Saturday, December 23, 2017

ህዳር 25 1988 አ.ም.

በዚህ ቀን ጠዋት የኔ ቡድን ያልጋ ዙሪያ ትምህርት (bedside) የነበረው ሲሆን አንዱም የቡድኑ አባል ትምህርቱ ጠዋት እንደሆነ ስላልነገረኝ ሳልገኝ ቀረሁ:: አመለጠኝ::  ለኔ ፕሮግራሙ ከሰአት በሁዋላ የሚካሄድ  ነበር የመሰለኝ:: እንደዚህ መቅረት  በጣም በጣም ነው የሚከብደኝ:: ጠዋት እኔ ተረጋግቼ አገር ደህና ብዬ ስረማመድ አምስት ሰዓት ተኩል ገደማ ተቧዳኞቼ በእውቀት በልፅገው ሲወጡ አየሁዋቸው:: ያለኔ መኖር  ይህ በመሆኑ ከመጠን ባለፈ ተበሳጨሁ : ሴራ መሰለኝ:: ሁሉንም  ለተወሰኑ ሰአታት ጠላሁዋቸው:: ክፉዎች!

በዚህ ቀን ምሽት ላይ በጣለው ዶፍ የቀላቀለ ዝናብ ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቁዋረጡና ለማንበብ የሚረዳ የመብራት አገልግሎት በመጥፋቱ የተከሰተውን ሰበብ በመንተራስ የቅርብ ጉዋደኞቼና የአስተሳሰብ ተጋሪዎቼ ከሆኑት አብይና አብርሃም ጋር በመሆን ከጤና ሳይንሱ ወረድ ብላ ከምትገኘው ቆጪ ሰፈር በመጠጥ ለመዝናናት ወረድን::  ሌላ ጉዋደኛችን ተከራይቶ ከሚኖርባት ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የምትሆን ትንሽ የኪራይ ቤት ውስጥ መሬት ላይ ተቀምጠን ከዚያው አካባቢ ያስገዛነውን ጠጅ እየጠጣንና የፍልስፍና ድባብ የተላበሰ ወግ እየጠረቅን አመሸን:: እኔ መቼም ከዚህ በፊት እንዳልኩት ከምወዳቸውና ሃሳብ ከሚጋሩኝ ጉዋደኞቼ ጋር የማሳልፈውን ግዜ በፍቅር ነው የማጣጥመውና  የምወደው:: ምንም እናርግ ምን ወይም ምንም አናርግ አያገባኝም ነገር ግን ከነዚህ ጉዋደኞቼጋ መሆንና ግዜውን አብሮ ማሳለፉ ብቻውን የሚሰጠኝ ደስታ አለ::  በዚያች እስር ቤት በምታህል ትንሽ ክፍል ቤት ውስጥ  በሻማ ብርሃን እየተያየን: ጠጃችንን እየጠጣንና በየተራ ምናባችን የሰነቀውን ፍልስፍናዊ ሃሳቦች እየተካፈልን እንዲሁም እያካፈልን እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ቆየን::  ወደ ጤና ሳይንሱ ስንመለስ ደጁ በደማቅ ጨረቃ የተዋበ ነበር::  ጨረቃ ድምቡል ቦቃ.....


በበነጋው ወደተለመደ ትምህርት የተሞላ ባህር ውስጥ ገባሁ:: የውስጥ ደዌ ሕክምና ፈተና እየተቃረበ ስለነበር ትከሻዬን መክበድ አስቀድሞ ጀምሮኛል...........:: ትከሻ መክበድ ብቻ ሳይሆን ፈተና ሲደርስ አይኔም መርገብገብ ይጀምራል:: ግን ይህን ሁሉ ስለለመድኩት ምንም አይመስለኝም:: አንዳንዴ አንዳውም በዚህ ሁሉ ርካታ አልባ የህክምና ትምህርት የንባብ ሂወት ውስጥ እየተሰቃየሁ ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ:: እየተሰቃየሁ ቢሆን በውነቱ ላውቀው አልችልም:: የስሜት ህዋሳቶቼና የስሜት መሰማት አቅሜ ክፉኛ ስለቀነሱ አእምሮዬ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ባንድ አይነት ሁኔታ መቀበል ከጀመረ ቆየ....

Sunday, October 22, 2017



ጥቅምት 19 1988 አ.ም.

የውስጥ ደዌ ሕክምና (Internal Medicine) በእውነትም ሰፊ እጅግ በጣም ሰፊ ነው:: በዚህም የተነሳ አሁን ያለሁበት የተግባር ልምምድ ፈታኝ ነው:: ብዙ ብዙ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ማንበብ ይጠይቃል:: ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ መጠየቅን ይጠይቃል:: እያንዳንዱ በሽታ ለምን አንደመጣ ከየት እንደመጣ እንዴት እንደመጣ መቸ እንደሚያበቃ በምን እንደሚያበቃ ምን እንደሚያስከትል  እና ሌሎችም እልፍ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው :: እንደ የውስጥ ደዌ ሕክምና ተማሪነቴ እንዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በሰኮንድ በሚቆጠር ቅፅበት በአእምሮዬ ውስጥ ፈጥሬ መልሱንም መመለስ ይጠበቅብኛል::  ይህ ግን በተግባር ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ነው:: የቻልኩትን ያህል እሞክራለሁ:: የቻሉትን መሞከር ጥሩ ተግባር ቢሆንም ዶክተር ጴጥሮስ በሚጠይቅ ግዜ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ አውቆ አለመገኘት ተስፋ አስቆራጭ ነው:: ለአሸማቃቂ ትግሳፅ ይዳርጋል::

