ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 9 1988 አ.ም.
አርብ መስከረም 4 ቀን ጠዋት ተኝተው ከሚታከሙ ህመምተኞቼ አንዱ በውጋት እየተሰቃየ ሲጮህ ደረስኩ:: ወደሆስፒታል መኝታ ከፍል እንዲገባ የተደረገበት
ምክንያት በብልቱ ውስጥ የሚያልፈው የሽንት ቱቦ በቆየ ጠባሳ ምክንያት ተዘግቶ አላሸና ብሎት ነው (Urethral Stricture):: የዚያን ለት ጠዋት ፊኛው
ሞልቶና መሽኛው ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ስለነበር ውሃ ሽንቱ በየት ይውጣ?! በከፍታኛ ሁኔታ አመመው:: እጆቹን ፊኛው ላይ ለጥፎና ተጣጥፎ እየተንፈራፈረ ይጮሃል::
በረዥሙና ሞላላው ስርጅካል መኝታ ክፍል ውስጥ የነበሩ ሌሎች ህሙማን በሱ ሁኔታ ሁከት ውስጥ ገቡ: ተሸበሩ:: ህመመተኛው በአስቸኩዋይ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል እንዲወሰድ
በመወሰኑ የዚያ ቀን ያልጋ ዙሪያ ትምህርት (Bed Side) ተሰረዘ:: እኔም ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ከቀዳጅ ሐኪሙ ጋር በመግባት የህመመተኛው ሆድ
ተቀዶ የሽንት ፊኛው ውስጥ (Urinary Bladder) ሰው ሰራሽ ቱቦ (Catheter) ሲገባለት አየሁ:: ረዳት (Assistant) በመሆን አገለገልኩ:: በዚህም አነስ ያለች ኩራት ተሰማችኝ:: ህመምተኛው ከቀዶ ጥገናው በሁዋላ
እፎፎፎፎይ አለ:: ለጊዜው ሽንቱ ሁሉ በበሰው ሰራሽ ቱቦው በኩል ስለሚወጣ ሽንቴ መጣብኝ: የት ልሽና ገለ መለ ብሎ መጨነቅ አያስፈልገውም:: ነገር ግን የችግሩ ሁሉ ምንጭ የሆነው ጠባሳ ገና ስላልተቀረፈ ሌላ ቀዶ ጥገና ይጠብቀዋል::
ቅዳሜ መስከረም 5 ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ነበርኩ:: ላለሁበት
ቡድን የማቀርበው ዲስኩር (presentation) ስለነበር በትጋት ማንበብ ነበረብኝ:: የተጠሰኝን አርስት አልወደድኩትም:: “Lung
Nodules” ይላል:: ያልተለመደ አርስት ነው:: የሚነበብ ሰብሰብ ያለ መረጃ ስላላገኘሁ ጭንቀት የወለደው ብስጭት በጣም ተበሳጨሁ:: ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ
ማንበቤን ቀጠልኩ : ይባስ ብዬ እሁድንም በተመሳሳይ ተግባር አሳለፍኩ:: የማቀርበው ማክሰኞ ስለሆነና ሰኞ ደሞ በሌሎች ትምህርታዊ ሂደቶች ስለምጠመድ የዲስኩሩን ዘገባ እሁድ ማጠናቀቅ የግድ ነበር::
ሰኞ መስከረም 7 አዲስ ጉዋደኛ አገኘሁ:: አንድ ወጣት የጅጤሳ መግቢያ በር ላይ ይጠብቅሃል ተብዬ ስሮጥ ሄድኩ:: በኔው
የእድሜ ክልል ያል ፊቱ ጠቆር የሚል መልኩ ግን የሚያምር የሚመስል አፍንጫ ሰልካካ ፀጉረ ሉጫ ፈገግተኛ ሰው:: ያደኩበት ሰፈር ልጅ እንደሆነ ወዲያውኑ አወቅሁ:: ከዘህ በፊት እንዳየሁት እርግጠኛ ነኝ:: ግን በትክክል እንዴት እንደማውቀው ተረሳኝ:: ሰላምታ
ተለዋውጠን ስማችንን ተዋውቅን:: ግን የኔን ነገርኩት እንጂ የሱን በቅጡ አልሰማሁትም ነበር:: ለአምስት ወራት የስራ ቆይታ ወደጅማ እንደመጣ ነገረኝ:: በቅርቡ አዲስ አበባ ከሚገኘው ከተማ ፕላን ኮሌጅ (Town Planning
College) በምህንድስና እንደተመረቀ ነገረኝ:: በጅማ የሚገኘውን የመድህን ድርጅት ህንፃ እድሳት ለመከታተል ነው የመጣው:: አንደኛ ደረጃ የሄድነው አንድ ትምህርትቤት ነው:: ትንሽ ካወራን በሁዋላ ለሚቀጥለው ቀን ተቀጣጥረን ተለያየን:: በማግስቱ
ከቀኑ አስር ሰዓት መጣ :: ስሙን አሁን አውኩት ጌታሁን ይባላል:: ጥሩ አቀራረብ ያለው ልጅ ነው:: ተመቸኝ:: እንደገና ለነገ ከሰዓት ተቀጣጥረን ተለያየን::
ማክሰኞ መስከረም 9 ያዘጋጀሁትን ዘገባ ለባልንጀሮቼና ለ ዶ/ር አበበ ደሰኮርኩ:: የሳምባ ውስጥ እባጭ ሊያመጡ የሚችሉ በሽታዎችን የምችለውን ያህል ሰሌዳው ላይ ደረደርኩ:: በዲስኩሩ መጨረሻ ላይ እኔ እንደተለመደው በራሴ አልረካሁም: ዶ/ር አበበ ግን አቀራረአቤን በማድነቅ አፅናናኝ::
No comments:
Post a Comment