎች ኩሽናው ውስጥ በመግባት በከፍተኛ ወኔና ድፍረት በልሙጥ ሽሮ የተሞላውን ጎላ ድስት ባፍጢሙ ደፉት:: ከዚያም እራት ለመመገብ ሰልፍ ይዞ የነበረው ተማሪ በሙሉ ወደ ምግብ ቤቱ በመግባት ፈንታ ግልብጥ ብሎ ወደ ጤና ሳይንሱ የተለያዩ ህንፃዎች በመሄድ መስኮቶቻቸውን በድንጋይ መሰባባበር ጀመረ:: አንዳንድ ተማሪዎች የመኪኖች መስታወቶች ላይ ሳይቀር ይወረውሩ ነበር:: ይህን ተከትሎ አመሻሹ ላይ የጤና ሳይንሱ ሹማምንት ባደረጉት የድረሱልን ጥሪ በርካታ አረንጉዋዴ ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች ጤና ሳይንሱን በመውረር ያገኙትን ተማሪ በጡጫ: በርግጫና በዱላ በማለት ከግቢው ማስወጣት አልፎም በመኪና እየጫኑ ወደ እስር ቤት መውሰድ ጀመሩ:: ትንሽ ትንሽ ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ የታሰሩ ተማሪዎች በማግስቱ ተፈተው ነበር:: ከኛ ከአንደኛ ዓመት ተማሪዎች መካከል ሳይቀር የታሰሩ ነበሩ:: የግርግሩ ትኩሳት በማግስቱ የበረደ ቢሆንም ና ትምህርት ቢቀጥልም ከሁለት ሳምንት በሁዋላ አንዳንድ ተማሪዎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት መወሰድ ጀመሩ:: ለካ ውስጥ ውስጡን የጤና ሳይንሱ ሹማምንት ከአካባቢው የደርግ ደህንነት ጋር በመተባበር በአመፁ ጎልተው የታዩ ተማሪዎችን ዝርዝር በምግብ ቤቱ ኃላፊዎች ጠቁዋሚነት ሲያዘጋጁ ከርመዋል:: በጥቆማ ማሰሩ ሲጀመር ነበር ታዲያ እኔና ጉዋደኞቼ የተጠማነውን የቤተብና የወዳጅ ናፍቆት ለመወጣት ወደየቤታችን የገስገስነው:: እኛ ከእረፍት እስከምንመለስ በነበረው ጊዜ የአንዳንድ ተማሪዎች ቀስ በቀስ መታሰር የወለደው ሌላ ሁሉን አቀፍ የተማሪዎች አመፅ ጎልቶ ወጣ:: ወደ አስራ አምስት የሚሆኑ ተማሪዎች የመጀመሪያው አመፅ ዋና አንቀሳቃሽ ናችሁ ተብለው ታስረው ነበር :: የቀረው ተማሪ በሙሉ የታሰሩት ካልተፈቱ ትምህርታችንን አንማርም ብሎ ሲል የጤና ሳይንሱ ሽማምንት ደግሞ ተማሪዎችን እንደዛ የምትሉ ከሆነ ጤና ሳይንሱን ለቃችሁ ወደየቤታችሁ ሂዱ አሉዋቸው:: ተማሪዎችም በአንድነት የመልቀቂያ ክሊራንስ ማስፈረም ጀመሩ:: በዚህን ጊዜ ነው የጅማ አካባቢ ኢሰፓ ሊቀመንበር የሆኑት ዳዲ ሁንዴ የተባሉ ባለስልጣን በጉዳዩ በመግባት ሁኔታውን እንዲበርድ ያደረጉት ሲባል ሰምቻለሁ:: ይመስለኛል የታሰሩት ልጆች በማስጠንቀቂያ ተለቀቁ ና ትምህርት አፍታም ሳይቆይ እንደ በፊቱ ቀጠለ:: የምግብ ቤቱም ሁኔታ ብዙም መሻሻል ሳያሳይ ሕይወት ቀጠለ....ታዲያ እኔ ሌሎች የባሱ አመፆች ወደፊት እንደሚመጡ በማላውቅበት በዚያ ሰዓት ያ የምግብ ቤት አመፅ የመጨረሻው መስሎ ተሰምቶኝ ነበር.......