እያንዳንዱን በሽታ ከስሩ ጀምሮ ለማንበብና ለማስታወስ ከሚገመተው በላይ ግዜ ስለሚወስድ ብዙ ግዜ መሸምደድ ያስፈልጋል:: ሽምደዳ አጭሩ መንገድ (Shortcut) የሆነበት ፊልድ ሕክምና ብቻ ይመስለኛል::

የህክምና እውቀታችን ከሚገመግምባቸው የዘወትር መድረኮች አንዱ ያልጋ ዙሪያ ውይይት (Bed  Side) ነው:: በዚህ በበሽተኛው ዙሪያ ቆመን በምናደርገው ውይይት ከመካከላችን አንድ የህክምና ተማሪ ከተመደቡለት ህሙማን ሰለ አንዱ ዝርዝር ሁኔታ ለአስተማሪው ዶክተርና ለቡድኑ አባላት ያቀርባል::  አስተማሪው በርካታ ጥያቄዎች ይጠይቃል:: አብላጫው ጥያቄ ላቅራቢው ቢሆንም  ሁሉም የቡድኑ አባል ቢያንስ አንድ ጥያቄ ይደርሰዋል:: ሁሉም ያቅራቢውን ሐተታ ከሰማ በሁዋላ በፍጥነት በማሰብ ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀት አለበት:: አላውቀውም ማለት ቢቻልም ደጋግሞ ግን አላውቀውም ማለት ከላይ እንዳልኩት ለአሸማቃቂ ታግሳፅ የሚዳርግ ነው::


ለምሳሌ ዛሬ ጠዋት አንድ AGN (Acute Glomerulonephritis) ኬዝ ላይ Bed  Side ነበረን: ከዶክተር ጴጥሮስ ጋር:: ባጠቃላይ ጥሩ አልነበረም:: ( ማለትም ዶክተር ጴጥሮስ ሁላችንንም ገስፆናል) ማለት ነው::  ከሰዓት ደሞ Management Session ነበረን:: ይህ እንደ Bed  Side አይነት ቢሆንም በሽተኛው በሌለበት ክላስ ሩም ውስጥ የሚካሄድ ጠለቅ ያለ ትምህርት ነው:: ኬዙ Diabetic Ketoacidosis, Hypoglycemia ና Hyperosmolar coma ነበር:: እጅግ የሚያደክም ከሰዓት ነበር:: በዚህ የተነሳ ምሽቱን ከማንበብ ቦዘንኩ:: ለነገ መነበብ የነበረባቸውን Anemia ና Bone & joint tuberculosis ሳላነብ አሸለብኩ:: 

Sunday, July 9, 2017

ማክሰኞ ጥቅምት 13 1988 አ.ም.


ህክምና ትምህርት ሁሉ ስፋት ግዝፈትና ጥልቀት ዋና መገለጫ የውስጥ ደዌ ሕክምና (Internal Medicine) ነው:: የ Internal Medicine ሁለተኛ ዙር ትምህርታችንን ዛሬ ከዶክተር ጴጥሮስ ጋር በተደረገ የህሙማን ጉብኝት (Round) ጀመርን:: ባለፈው ሳምንት ደስ ባላለኝ መልኩ የተጠናቀቀው የቀዶ ሕክምና (Surgery) ትምህርት ያዞረው ናላዬ ወደነበረበት ገና አልተመለሰም:: ስለዚህም የዛሬውን Round በግማሽ አቅሌ ነው የተከታተልኩት:: ኢንተርኞቹ የሕሙማኖችን የምርመራ ውጤት እንዲሁም የህክምና ዝርዝር (Management Plan) ለዶክተር ጴጥሮስ ሲገልፁለትና በጉዳዩ ላይ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት ወስደው ሲወያዩበት: ሲከራከሩበት እኔ እነርሱን በአግራሞት እየተመለከትኩ በውስጤ ግን ፍርሃት ሲንሰራፋ ተሰማኝ:: ምክንያቱም የሚያወሩት ነገር ለኔ ባዕድ ሆነብኝ: ምንም የማውቀው ነገር የለም:: በሚቀጥለው ዓመት እኔም እንዲህ እንደነሱ ኢንተርን ስሆን አሁን እንደሚያደርጉት ማድረግ እችል ይሆን? ብየ ራሴን ጠየኩ:: ከባለፈው ሳምንት የፈተና ወቅት ሽብር ወጥቼ ሌላ ሽብር ውስጥ ገባሁ:: ጣጣ ነው:: አራተኛ ዓመት ላይ ያወኩትን በሙሉ ረስቼዋለሁ ማለት ነው......የተመደቡልኝን ህሙማን በሁዋላ ማነጋገርና መመርመር እንዳለብኝ ሳስበው ለራሴ ዘገነነኝ:: ዶክተር ጴጥሮስ ከረዥም ቁመናው: ቀላ ካለው ፊቱና በነጭ ሸሚዙ ላይ ካንጠለጠው ያማረ ከረባት የማልጠብቀው ቁጣና አዘቃዛቂ ስድቦች ያሉት ሰው ነው::  ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ኮሪደሩ ላይ እርሱኑ እየጠበቅን ስናወራ ገና ለመጀመሪያ ግዜ ያገኘን ቢሆንም ሰላም እንኩዋ ሳይለን “What are you guys doing here!?” በማለት በጅምላ ቀልባችንን ገፎ ከቆምንበት በታትኖናል::  በውስጤ ይህችን ሳምንት ከአስተማሪ ወቀሳና ስድብ ልትረፍ እንጂ ለሚቀጥለው ሳምንት አውቅበታለሁ አልኩ::
 ::

