ታህሳስ ሃያዎች-አስራዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት አ.ም.
የፍረሽማን ማጠቃለያ ፈተና ሰሞን
ለፈተናችን ሶስት ቀን ሲቀረው አራት ትምህርቶች እንደኮሶ አስጠሉኝ: ፊዚክስ: ሶሺዮሎጂ: ፈርስት ኤይድ ና ኮሙኒቲ ሄልዝ:: ለትምህርትና ለንባብ የነበረኝን እጅግም ያልጋለ ፍላጎት ይበልጥ በረዶ እንዲሆን ያደረጉት እንዚህ ትምህርቶችና መምህራኖቻቸው ይመስሉኛል: አቤት ስጠላቸው! እርግጠኛ ነኝ ትምህርቶቹን ልጠላ የቻልኩት በመምህራኑ አስጠሊታ ና አታካች እንዲሁም የተዝረከረከ የማስተማር ዘዴ የተነሳ ነው:: በተለይ ፊዚክስ መምህር.....
የተዋበ መስሎ በሞራል የተጀመረው የአንደኛ ዓመት የህክምና ትምህርት በመሃል በዘመቻ ምክንያት ተቁዋርጦ: በመጨረሻው ላይ የሄው እንጨት እንጨት ብሎ ሊጠናቀቅ ነው:: የአንደኛ ሴሚስተር ውጤቴ መልካም የነበረ ቢሆንም ለዚህኛው ፈተና ዳግም ብቻ ሳይሆን የበለጠም ፈራሁ: እወድቅ ይሆን ብዬ...የተማሪ ነገር
ፈተናው በእንግሊዝኛና በካልኩለስ ተጀመረ:: አቤት ካልኩለስ መቼም ከባድ ነበር:: ሁሉም ተማሪ አማረረ:: እኔ በበኩሌ ከፈተናው ስወጣ ናላዬ ዞሮ ስለነበር በማግስቱ ጠዋት ለሚጠብቀኝ organic chemistry ፈተና ምንም አይነት የመጨረሻ ዝግጅት እንደማላደርግ እርግጠኛ ነበርኩ:: ሆኖም ግን organic chemistry ፈተና ያን ያህል አልከበደኝም ነበር:: organic
chemistry በተፈተንበት ቀን ከሰዓት የወሰድናቸው first aid ና community health ፈተኖችም ደህና ነበሩ::
በእውነቱ እዚህ ወቅት ላይ ቆም ብዬ በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው ወደ ሁለተኛ ዓመት እንደማልፍ ነው:: በዚህ ምንም ስጋት የለኝም::
ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቴ በአንደኛ ሴሚስተር ከነበረው በጣም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል:: ለነገሩ ምን አገባኝ ካለፍኩ...
organic chemistry ፈተና በወሰድንበት ቀን ማግስት biology ፈተና ይጠብቀኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ምሽቱን ያሳለፍኩት በቴሌቪዥን መመልከቻው አዳራሽ ውስጥ ነበር: relax እያደረኩ::
በተከታዮቹ ቀናት የቀሩትን ትምህርት አይነቶች በሙሉ ተፈተንናቸው::
የገና ዋዜማ ፩፱፰፬ አ.ም.
የአንደኛ ዓመት ማጠቃለያ ፈተናችንን ተከትሎ የገና በዓል ታህሳስ ሃያ ስምንት ቀን ተከበረ:: ለወትሮው በሃያዘጠኝ የሚከበር ቢሆንም የዘንድሮው ሃያዘጠኝ ረቡዕ ማለትም የፆም ቀን ላይ ስለዋለ ነው መሰለኝ ከፊቱ ባለው የፍስክ ቀን እንዲከበር ሆነ:: የሆነ ሆኖ በዛሬው በዓል የሚደሰቱ ከሆን ደስ ሊላቸው የሚችሉት ለሃይማኖታቸው ያደሩ የ ጴንጤ ና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ይመስሉኛል:: ምክንያቱም ካለፈው አርብ ጀምሮ ዛሬ አምስተኛ ቀን መሆኑ ነው: በጅማ ከተማ የኤሌትሪክ ኃይል ተቁዋርጡዋል:: መብራት የለም:: በዚህም ምክንያት ለማክሰኞ ዋዜማ ሰኞ ምሽት ሊደረጉ ታስበው የነበሩ የመዝናኝና የሙዚቃ ምሽቶች ሳይካሄዱ ቀሩ:: እኔና ጉዋደኞቼም አብይ ተውሶ ባመጣው ቴፕ ረኮርደር ዶርማችን ውስጥ ሙዚቃ እየሰማን ለመጨፈር አቅደን ነበር:: ምን ዋጋ አለው...አልሆነም:: ለነገሩ እነ መንጌ: አብይ: አምሳሉ: ማስረሻ ና ሚሊዮን ወደ ግሪን ሆቴል ሄደው ጠጣ ጠጣ አድርገው ተመለሱ:: እኔ ያልጠጣሁ ቢሆንም የዋዜማውን ምሽት አብሬያቸው ዋይት ሃውስ በሚገኘው ዶርም 006 ስጫወትና ስዘፍን አመሸሁ:: ዶርሜ ባይሆም እዚያው አደርኩ:: የዶርሙን ጨለማ በገፈፈች አንዲት ሸንቃጣ ሻማ ታግዘን የእንግሊዝኛና የአማርኛ ዘፈኖች እራሳችን እየዘፈንን ዶርሙንም ሆነ አጎራባች ዶርሞችን በጠበጥናቸው:: በተለይ መንጌ አይረሳኝም: ከዚያ ቀን በፊት አሳይቶት በማይውቅ ሁኔታ ይደንስና ይጫወት ነበር……ትዝታ
No comments:
Post a Comment