Wednesday, February 19, 2014

Unknown B

ህዳር ፮ ቅን ፩፱፰፫ አ.ም.

Unknown B

እኔና እኔን መሰል የህክምና ተማሪዎች ጠዋትና ከቀትር በሁዋላ ለትምህርት: ማታ ማታ ደግሞ ለጥናት በምናውለው ሰዓት ምክንያት እረፍት አጥተን ግዜ እያጠረን: የ ቀኑን መሮጥ ሳናውቀው: በእለት ተለት ክስተቶች ታጅቦ ግዜ ወደፊት ሲነጉድ የግዜን ተቃራኒ አቅጣጫ ይዞ ደሞ የ ግማሽ ሰሚስተር ፈተና ከች አለ! 

ከፊዚክስ በስተቀር በሁሉም የትምህርት አይነቶች ፈተና ለመውሰድ የቀረን አንድ ሳምንት ብቻ ነው:: ፊዚክስ ፈተና ነገ እንወስዳለን! ወይኔ! አሁን ይሄን በምፅፍበት ሰዓት ብዙዎቹ እኔን መሰሎች በየሌክቸር ሆሉ: በየ ዶርሙ: በላይብረሪው ጥጋጥጎች እንዲሁም ውጭ ሳይቀር ባገኙት አመቺ ቦታ ሁሉ ተቀምጠው ረዛዥም በሆኑ የፊዚክስ ቀመሮች ራሳቸውን ያለማምዳሉ:: ነገ በ ፍሬሽማን ሌክቸር ሆል ውስጥ መንኮራኩር ይመጥቃል! የብርሃን ጉዞ: የኮስሞስ ና የ አስተሮይድ ርቀት ይለካል...

ይህችን አጭር የሆነች ማስታወሻ ከመዝጋቴ በፊት አንድ ነገር ልበል:: አሁንም በባዮሎጂ ላቦራቶሪ ውስጥ የሚፈጠሩ አጋጣሚዎቼ እንደቀጠሉ ናቸው:: ከትናንት ወዲያ ከሰዓት የምግብ አይነቶችን መለየት በሚል ርዕስ በላቦራቶሪ ውስጥ የሚገኙ Pipettes (ፓይፔትስ) በመጠቀም የተለያዩ ኬሚካሎችን ካንዱ ብርጭቆ ወደ አንዱ የማገለባበጥ ሥራ ላይ ነበርን:: በመጀመሪያ ምን እንደነካኝ አላውቅም አንድ ቴስት ቱብ ሰበርኩ:: የሱ ሳያንስ ትንሽ ቆይቼ አንድ "Unknown B" የሚል ፅሁፍ የሰፈረበት ቴስት ቱብ ውስጥ ያለን ኬሚካል ወደ Pipette ውስጥ ለመሳብ ዘወትር እንደሚደረገው  በመጠኑ በፓይፔቱ በላይ በኩል በአፌ ሳብ አደርጋለሁ ስል ኬሚካሉ እየተምዘገዘገ ወጥቶ አፌ ውስጥ ተዘራ:: በ reflex action ጠጣሁት:: ምንም ምንም አይልም ለነገሩ: 

ምንነቱ ያልታወቀ ነገር በመጠጣቴ ደነገጥኩ: ግን ጠጥቼ ቀና ስል ማንም መጠጣቴን እንዳላስተዋለ ተገነዘብኩ:: ጎሽ! ሁሉም በየራሱ ጠረቤዛ ላይ በተመሳሳይ ሥራ ተጠምዱዋል: ግማሹ እንደኔ ፓይፔት ይዞ መጠጣ ያካሂዳል:: ሌላ የጠጣ ቢኖርስ? አልኩ በሆዴ:: ማን መጠጣቱን ማን ያውቃል? 