Tuesday, July 4, 2017


አርብ ጥቅምት 9  1988 አ.ም.

ዛሬ በተለካሁበት የተግባር ፈተና ሰርጀሪ ትምህርት በሂወቴ ለመጨረሻ ግዜ ተጠናቀቀ:: ስፔዣላይዝ ላለማድረግ የወሰንኩት የህክምና ዘርፍ  ስለሆነ ዳግም  በትምህርት መልኩ የሚገጥመኝ አይመስለኝም:: የጠዋቱ ፈተና አንዲት የእንቅርት በሽታ ተጠቂ የሆንች እንስት ላይ ነበር:: ብዙም ታሪካዊ አልነበረም:: ከሰዓት ግን ፈተናዬን ስጨርስ ደስተኛ አልነበርኩም:: የቃል አንካ-ስላንትያው (VIVA EXAM) አባጣ ጎርባጣ የበዛበት ነበር:: የፈተነኝ በጣም የምወደውና የማከብረው ቀዶ ሀኪም ዶክተር ሚናስ ነበር:: እንዳጋጣሚ ሆኖ ግን ፈተናው ላይ ኮከባችን አልገጠመም:: አመላለሴ አልጣመውም:: ሚናስ የተቆጣ መሰለኝ:: ነብር ሆኖ ታየኝ:: ምንድን ነው ችግሩ? የሱን ሁኔታ በማየት ከፈተናው በፊት የተጨነኩት ሳያንስ ፈተና ውስጥ እያለሁ ጨነቀኝ:: ግራ ተጋባሁ:: ከፈተናው በሁዋላ በውስጤ የነበረው ብቸኛው ተስፋ ይህ ፈተና የውስጥ (Internal) የመሆኑ ሀቅና ከፅሁፍ ፈተናው ጋ ተደምሮ የኔን የቀዶ ሕክምና ችሎታ ለመገምገም የሚኖረው ድርሻ ከሲሶ ያነሰ (30% )ብቻ መሆኑ ነው:: ሌላው 70% የሚመጣው ሙሉ በሙሉ ከመጨረሻው የውጭ የተግባር (External) ፈተና ነው:: ያ ፈተና ገና ብዙ ወራቶች ይቀሩታል:: እዚያ ላይ እበረታ ይሆን በሚል በጭንቅላቴ የተፈጠረችውን አናሳ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ጨበጥኩዋት እና ሚናስን ረሳሁት......

ሰኞ ና ማክሰኞ ጥቅምት 5 ና 6  1988 አ.ም.
የፈተናዬ ቀን ሮብ መስሎኝ ተሸብሬ ነበር:: በአይኖቼ መንቀጥቀጥ የታጀበ ጥልቅ ጭንቀትና መደናበር ውስጥ ነበርኩ:: ነገር ግን ዛሬ ሚኪያስ የኔና የርሱ ተራ አርብ መሆኑን ሲነግረኝ ደስ አለኝ::  አርብ ለት ከሚኪያስ ቀጥሎ ሁለተኛው ተፈታኝ ነኝ:: ይህን በማወቄ አሁን መረጋጋት ብቻ ሳይሆን የፈተና ፍራቻዬ ቀንሶ የንባብ አትኩሮቴ ደሞ ጨምሯል:: ሰውነቴ በቅፅበት ተፍታታ:: እጅግ በጣም ተፍታታ::  ነገ ቢሆንስ ኑሮ ፈተናዬ? አርብ በመሆኑ እድለኛ ነኝ አልኩ በውስጤ ...አንዳንድ ያላነበብኩዋቸውን ሀቆች ለመሸፈን ግዜ አገኘሁ ማለት ነው::

