ዳግም ሲጀመር
ሰኞ መስከረም ፩፪ ቀን ፩፱፰፬ አ.ም.
ከደርግ ውድቀት በሁዋላ በተከተለው መስከረም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቁዋማት ሁሉ በራቸውን ለተማሪዎች ክፍት በማድረጋቸው ወደ ጅማ ጤና ሳይንስ አቀናሁ:: ትምህርትም ዛሬ ተጀመረ:: የሚሳዝነው ግን አሁንም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ መሆኔ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ባለፈው ዓመት ማደሪያዬ ከነበረው ቀይ የሸክላ አዳራሽ ውስጥ መገኘቴ ነው:: አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ነው:: ባለፉት ስድስት ወራት ዉስጥ የተከሰቱ የባህሪ ለውጦች ለውስጤ ይሰሙታል:: እንደበፊቱ ቀልድ የማላበዛ መስሎ ይሰማኛል:: ፊቴ ላይ እንደሚገለፅ እርግጠኛ ባልሆንም ውስጤ ግን ኮስታራነት ይሰማኛል:: ለሰላምታ ግድ የለሽ የሆንኩም ይመስለኛል:: በፊት ለመሰንዘር አመነታባቸው የነበሩ ቃላትን አሁን እንደዋዛ እናገራቸዋለሁ: ስለ ሌሎች ሰዎች ማሰብም ሆነ መጨነቅ አይዳዳኝም:: ከደብዳቤ አቅም እንኩዋን ጉዋደኞቼን ትቼ ለቤተሰቤ ብቻ ነው የፃፍኩት: ያውም በመከራ: አምና የነበረኝ የከረመ ፍቅርም እየወጣልኝ ነው መሰለኝ ልጅቱዋን አስቢያት አላውቅም: ቶሎ እበሳጭ የነበረውንም ትቻለሁ...ጉርምስናዬ ዘግይቶ መጥቶ ነው ማለት ነው??
ትምህርታችን ባለፈው ወደ ብላቴ የዘመትን ግዜ ካቆመበት እንደሚቀጥልና ወደሁዋላም ተሂዶ በሌክቸር የሚከለስ ነገር እንደሌለ ተነግሮናል:: ስለዚህ በንባብ ድጋፍ ተሃድሶ ማድረግ ይጠበቅብናል:: በመጪው ታህሳስ ወር የአንደኛ ዓመት ትምህርታችንን እናጠናቅቃለን ተብሎ ይጠበቃል::
ለምን እንደሆነ ባላውቅም ትምህርቱ ዳግም የሚቁዋረጥ መስሎ ይሰማዋል: ለውስጤ:: ያለፉት ስድስት ወራት ያሳዩኝ ከፍተኛና በቁጥር በርካታ የሆኑ የሀገር ውስጥ
ለውጥ እንቅስቃሴዎች ያሳደሩብኝ ተፅዕኖ ይሆን? የቅርብ ጉዋደኞቼንም ሳያቸው ለትምህርቱ ግድ የለሽ የሆኑ ይመስላሉ:: በቃ በጤና ሳይንስ ግቢ ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴ የውሸት የውሸት ሆኖ ይሰማኛል….
ሐሙስ መስከረም ፩፭ ፩፱፰፫ አ.ም.
ከምሽቱ ፭ ሰዓት ከ ፪፭:: እንደሚመስለኝ አሁን ትምህርት የምር ተጀምሩዋል:: ብዙዎችን ከልባቸው ሲያነቡና መፅሐፍት ይዘው ሲንቀሳቅሱ ላይብረሪውንም ሲጠቀሙ ማየት ጀመርኩ:: እንደአምናው ሌሎችን
ሲያነቡ ሳይ መደናገጥ አሁን በጭራሽ አልዳሰሰኝም:: የማንበብ ፍላጎቴ እስከአሁን ብቅ አላለም:: ይገርማል:: ይበልጥ የገረመኝ ና ያሳሰበኝ ግን ይህ ሳይሆን ባለማንበቤ "ለምን አላነበብኩም?" ብዬ አለመጨነቄ ነው:: ቀለል አድርጌ ነው የያዝኩት:: በተለይ ላይብረሪ ውስጥ እስካሁን በተከታታይ ከአስራ አምስት ደቂቃ በላይ የቆየሁበት ጊዜ የለም:: በብዛት በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ እየተራመድኩ የተለያዩ ሃሳቦችን ባይምሮዬ ማሰላሰል ይቀናኛል እንዲሁም ይቀለኛል ::
ሌክቸር ላይ ያለኝ የማዳመጥ ጉጉት ና አንክሮ ከቀድሞው በእጅጉ ቀንሱዋል:: ለዚህም ግድ የለኝም:: ክለሳን በሚመለከት ከስድስት ወራት በፊት በደብተሮቼ ላይ ያሰፈርኩዋቸውን የሌክቸር ማስታወሻዎች ስመለከት በተለይ ሂሳብና ኬሚስትሪ ከብደው ና የማይገፉ ሆነው የታዩኛል::
No comments:
Post a Comment