Unknown B ከጠጣሁ ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ምንም የተከሰተብኝ  ነገር ባለመኖሩ ፍርሃቴ ለቀቀኝ........

Wednesday, February 12, 2014

ጥቅምት ፪፭ ፩፱፰፫ አ.ም.

ጥቅምት ፪፭ ፩፱፰፫ አ.ም. ከምሽቱ ሰባት ሰዓት

በዚህ ሰዓት የ ፍሬሽማን ትምህርት  ሞቅ ያለ ሲሆን የኔ የሰፈር ና የ ቤተስብ ናፍቆት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከስሟል:: የጤና ሳይንሱ ኑሮ ተስማማኝም ልበል? የግቢው ማህበረ-ነፍሳት አባላት የሆኑት ቢምቢዎች ሰውነቴን ነካክሰው የጣሉብኝ ጉብ ጉቦች ሁሉ ጠፉልኝ:: ጥሩ ነው መቼም...ግና ያው የኔ የሆኑት ራስ አመጣሽ የሀሳብ እክሎች ና ጉርብጣቶች እንደቀጠሉ ናቸው:: ከነዚህ የሚቆርቁሩ እሳቤዎች አንዱ ራሴ ያወጣሁትን ፕላን በስራ ላይ አለማዋሌ ነው:: ማስታወሻዬ: ፕላን ስል ደግሞ ትልቅ ነገር አይምሰልሽ:: መቼ ሂሳብ: መቼ እንግሊዝኛ: መቼ ባዮሎጂ.. ወዘተ እንደማጠና የሚገልፅ ሰንጠረዥ ማለቴ ነው:: በያንዳንዱ የትምህርት አይነት ያወቅነው እየበዛ የሄደ ሲሆን የትየለሌ የሆነብኝ ግን ገና ልናውቅ የሚገባን ነው:: እንግዲህ ይህን ልናውቅ የሚገባንን ነው ተቀምጠን መፃሕፍት ላይ አይናችንና ቀስረን ለዘለቄታው የምናውቀው ይሆን ዘንዳ በግብረ ህሊና እንድናትመው ኃላፊነት የተጣለብን:: ሌላው እንግዲህ የሚጠበቅብን ነገር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የ ትውስታ ማህደራችንን መክፈት ነው::  አሁን ይሄን ሁሉ እንዴት ነው ማስታወስ የሚቻለው?  

ከ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ትንሽ ከፍ ብሎ በሚገኘው ሌክቸር ሆል ውስጥ ከኮርኒሱ ላይ ከላይ እስከ ታች የተገጠገጡትን ፍሎረሰንት አምፑሎች አብርተን እኔና እኔን መሰል የፍሬሽ ማን ህክምና ተማሪዎች ምሽቱን ስናነብ አንዳንዶቻችንም ስናንጎላጅ እንቆያለን:: የእውነት እንቅልፉ የመጣበት ቶሎ ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ ይሄዳል ለመተኛት ወይም አልጋ ላይ ለማንበብ ለመሞከር (እኔ በብዛት እንደማደርገው):: የበረታ ደግሞ እስከ ምሽቱ ሰባት ወይም ስምንት ብሎም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይቆያል::