ማክሰኞ ለት ምሽት ላይ መብራት ተቁዋርጦ ስለነበር ለፈተና የማደርገው ዝግጅት ተስተጉዋጉሎ ነበር:: አሁንም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ይህን እየፃፍኩ ያለሁት በሻማ መብራት ነው:: እኔ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩ ባለሁበት ቅፅበት የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼ የሆኑት ቤተማርያምና በየበሩ የሻማ ብርሃን ተጠቅመው እያጠኑ ነው:: በየበሩ ማስታወሽ እየፃፍኩ እንደሆነ አውቁዋልና ይህችን የሻማ ንባብ ወቅት እንድከትባት አሳሰበኝ:: በዚህ የፈትና ዋዜማ ከመቼውም ግዜ ይበልጥ የሚፈለገው የኤሌትሪክ ብርሃን ባለመኖሩ እንዴት ፍዳችንን እያየን እንደምናጠና እንድፅፍ አሳሰበኝ:: በዚህ የጭንቅ ሰዓት አጋር ሆና የገኘችው ቀጭኗ ሻማ ምስጋና ይገባታል:: እርስዋ ባትኖርስ ኖሮ? ነገ ሮብ የሰርጀሪ ተግባር ፈተና በይፋ ይጀመራል:: እኔ ቤተማርያምንና በየበሩን ትቼ አስር ሚሊ-ግራም ዲያዘፓም ውጬ ልተኛ ዝግጅቴን አጠናቀኩ......




Sunday, June 25, 2017

የሰርጀ   ፈተና ሰሞን

እሁድ መስከረም 27 1988 አ.ም.

በዚህ እለት ጠዋት ድብርት ተጫጭኖኝ የነበረ ቢሆንም ከሰዓት በሁዋላ ግን ከቅርብ ወዳጆቼ በተደረገልኝ የቂማ (ጫት) ግብዣ ምክንያት ንቃትን ተላብሼ ነበር:: በሰርጀሪ ፈተና መቃረብ ያደረብኝ ስጋት እንዳለ ሆኖ ጫቱን ግን አጣጣምኩት:: ነቃሁበት! ምሽት ላይ ጥይት ሆንኩና ወደሆስፒታል መሄድ አማረኝ:: ሕሙማኖቼን መጎብኘት አሻኝ:: እናም ወደ ዋርድ ሄድኩ:: እዚያ ስደርስ ዶክተር ሚናስን  አየሁት:: ተረኛው ቀዶ ሀኪም እሱ ነበር:: እሱም ጥይት ሆኖ ነበር:: በዶክተር ሚናስ ዙሪያ ግርግር ነገር አየሁ:: በመጀመሪያ ለምን እንደሆነ አላወኩም ነበር በሁዋላ ግን አንድ በመኪና አደጋ ደረቱና ሳምባው የተጎዳ ህመምተኛ እንዳለ ተረዳሁ:: ዶክተር ሚናስ ለዚህ ሰው ደረት-ቱቦ (chest tube) አስገባለት:: እኔና በዚያ የነበሩ ሌሎች ታታሪ የህክምና ተማሪዎች የደረት ቱቦ አገባብ ተመለከትን:: የሚገርመው ግን ዶክተር ሚናስ ስለደረት ቱቦ ወይም ስለ ደረት ጉዳት ይነግረናል ብዬ ስጠብቅ የሌላ ራስ ቅሉ ላይ የጦር ጉማጅ የተሰካበት ህመምተኛ ኤክስ ሬይ ይዞ የነበረ ሲሆን ስለ head injury ሰፊ ትንተና አደረገልን:: በራስ ቅል ጉዳት (Head Injury) ዙሪያ ሰፊና ጠቃሚ እውቀት አስጨበጠን:: ቅሟል እንዴ?  ከዶክተር ሚናስ ትንተና በሁዋላ ወደ ምድብ አልጋዎቼ ሄድኩ:: አንድ አዲስ ህመምተኛ ነበረኝ:: እሱም በመኪና አደጋ ነው የመጣው:: ቀኝ ክንዱ ላይ ያለው ጡንቻ ተቦጭቁአል (Avulsion):: ለነገ ጠዋት ራውንድ የሚሆነኝን ያህል መረመርኩትና ወደ ዶርም ተመለስኩ....

አርብ ጥቅምት ሁለት ቀን 1988 አ.ም.

ዛሬ ቅር ያለኝ ነገር አለ:: የቀዶ ጥገና ረዳት መምህር የሆነው ዶክተር አብርሃም በእሳት የተቃጠለ (Burn) ህመምተኛ ላይ ያልጋ ዙሪያ ውይይት (Bed Side) እንደሚያደርግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን እኔም ሆንኩ የኔ ቡድን አባላት ስለ Burn አንብበንና ለጥያቄ ራሳችንን አዘጋጅተን ነበር:: ነገር ግን ዶክተር አብርሃም ሆን ብሎ ይሁን በሌላ የተመደበውን ሰዓት ስለ አንጀት እጢ (Colon cancer) በማውራት ገደለው:: የሚገርመው ስለ አንጀት እጢ ማውራቱ ሳይሆን ሆን ብሎ ነው ሊያስብለኝ በቻለ መልኩ የማናውቀውንና ትኩረት መስጠት የማይገባንን እንዲሁም በልካችን ያልሆነ  ነገር ነበር የሚያወራው:: እርግጠኛ ነኝ ያወራው ነገር ለፈተናም ሆነ ለተግባር አይጠቅምም:: ቅር መሰኘት ብቻ ሳይሆን እኔ ውስጤ ቅጥል ብሎ ነበር:: ለምን እንዲህ አደረገ ብዬ ራሴን ስጠይቅ የመጣልኝ ብቸኛው ግምት አብረውን Bed Side ሊካፈሉ የመጡ የ Nursing ተማሪዎች ስለነበሩ በነሱ ፊት ከኛ ከሕክምና ተማሪዎቹ እጅግ የላቀ እውቀት እንዳለው ላማሳየት ፈልጎ ይሆናል የሚል ነው:: ነው ደሞ!
በነገራችን ላይ ሌላም ቅር ያለኝ ነበር ዛሬ:: እናቴ በየወሩ የምትልክልኝን ሃምሳ ብር ዛሬ ጠብቄ የነበረ ቢሆንም ሳትልክ ቀረች::

