ግንቦት 1 1984 አ.ም. ቅዳሜ
ሳይታወቅ የግንቦት ወር ከተፍ አለ:: በትናንትናው እለት የተጠናቀቀው ያለፈው የትምህርት
ሳምንት በከፍተኛ ሁኔታ የተሯሯጥኩበት ሳምንት ነበር:: እኔ ብቻ
ሳልሆን ጉዋደኞቼም ጭምር:: የሁለተኛ ዓመት ትምህርት ኮስተር እያለ መጥቷል! ፕሮፌሰር ሳላህ ከያንዳንዱ ሌክቸር በሁዋላ በልምጥምጥ
አራት መአዘን ፕላስቲክ ላይ የሳላቸውን የአናቶሚ ስእሎች ትቶልን ይወጣል:: እኛም ስሎቹን ደብተራችን ላይ ለመገልበጥ በምናደርገው
ወንድማዊና እህታዊ ሽሚያ ግዚያችንን እንፈጃለን:: ግልበጣው ሰውነት ያዝላል:: እኔ በበኩሌ ከዚህ በፊት አሳይቼው በማላውቀው ሁኔታ
የትምህርት ፍላጎቴ የጨመረ ቢሆንም በተለያዩ ጅጤሳ ነክ ምክንያቶች የጥናት ፕሮግራሜ መሰናከሉ አልቀረም:; አሁን ባለፈው አመሻሹ
ላይ ቤተ መፅሐፍት ገብቼ አጠናለሁ በሚል ወደዚያው አቅንቼ ሳለ ተዘግቶ ጠበቀኝ:: እንዲያውም ለካ ቤተመፅሃፍቱ ሳምንቱን ሙሉ ዝግ
ኑሯል:: ተስፋ ሳልቆርጥና እንደቀድሞው ስሜቴ ሳይነካ ቀን-ቀን የምንማርበት ክፍል (ሌክቸር ሆል) በመሄድ ማንበብ እንደጀመርኩ
መብራት ጠፋ! በውስጤ ሊገነፍል ያለን ቱግታ አፍኘ አደርኩ:: በማግስቱ ጠዋት በመልካም ስሜት ቀኑን በመጀመር የልብስ አጠባ ፕሮግራሜን
ለመተግበር በትጋት ወደ ቧንቧው ሳቀና ውሃ አልነበረም:: ምንም አይደለም በሚል በመልካም አመለካከቴ ቀጥዬና ደብተሬን ገልጬ ጠዋቱን
አናቶሚ ደስ እያለኝ አጠናሁ:: ከሰዓት የተቁዋረጠው የውሃ አገልግሎት ስለጀመረ ልብስ ማጠብ ጀመርኩ:: ነገር ግን በአጠባው በግምት
መሃል ላይ ውሃው እንደገና ተቁዋረጠ:: ይመለሳል ብዬ ለሰአታት ጠበኩ:: የቁራ መላክተኛ ሆኖ ቀረ:: ይህ ሲሆን ሰዓቱ ወደ አመሻሹ ገደማ ሆኗል:: በቀዳሚው ቀን ተቁዋርጦ የነበረው
መብራት የተመለሰ ቢሆንም ለኔ በዚህ ወቅት አስፈላጊ አልነበረም........
ግንቦት 3 1984 አ.ም. ሰኞ
ዛሬ ፊዚዮሎጂ ትምህርት በይፋ ጀመርን:: ጠዋትም ከሰዓትም በመማር: በጠቅላላ
ለአራት ሰዓት ያህል በጨቅላ ጭንቅላቶቻችን ውስጥ በፕሮፌሰር ማሂ አማካይነት በአይነት አዳዲስ የሆኑ እውቀቶች ተጠቀጠቁ::
የፒሲዋን ትምህርቶች ባጠቃላይ ሲነበቡ ደስ የሚያሰኙና የሚስቡ ሲሆኑ ነገር ግን እንደቀልድ
እየበዙና እየተከመሩ የሚሄዱ ናቸው:: በፒሲዋን ሌክቸር ሆል ውስጥ እልፍ ሳይንስ ይወራል:: እኛም እልፍ እንፅፋለን እልፍም እንዳምጣለን::
አናቶሚ ደሞ እልፍ ስዕል እንስላለን:: የፕሲዋን ሌክቸሮች በነፍስወከፍ ሁለት ሰዓት የሚፈጁ ሲሆን በመሃል የአምስት እስከ አስር
ደቂቃ እረፍት አለ:: በሌክቸሩ ክፍለጊዜ በያንዳንዷ ሰከንድ ከተናጋሪው አፍ የሚወጣው አዲስና ንጥር ጭብጥ ስለሆነ ለቅንጣት ጊዜ
ቀልብ ማጣት ወይም ዝንጉ መሆን ቁልፍ የሆነ ግንዛቤን ሊያሳጣ ይችላል:: ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ቀልብ ገዝተንና ነቅተን መምህራኑ
የተናገሩትን እያንዳንዱዋን ነገር ደብተራችን ላይ በብእራችን መከተብ ይጠበቅብናል:: ሰሞኑን ታዲያ በርካታ ተደጋግመው ቢነበቡም የሚረሱ ሃሳቦችን
ፃፍን:: በተለይ አናቶሚና ባዮኬምስትሪ በጣም ብዙ ሄደናል:: ፍሬሽማን ብንሆን ኑሮ እስካሁን በፃፍነውና ባደመጥነው ብዛት የመጀመሪያው
ሴሚስተር ተገባዶ ነበር- ይሄኔ!
ዛሬ ማታ እያጠናሁና እያነበብኩ ያመሸሁ ቢሆንም በጥናቱ አልረካሁም:: ባነባቸውም ላገናዝባቸው: ላብላላቸውና አንዱን ካንዱ ላገናኛቸው ያልቻልኩዋቸው የተለያዩ ጭብጦች (concepts) አሉ በተለይ ባዮከምስትሪ ውስጥ! ከላይ እንዳልኩት በዝንጋታና ቅፅበታዊ ቀልብ ማጣት የተነሳ ሳላዳምጥ ያመለጠኝ ነገር አለ መሰለኝ:.....
ዛሬ ማታ እያጠናሁና እያነበብኩ ያመሸሁ ቢሆንም በጥናቱ አልረካሁም:: ባነባቸውም ላገናዝባቸው: ላብላላቸውና አንዱን ካንዱ ላገናኛቸው ያልቻልኩዋቸው የተለያዩ ጭብጦች (concepts) አሉ በተለይ ባዮከምስትሪ ውስጥ! ከላይ እንዳልኩት በዝንጋታና ቅፅበታዊ ቀልብ ማጣት የተነሳ ሳላዳምጥ ያመለጠኝ ነገር አለ መሰለኝ:.....
በመጨረሻ:-እኔ በበኩሌ እየበዛ ቢሄድም እንኩዋን አናቶሚ ትምህርትን ከሁሉም በጣም
የወደድኩት ይመስለኛል:: እርግጠኛ ነኝ በስዕሉ ምክንያት ነው:: የተዋጣልኝ ባልሆንም ከልጅነቴ ጀምሮ ስዕል መሳል እወዳለሁ:: የአናቶሚ ስሎችን ስስል ለጊዜውም ቢሆን ትልቁን የፒሲዋን ጭንቀቴን እረሳለሁ........
No comments:
Post a Comment