በቀደም ለት የባዮሎጂና የኬምስትሪ ላቦራቶሪ ረፖርት ውጤት ሲታደለን እኔ ሁለቱንም አስር ከአስር ነበር ያገኘሁት:: ብርታት ብጤ ተሰምቶኛል:: ያን ብርታት የተቀዳጀሁ ቀን ታዲያ ሌላ የባዮሎጂ ላቦራቶሪ ክፍለ ግዜ ነበር::አላማው የእንሰሳትና የእፅዋትን ሴሎች በአጉሊ መነፅር ማየት ነበር:: ክጉንጫችን የውስጥ ክፍል ላይ በስንጥር ጫር አርገን  በእንሰሳ ሴልነት እንድናቀርብ ኢንስትራክተሩ የነገረን ሲሆን ከኔጋ አጉሊ መነፅር የምትጋራው ሴት ልጅ ግን ጉንጭዋን ለመጫር የፈራች ይመስል ስታመነታ አየሁዋት:: ታዲያ እኔ ወንዱ አለመፍራቴን ለማሳየትም ይሁን ያ አስር ከአስሩ ውጤት የሰጠኝ የልብ ልብ ጉንጬን በውስጥ በኩል በኃይለ ጣት ጫርኩት:: ድርጊቱን ስለደጋገምኩት ጫጫርኩት ብለው ይሻላል:: በመጀመሪያ ከጥፍሮቼ ሁሉ ረዝማ በምትታየው በቀኝ ትንሹዋ ጣቴ ጥፍር የጫርኩትን ስንመለከተው ሌላ ነገር ሆኖ ተገኘ:: ከዚያ በስንጥር ጉንጬ ተልጦ እስከሚደማ ደጋግሜ በመጫር በመጨረሻ ተሳክቶልን Epithelial Cell አየን::

በዚያው ሰሞን ወደ አዲሳባው ቤታችን ስልክ መታሁ:: አባቴንና እናቴን አነጋገርኩዋቸሁ:: ገንዘብ ስጡኝም አልኩዋቸሁ:: ባጋጣሚ ቤተሰቦቼ ካሉበት ሰፈር ወደ ጤና ሳይንሱ የሚመጣ ተማሪ ስለነበር በሱ በኩል ገንዘብና ለመፃፍ የሚያያገለግሉኝ በርካታ ብዕሮች ተላኩልኝ:: ቤተሰቤ ዉስጥ ያሉ ልጅ አዋቂ ሳይባል እናቴን ጨምሮ: ከጎረቤትም አንዲት ልጅ ደብዳቤ ላኩልኝ:: አባቴ ደግሞ ግለሰብ ዝንጉ ነው በሚል የኢትዮጵያ ፖስታ አግልግሎት ድርጅትን በመጠቀም የላከው ዳብዳቤ በጅጤሳ የተማሪዎች ዲን ፅህፈት ቤት በኩል መጣ:: ምን ቢሆን ጥሩ ነው ታዲያ:: ምንም አልመሰለኝም:: ከ አንድ ወር በፊት ቢሆን ጮቤ የሚያስረግጠኝ ነበር:: ከላይ እንዳልኩት የቤተሰብ ናፍቆት ጭምብል ከላዬ ላይ ወልቆ ነበር.... 

Wednesday, February 5, 2014

ምቾት አልባ ጅምር

ጥቅምት ፩፰ ፩፱፰፫ አ.ም.

ምቾት አልባ ጅምር...

ዛሬ ጅማ ከደረስኩ ልክ አንድ ወር ሆነኝ:: የቤተሰብና የሰፈር ናፍቆት እየለቀቀኝ የሄደ ቢሆንም የቀዩ ሸክላ አዳራሽ ኑሮ ግን በጭራሽ አልተስማማኝም:: በተደጋጋሚ የሐይ ስኩል ተማሪነት ግዜዬ ና ትምህርት ቤቴ ራሱ እንዲሁም ያለፈው ዓመት ወራቶች በመልካም ሁኔታ ትዝ ይሉኛል:: ፀጥታን ከምንም በላይ የምወድ መሆኔን ያወቅሁት እዚህ አዳራሽ ውስጥ ነው:: መኖሪያ ቤታችን በስተጉዋሮ ከመሬት አንድ ሜትር ከፍ ብላ የምትገኘው የመኝታ ና የ ጥናት ከፍሌን አስታወስኩ:: ሃይ ስኩልን ሙሉ የሄድኩበት አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት የጠዋት ክፍለ ግዜ ሲጠናቀቅ አልፎ አልፎ መፅሐፍት ቤት ለመሄድ ካልሆነ በቀር ዘወትር ወደ ቤት ነበር የምገሰግሰው:: ታዲያ ከሰዓት በሁዋላ ሰፈራችን ፀጥ ይላል:: በፀሃያማዎቹ  የበጋ ወራት ከቀትር በስቲያ አልፎም በከዋክብት ና በጨረቃ ደምቆ ፀጥታን በተላበሰ ሌሊት ደብተሮችና ና መፅሐፍት ገላልጬ ከጥናት ጠረጴዛዬ ላይ የማሳልፈው ግዜ ታወሰኝ:: አንዳንዴ ከ አሮጌው ቴፕ ረኮርደር የሚወጡ የአማርኛ ዘፈኖችን እየሰማሁ ከ College Physics/Algebra መፅሀፎች የ ፊዚክስ ና የሂሳብ ጥያቄዎችን ስሰራ የሚነጋበት አጋጣሚ አለ:: ያ... ለብቻዬ ነገሮችን አከናውንበት የነበረውን ግዜ አሁን እዚህ ላገኘው አልቻልኩም:: እስቲ አንቺ ማስታወሻዬ አስቢው አንድ ሰው ከ ጥቂት ወራት በፊት ለብቻ ግዜን ከማሳለፍ ተነስቶ በድንገት ከ ፬፱ ሌሎች ሰዎች ጋር በ አንድ ጣራ ስር ሲያድር እንዴት አዲስ አይሆንበት?:: ጩሀት: ወሬና ገርግር ቀኑን ሙሉ የአዳራሹ መለያ ምልክቶች መሆናቸውን ቀጥለዋል:: 