እሁድ ጥቅምት 4  1988 አ.ም. ከቀኑ አስር ሰዓት

ሰርጀሪ የተግባር (Practical) ፈተና  ነገ ሰኞ ይጀመራል:: የኔ የፈተና ቀን ግን ሮብ ነው:: እንደተለመደው በዚህ የተግባር ፈተና ዋዜማ እለት በውስጤ ሽብር የነገሰ ሲሆን በራስ መተማመኔ ደግሞ ባይ ባይ ብሎኝ ሂዷል:: በርካታ ይህን አይነት የአእምሮ ውጥረትና የስሜት ልሽቀት የሰፈነባቸው ቀናት አሳልፊያለሁ ነገር ግን ልለምደው አልቻልኩም:: ሁልግዜ እንደአዲስ ነው:: በተለይ በተለይ የማልረሳው የሁለተኛ ዓመት (ፒሲ-ዋን) የመጨረሻ ቀን የፊዚዮሎጂ የቃል ፈተና ልፈተን አምስት ደቂቃ ሲቀር የተሰማኝን ስሜት ነው:: አሁን ለማመን በሚያስቸግረኝ ሁኔታ የልቤ ምት ጠፍቶብኝ ነበር:: በተለምዶ ሰው ሲደናገጥ የልቡ ምት ይበልጥ ይሰማል:: የኔ ግን ጠፋ:: የልቤን ምት እንደገና መስማት የጀመርኩት ስሜ ተጠርቶ ፈታኞቹ ወደነበሩበት ቢሮ ስገባ ነው:: ለማንኛውም አሁን የአምስተኛ ዓመት የቀዶ ጥገና የውስጥ (Internal) የተግባር ፈተና ነው ይሄ:: ማለቴ ገና ዓመቱ መጨረሻ ላይ የውጭ (External) ፈተና ይኖረናል:: የውስጤ መሸበር ግን እንደተጠበቀ ነው:: ባጠቃላይ ለፈተናው ዝግጁ አይደለሁም:: ደግነቱ ይህ የውስጥ ፈተና ሲሆን የውስጥ ስሜቴን ደሞ ማንም አያውቅም::  በሚቀጥሉት ተቂት ቀናት ውስጤን ለማረጋጋት ይረዳል ብዬ ያሰብኩት ስልት (ስትራቴጂ) የሚከተለው ነው:: አርስቱ የሰነፍ ተማሪ አቁዋራጭ ስልት ብለው ደስ ይለኛል::

  1. በምንም አይነት መፅሐፍ (Text Book) ከማንበብ መቆጠብ
  2. ደብተሮችንና ማስታወሻዎችን በፍጥነት ማንበብ::  የበሽቶች አናቶሚና ፊዚዮሎጂ ላይ ግዜ አለማባከን: ቀጥታ ወደጉዳዩ ገበመግባት ሕክምና: ላቦራቶሪ: የበሽታው መዘዝ (complications)ና ለበሽታው የሚያስፈልገው የቀዶ ጥገና ሕክምና የተመለከቱት ላይ ማተኮር::
  3. አላስፈላጊ ናቸው ብለህ ያሰብካቸውንና ሲነበቡ ደስ የማይሉ እንዲሁም ለመረዳት ቀላል ያልሆኑ ሀቆችን (facts) ዝለላቸው::
  4. ያልጋ ዙሪያ (Bed Side) ትምህርት ላይ የከተብካቸውን ማስታወሻዎች አንብብ::
  5. በምታነብበት ግዜ ህመምተኛውን አስብ::
  6. በምታነብበት ግዜ መፃፍ አቁም::
  7. ዛሬ ማታ ለማንበብ ይመቹኛል ወይም አስፈላጊ ናቸው ብለህ ያመንክባቸውን አርስቶች ምረጥ::
  8. መልካም ዕድል::

ልብ በል/ይ በዚሁ ቀን ምሽት ላይ በጥናት ሳልተጋ ቆይቼ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲሆን መኝታ ክፍላችን ውስጥ ካለው ጠረጴዛ አጠገብ ቁጭ ብልም ቀን ለራሴ ቃል የገባሁትን ከላይ ቁጥር ሰባት ላይ የሰፈረውን ዘልዬው ወደ አልጋዬ አመራሁ ......


