እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 1985 አ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል
ቀንም ሆነ ማታም ሆነ:: ፒሲዋን ሁለተኛ ሴሚስተር ከተጀመረ ልክ 2 ሳምንት::
ከመጀመሪያው ሳምንት ይልቅ በሁለተኛው ሳምንት በጥናትና በንባብ በርትቼ ነበር እላለሁ:: እርግጥ ነው አንዳንዴ ዋይትሃውስ ፎቅ
ስር ባለው የተማሪዎች ቴሌቪዥን መመልከቻ አዳራሽ በኩል ሳልፍ በወቅቱ ከቴሌቪዥኑ በሚተላለፈው ዝግጅት ተስቤና ተሰናክዬ ወደ
አዳራሹም ገብቼ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት በመቀመጥ ከጥናቴ እዘናጋ ይሆናል:: ቢሆንም.....ቢሆንም.....የመኝታ ሰዓቴ
እስካሁን ድረስ ከምሽቱ 7 ሰዓት ዝቅ አላለም:: ሳነብም የማተኮሬና ሃሳቤን የመሰብሰቤ ሁኔታ እስካሁን መልካም ነው::
በጤና ሳይንሱ ግቢ ውስጥ በሁሉም ደረጃ ያሉ የሁክምና ተማሪዎች በሙሉ በፍጥነት ወዲያና
ወዲህ ሲሯሯጡ ማየት የየዕለት ክስተት ነው:: በቃ የሂወት ትንቅንቅ አካል ኖሮት ይታየኛል:: ታዲያ አይቼ አይቼ .....አይቼ
ይገርመኝና የህክምና ተማሪ በመሆኔ እደሰታለሁ:: እንደውጭ ሰው ሆኜ ሳየው ውስጡ መልሶ መግባት ይናፍቀኛል:: ግን ደግሞ
አለሁበት.....አይደል እንዴ?
ባለፈው ስለአለመጨነቄ ስናገር ነበር አይደል? ዛሬ ታዲያ ከኔ እጥፍ በጥፍ
የማትጨነቅ የኛው ባች አባል መኖሯን ላስታውስሽ ወደደኩ:: ትዕግስት! ከኔጋ እንደማንኛውም ተማሪ እንቀራረባለን:: አንዳንድ
ሁኔታዋ ያስገርመኛል:: ለምሳሌ በቁጥር በርከት ያሉ ሌክቸሮች ላይ አላየሁዋትም:: አንዳንዴ ደብተሬን ትዋሰኝና ገልብጣ
ትመልስልኛለች:: ያንደኛውን ሴሚስተር ያሳለፈችው እንደዚህ ነው:: በጣም በጣም ዘና ብላ:: ታዲያ የባዮስታትስቲክስ አንደኛ
ሴሚስተር ፈተና ውጤቷ B መሆኑ ገርሞኛል:: ማለቴ ትንቅንቅ ትይንት ውስጥ ላልታየ ተማሪ በጣም ጥሩ ውጤት ነው ...በተለይ
ባዮስታትስቲክስ! ትዕግስት በዚህ ሴሚስተርም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥላለች:: ሰሞኑን እንደውም አላየሁዋትም:: ተስፋ ቆርጣ
አይመስለኝም:: አንድም ቀን ስታማርር ሰምቻት አላውቅም::
እንዲያውም የአንደኛ ሴሚስተር ፈተናዎቻችንን ያጠናቀቅን ለት እኔ በምሬት ስናገር ሰምታኝ “ ተው እንጂ አንድ ሴሚስተር መጨረሻ
ላይ መድረስ ራሱ ቀላል አይደለም” ብላኝ ነበር........
ቅዳሜ ጥቅምት 7 1985 አ.ም. ከምሽቱ 7 ሰዓት 10 ደቂቃ
የአናቶሚ ላቦራቶሪ ፕሪክልኒካል ተብሎ የሚጠራው ህንፃ ውስጥ በግራ በኩል ከዋናው
ወለል በተወሰኑ ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ይገኛል:: በፈለግነው ሰዓት እንድንገባ ተፈቅዶልናል:: እኔ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ ቁጭ
ብዬ ማጥናት ደስ ይለኛል:: ሰሞኑን ምሽት ላይ ከዚያ አልጠፋም:: ቸርነትና እመቤትም አብረውኝ ያመሻሉ:: ታዲያ ሁልጊዜ ቀን
ቀን የምንማርባቸው አራት ሬሶች (cadavers) በነጭ ጨርቅ ተሸፍነውና በፀጥታ ተጋድመው ይታያሉ:: ፈፅሞ አይረብሹንም::
በሰፊውና በረዥሙ አናቶሚ ላቦራቶሪ ውስጥ አንደኛው ማዕዘን ጋር ካለው ጠረጴዛ ላይ ከቸርነትና ከእመቤት ጋር ሆነን የምናሳልፈው
የጥናት ግዜ ባልፅፈውም ወደፊት የማስታውሰው ይመስለኛል.....
ዛሬ ታዲያ በሚገርም ሁኔታ በትዕግስት አናቶሚ ትምህርት ያለማቁዋረጥ ለሶስት
ሰዓት አነበብኩ:: ሀቅ ልናገር ከተባለ ይህ በኔ የጥናት ሂወት ውስጥ ሁልጌዜ አይከሰትም:: ተቀምጦ ለረዥም ሰዓት ማንበብ?
እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በጣም በጣም አንዳንዴ (rare) ከመሆኑ የተነሳ ከዚህ በፊት ለሶስት ሰዓት ያለማቁዋረጥ ያነበብኩበትን
ግዜ አስታውሰዋለሁ:: አንድ ግዜ ብቻ ነው የሆነው:: ባለፈው ዓመት አንድ ቀን ሳይኮሎጂ ትምህርት ሳጠና..በቃ! በተማሪነት
ሄወቴ ስለራሴ በሂደት ከተገነዝብኩዋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ለንባብ ትዕግስት እንደሚጎድለኝ ነው:: ስለዚህ በየሃያና
ሰላሳ ደቂቃው ለማንበብ የተቀመጥኩበትን ቦታ ለቅቄ ገለል ማለት ያስፈልገኛል:: ከአናቶሚ ላቦራቶሪው ጥናት እረፍት የማደርገው
ወጣ ብዬ ከፕሪክሊኒካል ህንፃ ፊት ለፊት ካሉት ዛፎች ስር ራመድ ራመድ በማለት ወይም ቆሜ በዛፎቹ መካከል ጨረቃን ፍለጋ ወደሰማይ
በመመልከትና ሲያጋጥም ደግሞ የጅማን ደረቅ የምሽት አየር በመማግ: ይሆናል.......
No comments:
Post a Comment