ሌላው የሚገርመው እዚህ አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ምንም ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ሳልሰራ ድካምን መቀዳጀቴ ነው:: ኮሌጅ ውስጥ እንደዚህ አይነት ስሜት መቼም አስጊ ነው: ምክንያቱም በድካም ጥናት አጠና መፅሀፍም አንብቤ እረዳ ዘንድ ከቶ አይቻለኝም:: ምሽት ላይ እንደሌሎቹ እኔን መሰሎች ቀን ትምህርት በምንቅስምበት ሌክቸር አዳራሽ ተገኝቼ ለማንበብ: ከንባቡ ውስጥም ፍሬ ነገሩን እየቁዋጨሁ ወደ ትውስታ ማህደር ለማኖር ስሞክር በመጀመሪያ አይኖቼ በእንባ ይሞላሉ: እንደ አለርጂክ መሆኑ ነው:: ያሳክከኛል ሁሉ:: ከዚያም ቶሎ ቶሎ በረጅሙ ያዛጋኛል ብሎም አልጋ ላይ ስወጣ ብቻ የሚጠፋው እንቅልፌ ይመጣል:: እሺ ይበቃኛል ብዬ ና ትቸው ወደ ቀዩ የሸክላ አዳራሽ እንዳልመለስ ከጥናት ና ቀን ከሞነጫጨሩት ማስታወሻ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ያቀረቀሩት ሌሎቹ እኔን መሰሎች ያስቀኑኛል::  ማስቀናት ብቻ አይደለም ውስጣዊ ሽብር ይነዙብኛል....

ለመጀመሪያ ግዜ ከዚህ ትምህርት ቤት ወድቄ እባረር ይሆን? ብዬ አሰብኩ:: የ ክሪስማስን ፈተና በርቀት አስቤው የማልፈው አልመስልህ አለኝ:: ለዚህ አይነት ስሜት በውስጤ መፈጠር ምክንያት ከሆኑት ክስተቶች አንዱ በቀደም ለት የተሰጠን የባዮሎጂ ና የ ኬሚስትሪ ላቦራቶሪ ረፖርት ውጤት ነው:: ባዮሎጂ ስምንት ከ አስር እንዲሁም ኬምስትሪ ሰባት ከአስር ይላል የኔ ውጤት:: ጅጤሳ ትመህርት ከጀመርኩ የመጀመሪያዎቹ የሆኑት እነዚህ ውጤቶች አላስደሰቱኝም:: ወይኔ ሃይ ስኩል! ይባስ ብሎ የከሚስትሪ ውጤት ላይ "Please do not copy from your friend" የሚል አስተያየት ተፅፎበታል:: ወይ አምላኬ.........