Friday, March 31, 2017



መስከረም  26 ቀን 1988 አ.ም. ቅዳሜ ጠዋት

ህልሜ

በሠርጀሪ ፈተና መቃረብ የተነሳ ሰሞኑን ከመተኛቴ በፊት የእንቅልፍ ኪኒን (diazepam) እወስዳለሁ:: ታዲያ ለሽ ብዬ ነው የምተኛው:: እኔ ብቻ ሳልሆን ቁጥራቸው ቀላል የማይሰኝ ባልንጀሮቼ ያለሱ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው ውስጥ ውስጡን ሰምቻለሁ:: ብቻ ይህ የአደባባይ ጉዳይ አይደለም::

ታዲያ በእንቅልፍ ክኒኑ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ትናንት ሌሊት ለዛሬ ሰፋ ያለና የሚገርም አይነት ሕልም ታየኝ:: የህልሙን እያንዳንዱን ድርጊት ቁልጭ ባለ መልኩ በማስታወሴ ነው ይበልጥ የተገረምኩት....

የቀዶ ጥገና ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆነው ዶክተር አለምሰገድ ሌክቸር እየሰጠን ነበር:: የነበርንበት ክፍል ግን ከወትሮው ሌክቸር ሆል የተለየ ነበር:: ሴሚናር ከምናደርግባቸውም ክፍሎች የተለየ ነበር:: ከኔ ቡድን (group) የነበርኩት እኔ ብቻ ነኝ:: ሌሎቹ የት እንደነበሩ ትዝ አይለኝም:: የሆነ ሰው ዶክተር አለምሰገድን ውጭ ቆሞ እየጠበቀው ነበር:: ስለዚህም ዶክተር አለምሰገድ ሌክቸሩን ለማሳጠር በፍጥነት እየተናገረ ነበር:: በእጁ የሲጋራ መለኮሻ ላይተር ይዞ ነበር:: ድንገት ግልፅ ባልሆነልኝ ምክንያት ላይተሩን ለኮሰው:: በዚያው ቅፅበት ከላይተሩ ጫፍ የሚስፋፋ ነጭ ሰማያዊ ጭስ መውጣት ጀመረ:: እኔ ካርቦን ሞኖክሳይድ ነው ብዬ አሰብኩ:: ወይም ሌላ ለሂወት የሚያሰጋ ኬሚካል መሰለኝ:: ክፍሉ ውስጥ የነበረ ተማሪ በሙሉ በያቅጣጫው ሂወቱን ለማትረፍ መራወጥ ጀመረ:: አንዳንዶቹን በጭሱ ታፍነው የክፍሉ ወለል ላይ ሲወድቁ ተመለከትኩ:: ዶክተር አለምሰገድ የት እንደደረሰ አላውቅም:: እኔም ራሴ ትንፋሽ የማጠር ስሜት ይሰማኝ ጀመር::  ባለሁበት ድካምና ጡንቻዎቼ ሲዝሉ ተሰማኝ:: ከየት እንደመጣ ያላወኩት አንድ ሕፃን ልጅ ጋር ከክፍሉ ለመውጣት የምንችለውን ያህል ተፍጨርጭረን መጨረሻ ላይ ተስካልንና ወጣን:: ከዚያም ሩጫዬን ከልጁጋ አብሬ ቀጠልኩ:: ከክፍሉ እንደወጣን ከፊት ለፊታችን ያጋጠመን በረጃጅም የእህል ማሳ ነበር:: ወደማሳው እየሮጥን ገባንበትና በውስጡም ሁነን ሩጫችንን ቀጠልን:: በማሳው የወድያኛ ጥግ ደርሼ አልፌው ስወጣ አብሮኝ የነበረው ልጅ የለም: ብቻዬን ነበርኩ:: ከፊት ለፊቴ መንደር አየሁ:: በአንድ አይነት ሁኔታ የተሰሩ ቤቶች አየሁ::  ቤቶቹ ነጫጮች ሲሆኑ በልጅኔቴ የተማርኩበት ቅዱሥ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ቀሳውስት ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶችን ይመስላሉ:: ወደቤቶቹ አቅጣጫ እያመራሁ ሳለ አንዲት ኮረዳ በድንገት መንገዱ ላይ  ብቅ ብላ አናገረችኝ:: እኔም በሌክቸር ሆሉ ውስጥ የተፈጠርውን ነገርኩዋት:: እርሱዋም ለደህንነቴ በማሰብ አዳሬን በመንደሩ እንዳደርግ መከረችኝ:: ይህን ካለችኝ በሁዋላ ወዴት እንደሄደች አላውቅም:: እኔ ግን ርምጃዬን ቀጠልኩ:: በመንደሩ ውስጥ ስጉዋዝ በመንገዱ ግራና ቀኝ ትልልቅ አለቶችን የሚፈልጡና የሚጠርቡ ሰዎችን አየሁኝ:: ካለሁበት ቆሜ ወደፊትለፊቴ  ስመለከት በርቀት የረጃጅም ህንፃዎች ጫፎች አየሁ:: ጂማ እንደነዚህ አይንት ፎቆች አይቼ አላውቅም:: ካለሁበት ወደየት እንዳመራሁ ትዝ አየለኝም ግን ሕልሙ እዚያ ላይ አለቀ...........


Tuesday, March 14, 2017


መስከረም 12 1988 አ.ም.

ዛሬ በተማሪዎች ቴሌቪዥን መመልከቻ አዳራሽ ውስጥ “No Place to Hide” የተሰኘው ፊልም ሲታይ እኔም ታደምኩ:: እጅግ የወደድኩት ፊልም ነው:: በልቤ ውስጥ ካለው ነገር ጋ የሚሄድ ጠንካራ ትርጉም አገኘሁበት:: በፊልሙ ውስጥ ያለው ዋና ገፀ ባህሪ በኔ ሚዛን እጅግ መልካም እንዲሁም እውነተኛ: እውነትን ለመታደግ ብሎም ሕግን ለማስከበር የቆመ ስለነበር ወደድኩት::



መስከረም 13 1988 አ.ም. - ራሴን ሳክም

አልፎ አልፎ እንደሚያደርገኝ ዛሬ ደብሮኝ ነበር:: ቀላል ድብርት አይደለም:: ትልቅ የሆነ ድብርት ከነጉዋዙ:: የመሰላቸት ስሜት የገነነበትና በራስ የመተማመን ስሜት ጥቂት የሆነበት:: “የፍልስፍና ሙድ” ውስጥ ነበርኩ:: አለማችን እግዚአብሔር ቆንጆ አድርጎ ቢፈጥራትም በዘመንና በሰው ልጆች ትብብር ቆሽሻ ታየችኝ:: የራሴን ምንነትና በዚህ የቆሸሸ ዓለም ላይ ያለኝን ቦታ ለራሴ ጠየቅሁ:: ራሴን የሆነ ቦታ መመደብ ፈለግሁ ግን ቦታ አጣሁ:: ያለማቁዋረጥ እንቶፈንቶ አሰብኩ:: ለቅፅበት ፍርሃት ውስጥ ገባሁና ወጣሁ:: የያዝኩት ሕክምና ትምህርት ዳግም ከመቸውም የበለጠ ከብዶ ታየኝ:: ተስፋ መቁረጥ ጀምሬ ተስፋ መቁረጤ ራሱ አስፈራኝና ተውኩት::በመፅሐፍ ቅዱስና በታገል ሰይፉ ግጥም ላይ ያነበኩትን የእምባቆምን ለቅሶ አስታውስኩ:: በእግዚአብሔር ታላቅ ተስፋን ለማድረግ ወሰንኩና መተንፈስ ቀጠልኩ........



መስከረም 14 ና 15 1988 አ.ም. - ቻዎ ሰርጀሪ

ዙሩን ለመጨረስ ሶስት ሳምንት ሲቀረኝ ቀዶ ጥገና (surgey) ትምህርት በማያሻማ ሁኔታ ሰለቸኝ:: በቃ በግልፅ ለመናገር  ከዚህ በሁዋላ የተንዛዛ (ቦሪንግ) ነው:: ይህ አምና ስፔሻላይዝ አደርግበታለሁ እንዲሁም በቀዳሚነት እወደዋለሁ ያልኩት ፊልድ የኔ እንዳይደለ ጥርት ብሎ ታየኝ....ቻዎ



መስከረም 17 1988 አ.ም. ሐሙስ ጠዋት - መስቀል

ከዛሬው ይልቅ ስለትናንት ማታ ልናገር:: ለኔና ለጉዋደኞቼ ጥሩ ምሽት ነበር:: እኔና እነመንጌ የመስቀል ዋዜማ በመሆኑ እንደተለመደው: ምሽቱን ወጣ ብለን ለማሰለፍ ሳንቲም አሰባሰብን:: ሳንቲም ካላቸው ጉዋደኞቻችን ተበደርን: አሮጌ ልብሶችና ጫማዎች ገበያ ወደን ጆሮ ግንዳቸውን አልን: ከዚያም ወደ ጅማ ከተማ እምብርት ሄድን...ጠለቅን:: በቅርብ የተዋወቁት መሃንዲሱ ጉዋደኛዬ ጌታሁን አብሮን ስለነበር የኔ ደስታ እጥፍ ነበር:: ሌላው ምሽቱን ልዩ ያደረገው ግርማ ሁንዴ ለመጀመሪያ ግዜ ምሽት ላይ እኛን መቀላቀሉ ነው:: እርሱ ደሞ ቀን ላይ አዲስ መጫሚያ ገዝቶ ስለነበር ተመችቶት ነበር:: ብዙ ግዜ እንዳደረግነው ወይን ጠጅ እየጠጣን ደነስን:: ዶርማችን ስንመለስ መንግስቱ ከሌሎቻችን በገዘፈ ሞቅታ ተኝተው የነበሩትን ጉዋደኞቻችንን ቀሰቀሳቸው:: ነገርግን እነሱ መንም ቅር አልተሰኙበትም:: ምክንያቱም መስቀል በተለምዶ የጉራጌ በዓል ነው ስለሚባል .............

Wednesday, February 8, 2017

ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 9 1988 አ.ም.

አርብ መስከረም 4 ቀን ጠዋት ተኝተው ከሚታከሙ ህመምተኞቼ አንዱ በውጋት እየተሰቃየ ሲጮህ ደረስኩ:: ወደሆስፒታል መኝታ ከፍል እንዲገባ የተደረገበት ምክንያት በብልቱ ውስጥ የሚያልፈው የሽንት ቱቦ በቆየ ጠባሳ ምክንያት ተዘግቶ አላሸና ብሎት ነው (Urethral Stricture):: የዚያን ለት ጠዋት ፊኛው ሞልቶና መሽኛው ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ስለነበር ውሃ ሽንቱ በየት ይውጣ?! በከፍታኛ ሁኔታ አመመው:: እጆቹን ፊኛው  ላይ ለጥፎና ተጣጥፎ እየተንፈራፈረ ይጮሃል:: በረዥሙና ሞላላው ስርጅካል መኝታ ክፍል ውስጥ  የነበሩ ሌሎች ህሙማን በሱ ሁኔታ ሁከት ውስጥ ገቡ: ተሸበሩ::  ህመመተኛ በአስቸኩዋይ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል እንዲወሰድ በመወሰኑ የዚያ ቀን ያልጋ ዙሪያ ትምህርት (Bed Side) ተሰረዘ:: እኔም ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ከቀዳጅ ሐኪሙ ጋር በመግባት የህመመተኛ ሆድ ተቀዶ የሽንት ፊኛው ውስጥ (Urinary Bladder) ሰው ሰራሽ ቱቦ (Catheter) ሲገባለት አየሁ:: ረዳት (Assistant) በመሆን አገለገልኩ:: በዚህም አነስ ያለች ኩራት ተሰማችኝ:: ህመምተኛው ከቀዶ ጥገናው በሁዋላ እፎፎፎፎይ አለ:: ለጊዜው ሽንቱ ሁሉ በበሰው ሰራሽ ቱቦው በኩል ስለሚወጣ ሽንቴ መጣብኝ: የት ልሽና ገለ መለ ብሎ መነቅ አያስፈልገውም:: ነገር ግን የችግሩ ሁሉ ምንጭ የሆነው ጠባሳ ገና ስላልተቀረፈ ሌላ ቀዶ ጥገና ይጠብቀዋል::

ቅዳሜ መስከረም 5 ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ነበርኩ:: ላለሁበት ቡድን የማርበው ዲስኩር (presentation) ስለነበር በትጋት ማንበብ ነበረብኝ:: የኝን አርስት አልወደድኩትም:: “Lung Nodules” ይላል:: ያልተለመደ አርስት ነው:: የሚነበብ ሰብሰብ ያለ መረጃ ስላገኘሁ ጭንቀት የወለደው ብስጭት በጣም ተበሳጨሁ:: ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ ማንበቤን ቀጠልኩ : ይባስ ብዬ እሁድንም በተመሳሳይ ተግባር አሳለፍኩ:: የቀርበው ማክሰኞ ስለሆነና ሰኞ ደሞ በሌሎች ትምህርታዊ ሂደቶች ስለምጠመድ የዲስኩሩን ዘገባ እሁድ ማጠናቀቅ የግድ ነበር:: 

ሰኞ መስከረም 7 አዲስ ጉዋደኛ አገኘሁ:: አንድ ወጣት የጅጤሳ መግቢያ በር ላይ ይጠብቅሃል ተብዬ ስሮጥ ሄድኩ:: በኔው የእድሜ ክልል ያል ፊቱ ጠቆር የሚል መልኩ ግን የሚያምር የሚመስል አፍንጫ ሰልካካ  ፀጉረ ሉጫ ፈገግተኛ ሰው:: ያደኩበት ሰፈር ልጅ እንደሆነ ወዲያውኑ አወቅሁ:: ከዘህ በፊት እንዳየሁት እርግጠኛ ነኝ:: ግን በትክክል እንዴት እንደማውቀው ተረሳኝ:: ሰላምታ ተለዋውጠን ስማችንን ተዋውቅን:: ግን የኔን ነገርኩት እንጂ የሱን በቅጡ አልሰማሁትም ነበር:: ለአምስት ወራት የስራ  ቆይታ ወደጅማ እንደመጣ ነገረኝ:: በቅርቡ አዲስ አበባ ከሚገኘው ከተማ ፕላን ኮሌጅ (Town Planning College) በምህንድስና እንደተመረቀ ነገረኝ:: በጅማ የሚገኘውን የመድህን ድርጅት ህንፃ እድሳት ለመከታተል ነው የመጣው:: አንደኛ ደረጃ የሄድነው አንድ ትምህርትቤት ነው::  ትንሽ ካወራን በሁዋላ ለሚቀጥለው ን ተቀጣጥረን ተለያየን::  በማግስቱ ከቀኑ አስር ሰዓት መጣ :: ስሙን አሁን አውት ጌታሁን ይባላል:: ጥሩ አቀራረብ ያለው ልጅ ነው:: ተመቸኝ::  እንደገና ለነገ ከሰዓት ተቀጣጥረን ተለያየን::


ማክሰኞ መስከረም 9 ያዘጋጀሁትን ዘገባ ለባልንጀሮቼና ለ ዶ/ር አበበ  ደሰኮርኩ:: የሳምባ ውስጥ እባጭ ሊያመጡ የሚችሉ በሽታዎችን የምችለውን ያህል ሰሌዳው ላይ ደረደርኩ:: በዲስኩሩ መጨረሻ ላይ እኔ እንደተለመደው በራሴ አልረካሁም: ዶ/ር አበበ ግን አቀራረአቤን በማድነቅ አፅናናኝ::